ዕለተ ዓርብ በሰሙነ ሕማማት

ካለፈው የቀጠለ…

ሚያዚያ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

፭. ዕለተ ዓርብ ነግህ

ዕለተ ዓርብ አዳምን ከሰይጣን ባርነት ነፃ ለማውጣትና የእርሱን የበደል ዕዳ ለመክፈል አምላካችን መከራ መስቀሉን የተሸከመበት ዕለት፣ የኀዘን ዕለት፣ የድኅነትም ዕለት ነው፡፡ ዓርብ ማለት ዐረበ ገባ (ተካተተ) ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም መካተቻ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረቱን ከእሑድ ጀምሮ በስድስተኛው ቀን ዓርብ አዳምን በመፍጠር ሥራውን ሁሉ አጠናቋልና (አካቷልና)፡፡ በኋላም በኦሪት ሕዝበ እስራኤል ከሰማይ የሚወርድላቸውን መና በሙሴ ትእዛዝ መሠረት ዓርብ ዕለት የቅዳሜን ጨምረው (ቅዳሜ ሰንበት ስለሆነ እህል መሰብሰብ ስለማይገባ) አካተው ይሰበስቡ ነበር፡፡  (ዘፀ.፲፮፥፬)

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት»  እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም የዓለም ሁሉ መድኃኒት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበትና የሰው ልጅ ድኅነት የተፈጸመበት (የተካተተበት) በመሆኑ (ዓርብ) ተብሏል፡፡  (፩ቆሮ.፩፥፲፰፣ማቴ.፳፯፥፴፭-፸፭)

ዓርብ ጠዋት ጎህ ሲቀድ አይሁድ ጌታችንን በጲላጦስ ፊት አቀረቡት፡፡ ጲላጦስም ወደነርሱ መጥቶ ‹‹የዚህ ሰው በደሉ  ምንድነው?››  አላቸው፤ የካህናት አለቆቹም ‹‹ክፉ አድራጊ ባይሆን ወዳንተ እናመጣዋለን? ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል፤ ለቄሳር አልገዛም ይላል፤ የሰንበትን ቀን ይሽራል….›› በማለት የተለያዩ ክሶች አቀረበቡት፡፡ ጲላጦስም ‹‹እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት›› አላቸው እነርሱም ‹‹እኛ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም›› አሉት፡፡  ጲላጦስም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊጠይቀው፣ ሊመረምረው ወደውስጥ አስገባው፡፡ ያንጊዜም ጲላጦስ ‹‹የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹ይህን የምትናገር ከራስህ ነውን ወይስ ስለእኔ የነገረህ ሌላ አለን›› ብሎ መለሰለት፤ ጲላጦስም ‹‹እንዲያ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህ›› አለው፤ ጌታችንም ‹‹እኔ ንጉሥ እንደሆንኩ አንተ ራስህ ትላለህ›› አለው ጲላጦስም ምንም ያገኘበት በደል የለም፡፡ ወደ ውጭም ወጥቶ ይህን ሰው በምትከሱበት ገንዘብ በደል አላገኘሁበትም፤ ነገር ግን በየዓመቱ በየፋሲካ በዓል ከእስረኞች አንድ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ እንግዲህ የአይሁድን ንጉሥ ልፈታላችሁ ትወዳላችሁን?›› አላቸው፡፡ እነርሱም በአንድ ድምጽ ከፍ አድርገው ‹‹በርባንን እንጂ ይህን አይደለም›› አሉ፡፡ በርባን ግን ወንበዴ ነበር፡፡  አይሁድም ‹‹ሕግ አለን እንደ ሕጋችን ይሞት ዘንድ ይገባል፤ ራሱን የእግዚብሔር ልጅ አድርጓልና›› አሉት፡፡ ጲላጦስም ሊያስተዋቸው እንዳልተቻለው ባየ ጊዜ አውጥቶ ገረፈው፤ ምክንያቱም በሀገራቸው የሚሰቀል አይገረፍም፤ የሚገረፍም፤ አይሰቀልም፤ ስለዚህ እንዳይሰቅሉት ራርተው ይለቁታል ብሎ ነው፡፡ ነገር ግን  ‹‹መጠውኩ ዘባንየ ለቅሥፈት›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ እንደዚሁም ዲያብሎስ የአዳምን ዘባነ ልቡና እየገረፈ ገሃነም አውርዶት ነበርና ለእርሱ ካሣ ሊሆን እንደመጣ ለማጠየቅ ጀርባውን ተገረፈ፡፡ (ዮሐ.፲፰፥፳፰-፴፩)

