‹‹ወደ ዕረፍት አወጣኸን›› (መዝ.፷፭፥፲፪)

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
ሰኔ ፲፫፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አባቶቻችን እስራኤላውያን በግብፅ ሳሉ የደረሰባቸውን መከራና ሥቃይ በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት የተመለከተውን እና ያየውን ታሪክ ነቢዩ ዳዊት ግልጽ አድርጎ ጽፎልናል። ከእሳትና ከውኃ መካከል እንዳወጣቸው እንዲሁም ዕረፍትን እንዴት እንዳገኙ በዚሁ ክፍል ተመዝግቦ እናገኘዋለን።

ቃሉም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ ለስሙም ዘምሩ፤ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ፤ እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት ‹ሥራህ ግሩም ነው› ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶችህ ዋሹብህ፤ በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፤ ለአንተም ይዘምራሉ፤ ለስምህም ይዘምራሉ፤ ኑ የእግዚአብሔርን ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው፤ በባሕርም በየብስም አደረጋት፤ ወንዙንም በእግር ተሻገርን፤ በዚያም በእርሱ ደስ ይለናል፤ በኃይሉ ለዘለዓለም ይገዛል፤ ዓይንኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ፤ አመጸኞች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ፤ አሕዛብ ሆይ አምላካችንን ባርኩ፤ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ። ነፍሴ በሕይወት ይኖራል፤ እግሮቼንም ለመናወጽ አልሰጥም፤ አቤቱ ፈትነኸናልና። ብርሃንም እንደ ሚያነጥሩ አንጥረኸናልና፤ ወደ ወጥመድም አገባኸን፤ በጀርባችንም መከራ አኖርን፤ በራሳችን ሰው ላይም አስረገጥከን፤ በእሳት እና ውኃ መካከል አለፍን፤ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።›› (መዝ.፷፭፥፩-፲፪) ስለ ቃሉ አምላካችን እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን።

አበ ብዙኃን አብርሃም ከእነ ልጅ ልጆቹ፣ ያዕቆብም ሰባ ነፍሳትን ይዞ ወደ ግብፅ በረሐ እንደ ተሰደደ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የሰው ልጅ ለምን ይሰደዳል?! ብዙዎቻችን በተለያየ ምክንያት እንሰደዳለን። ስንሰደድ ግን ምን ለማግኘት ነው? ምንስ ገጥሞን ነው? ሰው በሚኖርበት ስፍራ መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙት ሊሰደድ ይችላል። እነዚህ መሠረታዊ የምንላቸው መብላት፣ መጠጣት፣ መልበስ፣ መኖርም ሊሆን ይችላል፤ እነዚህን ፍላጎት ሲያጣ የሰው ልጅ ይሰደዳል። ያዕቆብ ፸ ነፍሳትን ይዞ ለልጆቹ የሚያበላው እና የሚያጠጣው ባጣ ጊዜ ወደ ግብፅ ተሰድዷል፡፡ ሆኖም እርሱ ልጆቹን ይዞ በተሰደደ ጊዜ የሚፈልገውን መሠረታዊ ነገር በግብፅ ቢያገኝም የኅሊና ዕረፍትን ግን አጥቶ ነበር፡፡

ሰው የእግዚአብሔርን ማደሪያ ቦታ ለመፈለግም ሲል ሊሰደድ ይችላል። ወይም ደግሞ ጠላት ሲያሳድደው ሊሰደድ ይችላል። እናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕተ ንጹሐን እመ አምላክ ወለዲተ አምለክ ወደ ግብፅ እንደ ተሰደደቺው ማለት ነው፤ ጨካኙ ንጉሥ ፈርዖንን እና ሄሮድስን ሽሽት ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ሊገድለው ባሰበ ጊዜ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን የሦስት ዓመት ሳለ ይዛው ወደ ግብፅ ተሰድዳለች። ስደቷም ምክንያት አለው፤ የተበተኑትን ለመመለስ፣ የራቁትን ለማቅረብ እንድሁም ምጽዓተ ክርስቶስን ለማመልከት ነው፤ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተሰደደችው ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ነው።

