ዕረፍቱ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ

 

እስራኤላውን በግብፅ ባርነት በተገዙበት ዘመን ፈርዖን እስራኤላውያን ወንድ ልጅ ሲወልዱ እንዲገደል በአዋጅ አስነገረ፡፡ የሙሴም እናት ልጇ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት እንዳይገደልባት ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ፍራቻ ልጇን በቅርጫት አድርጋ ወንዝ ውስጥ ጣለችው፡፡ ተርሙት የምትባለው የፈርዖን ሴት ልጅ በወንዝ ገላዋን ልትታጠብ ወርዳ ሳለ በዚያ ቅርጫት አግኝታ ብትከፍተው የሚያሳሳ ውብ ልጅ አገኘት፡፡ ‹‹ይህንንስ አሳድገዋለሁ›› ብላ ወደ ቤቷ ከወሰደችው በኋላ ሙሴ በንጉሡ በፈርዖን ቤት አደገ፡፡ የሙሴም እናት ተንከባካቢ ሞግዚቱ ሆና ተጥሎ የተገኘውን ልጇን እንድታሳድግ ከፈርዖን ሴት ልጅ ጋር በድብቅ በመስማማት በንጉሡ ቤት ገባች፡፡ እናቱም ልጇን ሙሴ የፈርዖን ልጅ እንዳይባል ሃይማኖቱን፣ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ባሕሉን ጠንቅቃ እያስተማረች አሳደገችው፡፡

ሙሴ ፵ ዓመት በሆነው ጊዜ አንዱ ግብፃዊ ዕብራዊውን ሲገድለው አይቶት ለወገኑ ተበቅሎ ግብፃዊውን ገደለው፡፡ በማግስቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በእርሳቸው ሲጣሉ አያቸው፡፡ ሊያስታርቃቸው ፈልጎ ወደ እነርሱ ጠጋ ቢል አንደኛው ዐመፀኛ ዕብራዊ ‹‹ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው ልትገድለን ትሻለህን?›› አለው፡፡ ሙሴም ‹‹በድብቅ አደረኩት ያልኩት ለካ ታውቆብኛል›› ብሎ ፈርዖንን ፈርቶ ወደ ምድያም ሀገር ሸሽቶ ሄደ፡፡ የምድያም ሀገር ካህን የሆነውን የዮቶርን (በሌላ ስሙ ራጉኤል ይባላል) ሴት ልጁን ሲፓራን አግብቶ ፵ ዓመት በምድያም ሲቀመጥ ሁለት ልጆችንም ወለደ፡፡ ይህችውም ምድያም የተባለች ሀገር ቅድስት ኢትዮጵያ ናት፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ፈርዖንም ሙሴ ግብፃዊውን እንደገደለው በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ፡፡ ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፤ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ፡፡ ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፤ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ፡፡ እረኞችም መጥተው ገፏቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፤ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው፡፡ ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ ‹ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፤ ደግሞም ቀዳልን፤ በጎቻችንንም አጠጣ› አሉ፡፡ ልጆቹንም ‹እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ› አላቸው፡፡ ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው፡፡›› (ዘፀ. ፪፥፩-፳፭)

‹‹ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ፡፡ እነርሱም ‹በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፣ እግዚአብሔርም ሰማ፡፡ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ፡፡ እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ‹ሦስታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን ውጡ› ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ፡፡ እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፣ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፤ ሁለቱም ወጡ፡፡ እርሱም ‹ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፣ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፣ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፡፡ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፤ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም?› አለ፡፡ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ፡፡ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም ማርያም ለምጻም ሆነች፣ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር፡፡ አሮንም ሙሴን ‹ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን›› አለው፡፡ (ዘኁ. ፲፥፩-፲፪)

ሕዝበ እስራኤል ከግብፅ ሳይወጡ በኋለኛውም ዘመን ጌታችን ኢየሱስ መድኃኒታችን ክርስቶስ ከመወለዱም ከብዙ ዘመን በፊት በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ካህን እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክረው ሐቅ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት የሚባለው ከበቂ በላይ ብዙ ምክንያትና ማስረጃ ኖሮ ነው እንጂ እንዲሁ አይደለም፡፡