ጲላጦስም ‹‹እነሆ ንጉሣችሁን ልስቀለውን?›› አላቸው፤ እነርሱም ‹‹ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም፤ ስቀለው፤ ስቀለው›› አሉ፡፡ ይህንን ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲተረጉሙት ‹‹ልደቱ ከዳዊት ዘር እንደሆነ ሲያመለክታቸው በመንግሥትም ደም በማስፈራራት ያስጥለው ዘንድ ነው፤ እነርሱ ግን እርሱን ለመግደል ጨከኑ፤ ከቄሳር በቀር ንጉሥ የለንም ብለው የዳዊትን ዘር መንግሥት ካዱ›› ብለውታል፡፡ ዳግመኛም አይሁድ በሕዝቡ መሐል እየተሽሎኮሎኩ ‹‹በርባንን ፍታልን፤ ክርስቶስን ስቀልልን›› በሉ እያሉ ሕዝቡን አሳመፁ፡፡ ጲላጦስም የሚረባና የሚጠቅም ነገር እንደሌለ ባየ ጊዜ ውኃ አምጡልኝ ብሎ ‹‹እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ራሳችሁ ዕወቁ›› ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ፡፡ ሕዝቡም መልሰው ‹‹ደሙ በእኛና በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን›› አሉ፡፡  ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ልጆቻቸው ደም ጨብጠው የሚወለዱ ሆነዋል፡፡ (መጽሐፈ ምሥጢር- ምዕራፍ ፩፥፬)

  የጌታችን ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

በሰሙነ ሕማማት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀሉን ስናስብ የምናስባቸው መከራዎቹ ወይም ሕማማቱ ዐሥራ ሦስት ሲሆኑ እነርሱም ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል  ማወቅና በየጊዜው ማሰብ ስለሚገባን ከዚህ በታች በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡

፩. አክሊለ ሦክ (የእሾህ አክሊል መድፋት)

አይሁድ የእሾህ አክሊል በጌታችን ራስ ላይ ያደረጉበት አነገሥንህ ብለው ሲሳለቁበትና ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ‹‹ወወደዩ ጌራ መድኃኒት ዲበ ርእሱ በአክሊል ዘአስተቀጸለቶ እሙ፤ እናቱ ያቀዳጀችውን የመድኃኒት አክሊል በራሱ ላይ አደረጉለት፤ የእሾህ አክሊል ጎንጒነው በራሱ ላይ አቀዳጁት›› እንዲል፡፡ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ጌታ አጥንቱ እንዳልተሰበረ ልናስተውል ይገባል፡፡ ወአስተአኃዝዎ ኅለተ ውስተ የማኑ፤ በቀኝ እጁ ዘንግ አስያዙት፤ በፊቱም ተንበርክከው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን›› እያሉ ተዘባበቱበት፡፡ በላዩም ላይ ተፉበት፤ ዘንጉንም ነጥቀው ራሱን መቱት፡፡››  በቀኝ እጁ ዘንግ ያስያዙት አነገሥንህ ብለውታልና በፍና ተሳልቆ (የመቀለድ) ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ኃጢአታችንን በፍዳ ታጽፍብናለህ ሲያሰኝባቸው ነው፡፡ ከዚያም ‹‹ከተዘባበቱበት በኋላ ቀዩን ልብስ ገፍፈው ልብሱን አለበሱት›› በእርሱም መገፈፍ ለአዳም የጸጋ ልጅነትን አለበሰው፡፡  (ድርሳነ መድኃኔ ዓለም፣ ማቴ.፳፯፥፳፱-፴፩)

፪.     ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዘንግ መመታት)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ ስለመመታቱና ስለ መቀጥቀጡም የሚገልጥ ሲሆን ቃሉም ‹‹ኰርዐ መታ›› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥምር ቃሉ (ተኰርዖተ ርእስ)  ትርጕም ደግሞ ራስን  መመታት ማለት ነው፡፡ ሀገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህንንም ያደረገው በአይሁድ ሕግ የተገረፈ ስለማይሰቀል፣ የሚሰቀል ደግሞ ስለማይገረፍም ነበር፡፡ እኔ ከገረፍኩት አይሰቅሉትም ብሎ ስለአሰበ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ጲላጦስ ከገረፈው በኋላ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስድስት ግርፋትን በመግረፍ የግፍ ግፍ ፈጽመውበታል፡፡ (ማቴ.፳፯፥፳፬፣ ማር.፲፭፥፲፭፣ ሉቃ.፳፫፥፳፭፣ ዮሐ.፲፰፥፴፱)