ሕዝበ እስራኤል በግብፅ ምድር በባርነት ተይዘው ለ፬፻፴ ዓመት በሚኖሩበት ዘመን ቀን ያለ ዕረፍት ሌሊት ያለ እንቅልፍ ጭቃን እየረገጡ ወይም እያቦኩ የግብፅ ፒራሚዶችን ለመገንባት ብዙ ሥቃይ እና መከራን ዓይተዋል፡፡ የብዙዎች እናት የብዙዎችን የ፬፻፴ ዘመን ለቅሶን ያለቀሰች ራሔል ባሏ ሮቤል ሞቶባት በማኅፀኗ መንታ ልጆችን አርግዛ ሳለ በባሏ ስፍራ ኖራ እርገጪ ተብላ ስትረግጥ ልጆቿ ወጥተው ወደቁ፤ ደንግጣ ስትቆምም ‹‹የሰው ሥጋ ያጸናዋል እንጂ ምን ይለዋል፤ እርገጪው›› ብለው ልጆቿን አስረግጠዋታል፡፡ በፈርዖን አገዛዝ ሕዝበ እስራኤል ተጨንቀው በነበረበት ዘመን እናታችን ራሔል ጎንበስ ብላ አልቅሳ የያዘችውን እንባዋን በእጇ ይዛ ወደ ሰማይ ረጨቺው፡፡ (ማቴ.፪፥፲፰ አንድምታ ትርጓሜ) ይህም እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ለቅሶ እንዲሰማ አደረገው፡፡ በእንባ የተላከ ደብዳቤ መልስ ይዞ መጣ፡፡ እኛስ በእንባ አልቅሰን እናውቃለን? እንደ በርጠሚዎስ አልቅሰን ማረን! ይቅር ብለን! ብለን ለምነን እናውቃለን? እንደ ራሔል አልቅሰን እናውቃለን? የራሔል ደብዳቤ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ የደረሰው በለቅሶ የቀረበ ስለሆነ ነው፡፡

ይህም ደብዳቤ ያን ጊዜ በእግዚአብሔር ጥበብ፣ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእግዚአብሔር ጥባቆት ያደገው ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ፣ የወገኖቹን ሥቃይ፣ የወገኖቹን መከራ፣ ጭንቀት አላይም በማለት በ፵ ዓመቱ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር እና ወደ ብንያም ሀገር እንደ ሄደ እናውቃለን፤ እንረዳለን። ስለዚህም በሄደበት ቦታ በጎችን መጠበቅ ተለማመደ። ምክንያቱም ክርስቲያን በበግ ስለሚመሰል ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤…ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ ….ግልገሎቼን ጠብቅ ነው›› እንዳለው ሙሴም መጀመሪያ ሕዝበ እስራኤልን ለመጠበቅ፣ ከባርነት ለማውጣት የመጠበቅን ትምህርት መማር ነበረበት፤ (ዮሐ.፲፰፥፲፯-፳፯) ከአማቱ ከዮቶርም የተማረው ይህን ነበርና የሰው ልጅ እንዴት መጠበቅ እንዳለበትና የሚያስፈልገውን ነገር እንዴት ማዘጋጀት እንዳለበት የተማረው ከአማቱ ነው፡፡ (ዘፀ.፲፰፥፩-፳፯)

