‹‹ዘመኑን ዋጁት›› (ኤፌ. ፭፥፲፮)

ዕለታት በወራት ተተክተው፣ አዲስ ዓመት ዘመንን ወክሎ በጊዜ ዑደት ውስጥ ያልፋሉ፡፡  ሰማይና ምድር እያፈራረቁ ቀንና ሌሊትን፣ ፀሐይንና ዝናብን ይለግሳሉ፡፡ ክስተቶቹም አልፈው ዳግም እስኪመለሱ በሌሎች ይተካሉ፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ‹‹ጊዜ›› እንደዚሁ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይቀጥላል፡፡

የሰው ልጅ ሕይወትም በዘመናት ዑደት ውስጥ ያልፋል፤ በሥነ ፍጥረቱና በዕድገቱም በምድር ላይ ይኖራል፡፡ ዘወትር የፈጠረውን አምላክ እግዚአብሔርን በመፍራት ይኖር ዘንድም በዐሥርቱ ትእዛዛት እና በእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ውስጥ ሕያው ሆኖ ሰማያዊ ርስትን ይወርስ ዘንድ ዕድል ፈንታው ነው፡፡

ሕይወታችን በዘመናት መተመኑ የጊዜን ዋጋ ዐውቀን በሕገ እግዚአብሔር እንድንኖር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹‹ቀኖቹ ክፎዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት፡፡ ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ፡፡›› አላቸው፡፡ ዘመኑን ለመዋጀት ወይንም ለመግዛት (የራስ ለማድረግ) እግዚአብሔር በፈቀደው መንገድ መኖር እንዳለብን ሐዋርያው በመልእክቱ ያስተምረናል፡፡ ስንፍና የተባለው ኃጢአት በእግዚአብሔር ዘንደ የተወገዘ በመሆኑ ከእርሱ ፈቃድ እንድንወጣ ያደርገናል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ምግባርን መፈጽም ግን ከእኛ ይጠበቃል፡፡ (ኤፌ. ፭፥፲፮-፲፯)

ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ የእግዚአብሔርን ፍቃድ ስለመተግበር ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ፡፡ ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው። ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹምንም መርምሩ፡፡ በተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበት አስቡ እንጂ በትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር፡፡ በአንዱ ሰውነታችን ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉ፥ ሥራቸውም ልዩ ልዩ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ሁላችን ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው አካሎች ነን፤ ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፡፡ እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፡፡ ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር፡፡ የሚያገለግልም በማገለግሉ ይትጋ፤ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛም በትጋት ይግዛ፤ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት፡፡ ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ መምህሮቻችሁንም  አክብሩ፡፡ ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ፡፡ በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልን አዘውትሩ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሰውም ጋርም አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እኛ አዋቆች ነን አትብሉ፡፡ ክፉ ላደረገባችሁ ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ፡፡ ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቍጣን አሳልፏት፥ “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራቱን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ። ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።›› (ሮሜ. ፲፪፥፩-፳፩)

ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ዘመኑን መዋጀት የምንችለው በእግዚአብሔር ፈቃድ በመኖር ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ሰዎች በዓለማዊ አስተሳሰብ በመጓዛቸው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥተዋል፡፡ ፈጣሪያቸውን የሚያሳዝን እና የሚያስከፋ ተግባርም ይፈጽማሉ፤ የእግዚአብሔርን ሕልውና በመርሳትና አምላክነቱን በመካድ ለባዕድ አምልኮ ተገዝተዋል፤ ሰንበታትን ከማክበር ይልቅ በጭፈራና በስካር እንዲሁም በተለያዩ ሱሶች ዝሙት የሚፈጸምባቸው ሥፍራዎችን ያዘወትራሉ፤ እርስ በርስ በመዋደድ፣ በመከባበርና በመተዛዘን መኖር ሲገባ በመናናቅ እና በጥላቻ የይምሰል ኑሮ ይመራሉ፤ በጥቅም ከመገዛታቸው የተነሣ በሰዎች ላይ በጭካኔ ክፋትና በደል ከመፈጸማቸው ባሻገር እስከ መግደል ይደርሳሉ፤ በሐሰት መንደር ሰምጠው እውነትን ይክዳሉ፤ ሀብትና ንብረትን በማካበት ምድራዊ ሕይወታቸውን ብቻ ለማሳካት ስርቆት፣ ምዝበራ እና የመሳሰሉትን እኩይ ተግባራት ይፈጽማሉ፡፡ ይህም የእግዚአብሔር አምላካችን ቁጣ በእኛ ላይ እንዲበረታ በማድረጉ ምድር በመቅሠፍት ታወከች፡፡

ሰው በተደላደለ ኑሮ ቢኖርም ሰላምና ፍቅር ከሌለው ደስታን እንደማያገኝ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ያወቀው እውነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን በጦርነት እና በበሽታ ሰላም ካጣች እንዲሁም በመካከላችን ፍቅር ከጠፋ ዘመናት ተቆጥረዋልና፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክ ወደ እርሱ ተመልሰን በሰላም፣ በፍቅር እና በአንድነት እንድንኖር ለአዲስ ዘመን አድርሶናልና ዘመኑን መዋጀት ከእኛ ይጠበቀል፡፡ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ  እመለሳለሁ›› እንዳለን በንስሓ ሕይወት ወደ እርሱ በመመለስ፣ በሕጉ በመኖር እና ትእዛዛቱን በመተግበር የእግዚአብሔርን ፍቃድ እንፈጽም፡፡ (ሚል. ፫፥፯)

ዘመኑን በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንኖር ዘንድ የአምላካችን ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