፫.   ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)

ተፀፍዖ መልታሕት ፊትን በጥፊ መመታት ማለት ሲሆን ይህም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደምና በበደል በረከሰ የአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ጌታችን በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ፊት እውነትን መናገሩ እንደ ስድብ ተቆጥሮበት ፊቱን በጨርቅ ሸፍነው አብዝተው በጥፊ መትተውታል፡፡ ደግሞም ‹‹ክርስቶስ ሆይ በጥፊ የመታህ ማነው? ተናገርልን›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡ በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል እርሱ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ፡፡ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩም ሞት የሌለበት ዘለዓለማዊ አምላክ ሲሆን ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን›› በማለት እየተሳለቁ በጥፊ ፊቱን ጸፉት፡፡ (ማቴ.፳፯፥፳፯፣ ዮሐ.፲፱፥፪-፬)

፬.     ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መትፋት)

ምራቅን በሰው ላይ ቀርቶ በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ነውርና ውርደትም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የባሕርይ አምላክ በሆነው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ላይ መትፋት ለመግለጽ ከቃላት በላይ ነው፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደተነገረ ርኩሳን አይሁድ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ላይ እየዘበቱበት ምራቃቸውን መትፋታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ እርሱ ንጹሐ ባሕርይ ሆኖ ሳለ ስለ እኛ ድኅነት ሲል ምራቅ ተተፋበት፡፡ በእርሱም መዋረድ በኃጢአት የቆሸሸውን የእኛን ሰውነት ከርኵሰት አነጻልን፡፡ እርሱ የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ያጠፋልን ዘንድ በነውረኞች አይሁድ ነውር የሆነው ምራቅ ተተፋበት፡፡ (ኢሳ.፶፥፮፣ማር.፲፭፥፲፱)

፭.     ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞት መጠጣት)

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፣ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ›› በማለት አስቀድሞ በመንፈሰ ትንቢት እንደተናገረ የትንቢቱ ቃል ይፈጸም ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ አይሁድ መራራ ሐሞት እንዳጠጡት የሚገልጥ ነው፡፡ ጌታችንም ቀምሶ ሊጠጣው አልወደደም፤  ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወትን ውኃ ምንጭ የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም፡፡ ዐርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ያጠጣቸውን ክርስቶስን የዝናማት፤ የባሕርንና የውቅያኖስን ጌታ በተጠማ ጊዜ ቀዝቃዛ ውኃ ከለከሉት፡፡ (መዝ.፷፰፥፳፩፣ማቴ.፳፯፥፴፬፣ ኢሳ.፶፭፥፩፣ ዘዳ.፲፮፥፩-፳፤፩ቆሮ.፲፥፫)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውኃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ፣ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ሁሉ ለማዳን መራራውን ቀመሰ፤ ሆምጣጤውንም በሰፍነግ ሞልተው ሰጡት፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ መራራ ሐሞትን ጠጣ፡፡

፮.     ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)

በነቢዩ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› ተብሎ እንደተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ በመንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ሲጠቀጠቅ በእሳት አለንጋም ሲገረፍም የነበረውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠርም ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት  ግርፋትን ተገረፈ፡፡ አይሁድ ሀገረ ገዥያቸው ጲላጦስ አንድ ሰው ይፈታላቸው ዘንድ ላቀረበላቸው ምርጫ እንዲፈታላቸው የመረጡት ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን በደል የሌበትን ንጹሑን ክርስቶስ ሳይሆን ወንበዴው በርባንን ነበር፡፡ (ኢሳ.፶፥፮፣ማቴ.፳፯፥፳፰፣ማር.፲፭፥፲፭፣ዮሐ.፲፱፥፩)

፯.    ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)

ይህ መከራ ሰማይን በከዋክብት ምድርን በአበቦች የሚያስጌጥ፣ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትንም ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላካችን እግዚአብሔር ወልድ ከልብስ መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ እርሱ ለተራቆቱት ጸጋን የሚያለብስ አምላክ ሆኖ ሳለ ልብሱን ተገፍፎ በመስቀል ላይ ራቁቱን ቆመ፡፡ በጨለማ ውስጥ ለሚኖረው የሰው ልጅ ብርሃንን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡ (ማቴ.፳፯፥፳፯)