ለእያንዳንዳችን አባት ያስፈልገናልና፤ የቱንም ያህል ዕውቀት እና ጸጋ ቢኖረንም መምህረ ንስሓ አባት ከሌለን ባዶ ነን። ንስሓ አባት ያስፈልገናል፤ ካህን ያስፈልገናል። ሕዝበ እስራኤልም ከባርነት የወጡት በካህን ተመርተው ነው፤ መንገዱን የሚያሳየን የሚባርክልን፣ የሚቀድስልን እንዲሁም ችግራችንን የምናዋየውና ኃጢአታችንን የምንናዘዝለት አባት ያስፈልገናል፡፡ ስንቶቻችን የንስሓ አባት እንዳላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ! መሪ ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ ቤታችሁን ልትመሩ ትችላላችሁ፤ ቤታችሁን ልታስተዳድሩ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ይህ ምድራዊ ቤታችን ነው። ለሰማያዊ ቤታችን ግን አባት ያስፈልገናል። ሙሴና አሮን ያስፈልጉናል፤ የሚመራን ደግ አባት ያስፈልገናል፤ እስራኤላውያን በጻድቃን አባቶች መሪነት ወደ አባታቸው ርስት ወደ አብርሃም ቤት የሄዱት ስለዚህ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ቃል የገባላቸውን እና እሰጣችኋለሁ ያላቸውን ርስት ፈለጉ፡፡ ፍላጎታቸው ከልብ የመነጨ ስለሆነ በ፮፻ ዘመን ሕዝበ እስራኤል ወደ አገራቸው ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡በዚህ ጊዜ ያላሰቡት ነገር ገጠማቸው፡፡ አሁንም እኛ በቤታችንና በኑሯችን ያላሰብነው ነገር ይገጥመናል፡፡ ሙሴም የቃዴስ በረሐ አጋጠመው፤ ይህ ያጋጥመኛል ብሎ አላሰበም፡፡ እንደዚሁም የበርኔን በረሀ ሀሩር አጋጠመው፡፡ እንደዚሁም የኤርትራ ባሕር ከፊታቸቸው ድቅን አለባቸው፤ ሕዝበ እስራኤል ይህ ድቅን ሲልባቸው ያመለከቱት ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡

እኛም መከራ፣ ጭንቅ፣ ረኃብ ሲገጥመንም ሆነ ያልጠብቀነው ነገር ሲያጋጥመን ወደ እግዚአብሔር እንድንመለከት ሙሴ አስተምሮናል፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት ካለ በግራና በቀኝ የሚመጣብን ጠላት ራሱ ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡ ባሕር ሲኦል ናት፤ ባሕር ዓለም ናት፤ ታሰምጣለች፡፡ እያሳሳቀች እንደ ዴማስ ትወስደናለች፡፡ ይህ ሁሉ ግን የሚያቆምልን እግዚአብሔር አምላክ ባመለከተን በትር ውኃውን ስንመታው ነው፡፡ የሚታየን ገደል የሚታየን ደስታ ደስታ እንዳልሆነ ያሳየናል፡፡ ዓለም ገደል ሆኖ ይታየናል፤ ብርሃን በሌለው ዓይናችን ስናይ ግን ደስታ ይሰማናል፤ ልክ እንደ ዴማስ ደስ ይለናል፡፡ ዓለምን ስንመለከታት ውበቷ ድንቅ ሆኖ ይታየናል፡፡ እስራኤል በሊቀ መልአኩ በቅዱስ ሚካኤል በመጋቤ ብሉይ መሪነት ያንን በረሀና ሀሩር ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን እየመራቸው ባሕሩን ተሻግረውታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ክብር ይግባውና ‹‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› ብሎናል፡፡ (ማቴ.፲፩፥፳፰) እርሱ የለመኑትንም ወደ ዕረፍት ያወጣል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአብዛኞቻችን ሸክም ከብዷል፡፡ እንዲያሳርፈን፣ የከበደ እንዲቀለን ምን ዓይነት መንገድ ላይ እየተጓዝን እንደሆንን ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ሸክማችን ከራሳችን በላይ ከፍ ብሏልና፤ የቆምን እንመስላለን ግን ወድቀናል፡፡ በተለያየ መንገድ፣በተለያየ ምክንያት ወድቀናል፡፡ እግዚአብሔር ጠርቶናልና፤ እኛ አልመጣንም፤ ወደ እርሱ ከተመለስን ግን ሸክማችን ይቀልልናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በእሳት እና በውኃ መካከል አለፍን፤ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን›› ያለውም ይህን ነው፤ ወደ ዕረፍት የወጡት ቅዱሳን በልቦናቸው ንጹሕ ሐሳብ ስለነበር እና የመከራውን ጊዜ እንደሚሻገሩ ስላሰቡ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹በፊትህ መላእክትን እሰዳለሁ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ›› ያለውን መልአኩን ተመለከቱት፤ ቅዱስ ሚካኤልንም አዩት፡፡ (ዘፀ.፴፫፥፫)

