ዘመነ ክረምት – ክፍል ስድስት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል አምስት ዝግጅታችን ሦስተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል በተለይ ደሰያትን እና ዓይነ ኵሉን መነሻ በማድረግ ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ደግሞ አራተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል የሚመለከት ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

፬. ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን፣ መዓልት

ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጕሜን ፭ (፮) ቀን (ከአብርሃም እስከ ዮሐንስ ዋይዜማ) ድረስ ያለው አራተኛው ክፍለ ክረምት ‹ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን መዓልት› ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ክረምት ውስጥ በሚገኙ ቀናት እነዚህን ፍጥረታት የሚመለከቱ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች በቤተ ክርስቲያናችን ይነገራሉ፤ ይተረጐማሉ፤ ይመሠጠራሉ፡፡ ‹ጎሕ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን፣ መዓልት› ዅሉም የግእዝ ቃላት ሲኾኑ ተመሳሳይ ትርጕምና ጠባይዕ ያላቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡ ‹ጎህ፣ ነግህ እና ጽባሕ› – ንጋትን፣ ማለዳን፣ ሌሊቱ ወደ ቀን፤ ጨለማው ወደ ብርሃን የሚሸጋገርበትን ክፍለ ጊዜ ይገልጻሉ፡፡ ብርሃን ደግሞ የጨለማ ተቃራኒ፣ የፀሐይ ብርሃን የማይታይበት ክፍለ ዕለት ሲኾን ‹መዓልት› ማለትም በአንድ በኩል የፀሐይ ብርሃን የሚታይበት ጊዜን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከእሑድ እስከ ሰኞ ያሉትን፣ እንደዚሁም ከ፩ – ፴ የሚገኙ ዕለታትን ያመላክታል (ዘፍ. ፩፥፭-፴፩)፡፡

ስለ ንጋትና ብርሃን ለመናገር በመጀመሪያ ስለ ፀሐይ፣ ስለ ጨረቃ እና ከዋክብት አፈጣጠር በጥቂቱ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በዕለተ ረቡዕ በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት ‹‹ለይኩን ብርሃን፤ ብርሃን ይኹን›› ባለ ጊዜ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት ተፈጥረዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ‹ብርሃን ይኹን› አለ፤ ብርሃንም ኾነ፡፡ እግዚአብሔርም ብርሃኑ መልካም እንደ ኾነ አየ፤ እግዚአብሔርም በብርሃኑና በጨለማው መካከል ለየ፤ እግዚአብሔርም ብርሃኑን ‹ቀን›፣ ጨለማውንም ‹ሌሊት› ብሎ ጠራው፤›› እንዲል (ዘፍ. ፩፥፫-፬)፡፡ የፀሐይ ተፈጥሮዋ ከእሳትና ከነፋስ ሲኾን ጨረቃንና ከዋክብትን ደግሞ ከነፋስና ከውኃ አርግቶ ፈጥሯቸዋል፡፡ ሲፈጥራቸውም ከዅሉም ፀሐይን፤ ከከዋክብት ደግሞ ጨረቃን አስበልጦ ነው፡፡ የፈጠራቸውም እርሱ ሊጠቀምባቸው ሳይኾን ለሰው ልጅ እና በዚህ ዓለም ለሚገኙ ፍጥረታት እንዲያበሩ ነው፡፡ እነዚህ የብርሃን ምንጮች (ፀሐይ እና ጨረቃ) ልዩ ልዩ ምሳሌያት አሏቸው፤ ከእነዚህ መካከልም በጻድቃንና በኃጥኣን መመሰላቸው አንደኛው ነው፡፡

ጻድቃን ዅልጊዜ በምግባር፣ በሃይማኖት ምሉዓን በመኾናቸው በፀሐይ፤ ኃጥኣን ደግሞ በምግባር አንድ ጊዜ ሙሉ፣ ሌላ ጊዜ ጐደሎ ማለትም አንድ ጊዜ ደግ ሌላ ጊዜ ክፉ እየኾኑ ግብራቸውን በመለዋወጥ ይኖራሉና በጨረቃ ይመሰላሉ፡፡ የፀሐይ እና ጨረቃ አካሔዳቸው በሰማይና በምድር መካከል ነው፡፡ ጻድቃንም በተፈጥሯቸው ምድራውያን ኾነው ሳሉ ሰማያዊውን መንግሥት ይወርሳሉ፡፡ ፀሐይ እና ጨረቃ ሠሌዳቸው ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኃ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ ጠባይዓት እርስበርስ ተስማምተው ብርሃንን እንዲሰጡ አድርገዋቸዋል፡፡ ስለዚህም በነፋሱ ፍጥነት፣ በእሳቱ ሙቀት፣ በውኃው ቅዝቃዜ ይስማማቸዋል፡፡ ይህም የመምህራን መንፈሳዊ ቍጣ ምሳሌ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ጠባያቸው እንደ ውኃ የቀዘቀዘ ቢኾንም የእግዚአብሔርን ክብር የሚያቃልሉ፣ ቅዱሳንን የሚጥላሉ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚፃረሩ መናፍቃን ሲመጡ ግን እንደ ነፋስ በሚፈጥን፣ እንደ እሳት በሚያቃጥል መንፈሳዊ ቍጣ ተነሣሥተው ይገሥፃሉ፤ ይመክራሉ፤ ያስተምራሉ፡፡ አንድም እነዚህ ሦስቱ የፀሐይ እና የጨረቃ ሠሌዳዎች የሥላሴ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይኸውም እሳት በመለኮት፤ ውኃ በትስብእት፤ ነፋስ በመንፈስ ቅዱስ ይመሰላል (መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