ሙሴ በምድያም ሀገር በዱር ሆኖ የካህኑን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በቁጥቋጦ ውስጥ ታላቅ ራእይ አየ፡፡ ነበልባል ከሐመልማል ጋር ሐመልማልም ከነበልባል ጋር ተዋሕዶ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም ነበልባሉን ሳያጠፋው ተመልክቷል፡፡ ይህንንም ምሥጢር ለመረዳት ጠጋ ሲል ከቁጥቋጦው ውስጥ እግዚአብሔር ድምፅ አውጥቶ ጠራው፡፡ የቆመባት ስፍራ የተቀደሰች ስለሆነች ጫማውንም ከእግሩ እንዲያወልቅ ነገረው፡፡ (ዘጸ. ፫፥፭፣ ሐዋ. ፯፥፴-፴፬)፡፡ ለጊዜው ሐመልማል የእስራኤል፣ ነበልባሉ ደግሞ የመከራቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐመልማሉ ነበልባሉን ያለመጥፋቱ እስራኤልም መከራውን ግብር ገብተን ቀኖና ይዘን እናርቀው ያለማለታቸው ምሳሌ ሲሆን ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ማየቱ የግብጽ መከራ እስራኤልን ጨርሶ ያለማጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ ፍጻሜው ግን ሙሴ ያየው የነበልባልና የሐመልማል ተዋሕዶ የመለኮትና የትስብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው፡፡ ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ መለኮት ምልአቱን ስፋቱን ርቀቱን ሳይተው ሥጋም ግዙፍነቱን ሳይተው የመዋሐዳቸው አንድ አካል አንድ ባሕርይ የመሆናቸው ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም ነበልባሉ የጌታችን ምሳሌ ሲሆን ሐመልማሉ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ ይኸውም ነበልባሉ ሐመልማሉን እንዳላቃጠለው ሁሉ እሳተ መለኮት ጌታችንም ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ባደረ ጊዜ እመቤታችንን ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትም፤ ሐመልማሉም ነበልባሉን እንዳላጠፋው ሁሉ ጌታችንም ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ቢሆንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠም፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ምስጋናው ላይ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡- ‹‹መለወጥ የሌለባት ድንግል ማርያም ሙሴ በበረሐ በነደ እሳት ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ያያት ዕፅን ትመስላለች፣ የአብ ቃል በእርሷ ሰው ሆኗልና እሳተ መለኮቱ አላቃጠላትምና፤ ከወለደችው በኋላ ድንግልንናዋ አልተለወጠምና፤ ሰውም ቢሆን መለኮቱ አልተለወጠም በእውነት አምላክ ነውና፣ በእውነት አምላክ የሆነ እርሱ መጥቶ አዳነን፡፡›› የደማስቆው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ዕፀ ጳጦስ የአምላክ እናት አምሳል ነበረች፤ ሙሴ ወደ እርሷ በተጠጋ ጊዜ እግዚአብሔር ‹አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ› አለው፡፡ እንግዲህ ሙሴ የወላዲተ አምላክን ምሳሌ ያየባት መሬት የተቀደሰች ከሆነች ምሳሌዋ ራሷ ምን ያህል የተቀደሰች ትሆን? እርሷ ቅድስት ብቻ ሳትሆን ቅድስተ ቅዱሳን ናት›› በማለት ስለ እመቤታችን አስተምሯል፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዲያወጣቸው ላከው፡፡

ሙሴም ወደ ግብፅ ሀገር ሄዶ ፲ የተለያዩ መቅሠፍቶች አመጣ፡፡ መጀመሪያ ውኃውን ወደ ደምንት ለወጠው፡ ፲ኛው የበኩር ልጆቻቸው ሞቱ፡፡ በተአምራቱም ሕዝቡን ይዞ ከግብፅ ወጣ፡፡ የኤርትራን ባሕር በበትሩ ለሁለት ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ሕዝበ እስራኤልን በምድረ በዳ ፵ ዓመት ሙሉ መና ከሰማይ እያወረደ መገባቸው፣ ከአለትም ላይ ውኃ እያፈለቀ አጠጣቸው፡፡ እራኤል ግን እጅግ ክፉዎች ነበሩና በክፋ ይነሱበት ነበር፡፡ በድንጋይ ሊወግሩት ያሉበት ጊዜም ነበር፡፡ እርሱ ግን ፍጹም በመታገስ በኃጢአታቸው እንዳይሞቱ ወደ እግዚአብሔር ይማልድላቸው ነበር፡፡ ሙሴ ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር ከእግዚአብሐር ጋር ፭፻፸ ጊዜ ቃል በቃል ተነጋግሯል፡፡ ፵ ቀን ፵ ሌሊት ከጾመ በኋላ ዓሥሩን ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላት ተቀበለ፡፡ እስራኤላውያን ባዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስኪሸፍንላቸው ድረስ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚያበራበት ጊዜም ነበር፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ፻፳ ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ እንዲያስረክበው ስላዘዘው ለኢያሱ አስረክቦታል፡፡ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ካዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ ዐረፈ፡፡ በዚያም በመልእክት እጅ በሥውር ተቀበረ፡፡ የእስራኤል ልጆችም ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሰወረ፡፡ ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላቸው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ ላይ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገሠጸው፣ ከዚህም ሥራ ከለከለው፡፡ የእስራኤልም ልጆች ለሙሴ ፵ ቀን አልቅሰውለታል፡፡ ጌታችን ስለ ሙሴ ሲናገር ከእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን ነቢይ እንደማይነሣ መስክሮለታል፡፡ ዕረፍቱም መስከረም ፱ ነው፡፡

የሊቀ ነቢያት ሙሴን ረድኤትና በረከቱን ያሳድርብን፤ እግዚአብሔር አምላክ በጸሎቱም ይማረን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ የመስከረም ወር ስንክሳር፣ ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