፰.    ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)

ይህ መከራ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ወንጀለኛ ሁለት እጆቹን ወደኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ነው፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜው በደረሰ ሰዓት ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለትና ሰዓት የአይሁድም ጭፍሮች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል፡፡ በኃጢአት ሰንሰለት ታሥሮ በጠላት ዲያብሎስ ግዛት በባርነት የኖረውን የሰውን ልጅ ከኃጢአት እሥራት ይፈታ ዘንድ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡ (ዮሐ.፲፰፥፲፪)

፱.     ርግዘተ ገቦ (ጎንን መወጋት)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በጦር የመወጋቱን መከራ የሚገልጥ ነው፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አጠገብ፣ በግራና በቀኙ የተሰቅሉትን ሁለቱ ወንበዴዎች ጭን ጭናቸውን ከሰበሩ በኋላ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ፈጽሞ እንደሞተ አዩት፤ ያን ጊዜም ከጭፍሮቹ አንዱ ለንጊኖስ የተባለ ወታደር ጎኑን በጦር ስለወጋው ወዲያው ከጎኑ ደምና ውኃ ፈሰሰ፡፡ የሞት መውጊያ በሆነው ኃጢአት የሞተውን የሰው ልጅን ለማዳን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውንም ኃጢአት ከሥሩ ነቅሎ ስለጣለው ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ?›› ተብሎ ተነገረ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት ነበርና፡፡ በዚህም መሠረት የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ እንዳይኖር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፡፡ በእርሱም ሞት በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር የተለየንበት ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፴፫፣፩ቆሮ.፲፭፥፶፬-፶፭)

፲.     አምስቱ ቅንዋተ መስቀል

አምሥቱ ቅንዋተ መስቀል የሚባሉት መድኃኒታችን በዕፀ መስቀል ላይ ሲሰቀል የተቸነከረባቸውን የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ሲሆን እነርሱም  ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራና ሮዳስ ይባላሉ፡፡ እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መሆናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡ ሐዋርያው ቶማስ ከትንሣኤ በኋላ ወንድሞቹ ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው በነገሩት ጊዜ በእጁ ላይ ያለውን የችንካሩን ምልክት በዓይኖቼ ካላየሁ አላምንም ሲል መድኃኒታችን ክርስቶስ ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን›› አለው፤ ‹‹ቶማስም መልሶ ጌታዬ አምላኬ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ይሁን እንጂ ቶማስ የተቸነከሩትን እጆቹን የተወጋውንም ጎኑን ካላየሁ በማለት መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ በእጆቹ ለመዳሰስ ሲሞክር እጆቹ እሳት እንደገባ ጅማት ተኮማትረዋል፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፯)

በክርስቶስ ስቅለት ጊዜ በሰማይና በምድር ላይ የተደረጉ ተአምራት

ሀ. በሰማይ፡- ፀሐይ ጨለመች፤ ጨረቃ ደም ለበሰች፤ ከዋክብትም ረገፉ፡፡ በትንቢት  ‹‹በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር ይገባል›› ተብሎ አስቀድሞ እንደተነገረ ጌታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ድረስ ምድር ጨልማለች፤ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትም የፈጣሪያቸውን ዕርቃን ይሸፍኑ ዘንድ ብርሃናቸውን ከልክለዋል፡፡  ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይህንን አስመልክቶ ሲናገር ‹‹ፀሐይ ጸልመ ወወርኀ ደመ ኮነ ወከዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ፤ ፀሐይ ጨለመ፤ ጨረቃ ደም ሆነ፤ ከዋክብት ፈጥነው ወደቁ፤ ብርሃን ያጎናጸፋቸውን የጌታን ዕርቃን እንዳያዩ›› ብሏል፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም እንደዚሁ ‹‹ጎየ ፀሐይ ወጸልመ ወርኅ ወከዋክብትኒ ተኀብኡ ከመ ኢያብርሁ፤ ፀሐይ ሸሸ፤ ጨረቃም ጨለመ፤ ከዋክብትም እንዳያበሩ ተሠወሩ›› ብሏል፡፡ (አሞ.፰፥፱፣ ማቴ.፳፮፥፵፭፣ ሃይማኖተ አበው ፳፮፥፲፩-፳፩)