በሌላ ምሥጢር ስንመለከታቸው ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን፣ መዓልት ወይም ዅሉንም በአጠቃላይ በብርሃን ምንጭነት ወይም በብርሃን ብንሰይማቸው የብርሃን ምንጭ ወይም ብርሃን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በጨለማው ዓለም፤ በጨለማው ሕይወታችን፤ በጨለማው ኑሯችን የሕይወትን ወጋገን፣ ንጋት፣ ብሩህ ቀን የሚያወጣ አምላክ ነውና (ዮሐ. ፩፥፭-፲)፡፡ ለዚህም ነው ‹‹እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኀኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማነው?›› በማለት ቅዱስ ዳዊት የሚዘምረው (መዝ. ፳፮፥፩)፡፡ ስለ ኾነም እኛ ክርስቲያኖች ብርሃን በተባለ በእግዚአብሔር መታመን ያስፈልገናል፡፡

ዳግመኛም የእግዚአብሔር ሕግ ብርሃን ይባላል፡፡ ብርሃን ጨለማን እንደሚያስወግድ ዅሉ የእግዚአብሔር ሕግም ከኀጢአት ባርነት፣ ከሲኦል እሳት ያድናልና፡፡ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፤ ለመንገዴም ብርሃን ነው›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ. ፻፲፰፥፻፭)፡፡ እንደዚሁም ብርሃን ክርስቲያናዊ ምግባርን ያመለክታል፡፡ ብርሃን ለራሱ በርቶ ለሌሎችም እንዲያበራ ክርስቲያናዊ ምግባርም ከራስ ተርፎ ለሰዎች ዅሉ ደምቆ በአርአያነት ይታያልና፡፡ እኛም ‹‹ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ የጽድቅ ሥራ የማይገኝበት ጊዜ የጨለማ ዘመን ከመምጣቱ በፊት የጽድቅ ሥራ መሥራት በምንችልበት ጊዜ ዅሉ በመልካም ምግባር ጸንተን እንኑር (ዮሐ. ፲፪፥፴፭-፴፮፤ ፩ኛ ዮሐ. ፩፥፯)፡፡

ደግሞም መልካም ግብር ያላቸው ምእመናን በብርሃን ይመሰላሉ፤ ብርሃን በግልጽ ለሰዉ ዅሉ እንደሚታይና እንደሚያበራ መልካም ምግባር ያላቸው ምእመናንም በጽድቅ ሥራቸው ለብዙዎች አርአያ፣ ምሳሌ ይኾናሉና፡፡ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል (ማቴ. ፭፥፲፬)፡፡ እንግዲህ ዅላችንም በጨለማ ከሚመሰለው ኀጢአት ወጥተን በብርሃን ወደሚመሰለው የጽድቅ ሕይወት ተመልሰን በክርስቲያናዊ ምግባር በርተን እኛ በርተን ወይም ጸድቀን ለሌሎችም ብርሃን ማለትም የጽድቅ ምክንያት ልንኾን ይገባናል፡፡ ‹‹ብርሃናችሁ በሰዉ ዅሉ ፊት ይብራ›› ተብለን ታዝዘናልና (ማቴ. ፭፥፲፮)፡፡

በአጠቃላይ ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን፣ መዓልት የሚባለው ክፍለ ክረምት ‹‹ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንደሚባለው ክረምቱ እየቀለለ፣ ማዕበሉ እየቀነሰ፣ ዝናሙ እያባራ፣ ሰማዩ እየጠራ የሚሔድበት የንጋት፣ የወጋገን፣ የብርሃን ጊዜ ነው፡፡ ልክ እንደ ዘመኑ እኛም እንደ ደመና በልባችን የቋጠርነውን ቂምና በቀል፤ እንደ ጨለማ በአእምሯችን የሣልነውን ክፋትና ኑፋቄ ወይም ክህደት፤ እንደ ዝናምና ማዕበል በወገን ላይ ያደረስነውን ጥፋትና በደል በንስሐ ፀሐይ አስወግደን ወደ ብርሃኑ ሕገ እግዚአብሔር፤ ወደ ብርሃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ወደ ብርሃኑ ምግባረ ሠናይ፤ ወደ ብርሃኑ ክርስትና እንመለስ፡፡ እንዲህ እንድናደርግም ልዑል እግዚአብሔር ‹‹በሕይወታችሁ ውስጥ ብርሃን ይኹን!›› ይበለን፡፡ እርሱ ‹‹ብርሃን ይኹን›› ካለ የኀጢአት ጨለማ በእኛ ላይ ለመሠልጠን የሚችልበት ዓቅም አያገኝምና፡፡

ይቆየን