ዐውደ ርእዩ በአሜሪካ ቀረበ

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ፭ኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ ከሰኔ ፲ – ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በአሜሪካ አገር መቅረቡን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ፡፡

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት

በአትላንታ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት በአትላንታ ከተማ በደብል ትሪ ሆቴል በቀረበው በዚህ ልዩ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የየአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እና የመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት፣ ታዳጊ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ምእመናን መታደማቸውን የንዑስ ማእከሉንና የዝግጅት ኰሚቴውን ሪፖርት ጠቅሶ ማእከሉ ዘግቧል፡፡

ዐውደ ርእዩ በአባቶች ቡራኬ ሲጀመር

በመኪና ከአራት እስከ ዐሥር ሰዓታት ከሚወስዱ ክፍለ ግዛቶች (ስቴቶች) ጭምር ዐውደ ርእዩን ለመመልከት በአትላንታ ከተማ የተገኙ ምእመናን እንደ ነበሩም ከዝግጅት ኰሚቴው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የተመልካቾች ቍጥር ከመብዛቱ የተነሣ ዐውደ ርእዩ በሁለት ክፍሎች የቀረበ ሲኾን፣ ትዕይንቶቹም በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተተረጐሙ ተመልካቾች በሚረዱት መልኩ ተብራርተዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ሲቀርብ

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል በተከፈተበት ዕለት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ቀርቧል፡፡

በመልእክታቸው እንደ ተጠቀሰው የዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጕመው እንዲቀርቡ መደረጋቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መኾኑን ብፁዕነታቸው አድንቀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በስፋት ለማዳረስ ይቻል ዘንድ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሌሎች ከተሞችም እንዲከናወን ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው አገልግሎቱን ሀገረ ስብከታቸው እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ታዳሚ አባቶች እና ምእመናን በከፊል

በዐውደ ርእዩ ከተሰሙ መልካም ዜናዎች አንዱ አንድ መቶ ሦስት የአብነት ተማሪዎችን በአንድ ለአንድ የድጋፍ ዘዴ ለመርዳትና ለማስተማር የሚያስችል ቃል መገባቱ ሲኾን፣ በቍጥር ከአራት እስከ ዐሥር የሚደርሱ የአብነት ተማሪዎችን በግል ወጫቸው ለማስተማር አንዳንድ ምእመናን ቃል ገብተዋል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ለጎንደር በአታ የቅኔ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል $2,628 (ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሃያ ስምንት ዶላር) ምእመናን ለግሰዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ተሳታፊ ምእመናን በከፊል

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ዕለት መልእክት ያስተላለፉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዐውደ ርእዩ አስተማሪ እንደ ነበር አስታውሰው በዚህም ይህን ሠራን ብሎ መታበይ እንደማያስፈልግ እና ስለ ሥራው ዅሉ እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ እንደ ኾነ አስተምረዋል፡፡

የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ ማንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ዕርገተ ቃል ‹‹አሁን ታሪክ ተቀይሯል፡፡ የአገልግሎቱ በር ተከፍቷል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ በአትላንታ ሰፋፊ ራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከሕዝቡ ጥያቄና አስተያየት የተረዳነውም ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ በርቱ›› በማለት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

‹‹ለዚህ ዅሉ ሥራ መሳካት ምክንያቱ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለ ኾነ ነው›› ያሉት የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ ያዕቆብ በበኩላቸው፣ ንዑስ ማእከሉ በዚህ ሥራ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች መንፈሳውያን ተግባራትንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በዝግጅቱ የቤተ ክርስቲያንን አስተዋጽዖ፣ ፈተናዎችንና የምእመናንን ድርሻ በስፋት እንደ ተረዱበት እና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የዅሉም ምእመናን ጉዳይ መኾኑን እንደ ተገነዘቡበት የዐውደ ርእዩ ጐብኝዎች በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በመጨረሻም ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት ትብብርና እገዛ ላደረጉ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ማኅበረ ካህናት፤ ለየሰንበት ት/ቤቶች አባላት፤ ድጋፍ በመስጠት (ስፖንሰር በማድረግ) ለተባበሩ የግል ድርጅቶች እና ለልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) አካላት የዐውደ ርእዩ አዘጋጅ ኰሚቴ ላቅ ያለ ምስጋናውን በማኅበረ ቅዱሳን ስም አቅርቧል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ከፊሉ

ዐውደ ርእዩ በሚቀጥለው ቅዳሜና እሑድ (ሰኔ ፲፯ እና ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም) በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ እንደሚቀርብ የአሜሪካ ማእከል አስታውቋል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ክውን ትዕይንቶች አንዱ (የአብነት ተማሪዎች በትምህርት ላይ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ ያዘጋጀው ፭ኛ ዙር ዐውደ ርእይ ከግንቦት ፲፯ – ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ቀርቦ በብዙ ሺሕ ሕዝብ እንደ ተጐበኘ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ዐውደ ርእይ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ማእከላት በየጊዜው እያዘጋጁ ትምህርቱ ለምእመናን እንዲዳረስ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በቅርቡም ከአገር ውስጥ ማእከላት መካከል ባሕር ዳር ማእከል ከግንቦት ፬ – ፲፫፤ ፍኖተ ሰላም ማእከል ከሰኔ ፰ – ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በቅደም ተከተል ዐውደ ርእዩን አዘጋጅተው ለብዙ ሺሕ ሕዝብ እንዳስጐበኙ ከማእከላቱ የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