ለ. በምድር ላይ፡- የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከሁለት ተቀደደ፤ አለቶች ተሰነጠቁ፤ መቃብራት ተከፈቱ፤ ሙታን ተነሡ፤ ይህን ጊዜ ፈያታዊ ዘየማን ወደ ጌታችን ዘወር ብሎ ‹‹አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› አለው፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹አንተ ትቀድሞ ለአዳም በዊአ ውስተ ገነት፤ አንተ ገነት በመግባት አዳምን ትቀድመዋለህ›› አለው፡፡ (ማቴ.፳፯፥፵፭-፷፬)

 

‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ›› (ማር.፲፭፥፴፬)

ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ›› (አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ) ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹ኤልያስን ይጠራል›› እያሉ ያወሩበት ነበር፡፡ ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ በዚያ የነበሩ እገሌን (ኤልያስን) ይጣራል እያሉ እንዳሙትና ክሕደትን እንደተናገሩ ዛሬም ከአይሁድ ያልተሻሉ ነቢይ ስለሆነ ነው፤ ፈርቶ ነው፤ ወደ አብ እየጸለየ ነው የሚሉ አሉና ይህን ለምን እንደተናገረ እንመልከት፡፡

ሀ. ለአቅርቦተ ሰይጣን፡- ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ሰባቱን ድንቅ ተአምራት ሲያደርግ ዲያብሎስ አሰፍስፎ ይጠብቅ ነበርና ወደኋላ ሸሸ፤ እንዲህም አለ ‹‹ኢሳይያስን በምናሴ ላይ አድሬ በመጋዝ ሳስተረትር፤ በአይሁድ ላይ አድሬ ኤርምያስን በድንጋይ ሳስወግር እንዲህ ያለ ተአምር አላየሁም፤ ይህ በእውነት የእግዚብሔር ልጅ ነው›› ብሎ ወደኋላ መሸሽ ሲጀምር ጌታችን ለአቅርቦተ ሰይጣን (ሰይጣንን ለማቅረብ) ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይህን ጊዜ ዲያብሎስ ‹‹ለካስ ፍጡር ነው፤ እንዴ ዛሬ ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል አኖራለሁ›› ብሎ ደፋር ነውና ነፍሱን ከሥጋው እለያለሁ ብሎ ቢቀርብ ጌታችን ‹‹ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ›› እንዲሉ በነፋስ አውታር በእሳት ዛንጀር ወጥሮ ዋይ ዋይ እያለ ወደ ጥልቁ ጥሎታል፡፡ ስለምን ሰይጣንን ማቅረብ ፈለገ ብንል ቀድሞ ሰይጣን አዳምና ሔዋንን በወሬ ደልሎ ወደራሱ አቅርቦ ድል እንደነሳቸው ጌታም ድል በተነሳችሁበት ድል ልንሳላችሁ ሲል አቅርቦ ቀጥቶታል፡፡ (ማቴ. ፳፯፥፵፮-፶)

ለ. ፍጹም ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ፡- መለመን መጸለይ ለሥጋ እንጂ ለመለኮት የሚስማማው ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሥጋን በመዋሐዱ ጸለየ ተባለለት፡፡ ስለዚህ መለኮት ሥጋን ተዋሕዷልና የሥጋንም ባሕርይ ገንዘብ እንዳደረገ፤ ፍጹም ሰው እንደሆነ ለማጠየቅ ለምኗል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ አጠቃላይ የጌታን መከራ መስቀል ለምን እንደሆነ ሲናገር ‹‹መከራ መስቀልን ተቀበለ፤ በመለኮት ሕያው ሆኖ ሳለ ዕራቁቱን ሰቅለው ዘበቱበት፤ ሕይወት እንደምን ሞተ ይባላል? ሰው መሆኑን ያስረዳንና ዳግመኛም ያስነሣው ዘንድ በሥጋው ሞተ›› (ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ፸፪፥፳፫)

ሐ.. አርአያ አብነት ለመሆን፡- እናንተም እንደኔ መከራ በደረሰባችሁ ጊዜ ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› በሉ ሲለን ነው፡፡ ጌታችን መምህረ ትሕትና እንደሆነ ሁሉ መምህረ ትዕግሥትም ነው፤ ለእኛ ያስተማረን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ነውና በፈተና ውስጥ ሳለን አምላካችን ለምን ራቅከን እጅህን ስደድልን፤ ኃይልህን ስጠን እያልን መለመን እንደሚገባን ለማስተማር ነው፡፡

ይቆየን