ነቢዩ ዳዊት ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ብሎ እንደተናገረው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ሕዝበ እስራኤልን በፊታቸው መርቶ አድኗቸዋል፤ (መዝ.፴፫፥፯) ባሕረ ኤርትራን እንደተሻገሩና እኔ ‹‹ከእናንተ ጋር ነኝ›› ያለውን ቃል አሰቡ፡፡ ሕዝበ እስራኤልም ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርበዋል፤ ‹‹ንሴብሖ›› እያሉም ዘምረዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው›› አሉ፡፡ (ዘፀ.፲፭፥፫) ስለዚህም ዛሬ እኛም እግዚአብሔርን ልናመሰግነን የምንችለው ስላደረገልን ነገር ልናመሰግን ያስፈልገናል፡፡ ሕዝበ እስራኤል ስለሆነላቸው ስላዩት ነገር አመስግነዋልና፡፡

እግዚአብሔር እኛ ባላሰብነውና በሚመቸን ሁኔታ ይዋጋልናል፡፡ እንዲዋጋልን ግን ልቡናችንን ንጹሕ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ልቡናችን ሻክሯል፤ ወደ ክፋትም እየመራን ነው፤ ልቡናችን እንደ ገበቴ ውኃ ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያለ ነው፡፡ ብዙዎቻችንም ተኝተናል፤ በመናፍቃን ቅሠጣ እየተበዘብዝንም ነው፤ ይህም የሆነው በውስጣችን እግዚአብሔር ስለሌለ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ (እውነተኛውን) ይዘን እንደመጓዝ በአርባና በሰማንያ ቀን ያገኘነውን ልጅነት በተለያየ መንገድ እየጣልነው ነው፡፡ እንደ አሳማ ተኝተን እየተበላን ነው፡፡ በጠዋት እግዚአብሔርን አመስግነን የምንወጣ፣ ማታ እግዚአብሔርን አመስግነን የምንተኛ ስንቶቻችን ነን?

ነገር ግን እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል? እንላለን፡፡ ራሄል የታዘዘቺውን ነገር ፈጽማለች፤ እግዚአብሔር ያላትን ነገር አድርጋለች፤ አምላክ ከእርሷ ጋር እንደሆነ ስላመነች የራሳን ልጆች ‹‹እርገጪ›› ስትባል ረግጣለች፡፡ በልቅሶም የጮኸችው የዚህ ሰዓት ነው፤ መከራም ሥቃይ ሲደርስብን ማልቀስ ያስፈልገናልና! የዚህን ሰዓት እግዚአብሔር አምላክ ይሰማናል፤ ይታረቀናል፤ ‹‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ኑ›› ተብለናልና፡፡ ስለዚህ ወደ አምላካችን እንመለስ!፤ ያሳርፈናልና፤ ሥጋውን እንብላ ደሙንም እንጠጣ፤ መድኃኒት ይሆነናልና፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሕይወታቸው በጨለመባቸው ጊዜ ብርሃን እንደሆናቸውም ለእኛ ብርሃን ይሆነናል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዛሬም የምናየው ዓለም የበለጠ እንዲታየን፣ ሥጋውና ደሙን እንቀበል!፡፡ ይኼ ድንግዝግዝ ዓለም ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ብርሃን ሳለላችሁተመላለሱ›› ተብለናልና! (ዮሐ.፲፪፥፴፭) ይህ ውሳጣዊው ብርሃናችን እንዲበራ ሥጋውና ደሙን እንብላ፤ እንጠጣ፤ ይቅር እንባባል፤ ፍቅር፣ አንድነትና መተሳሰብ ይኑረን፤ ያቺን ሰማያዊቷን እየሩሳሌም እንናፍቅ፤ ተስፋ እናድርግ፤ እኛ ርስታችን በምድር አይደለም፤ በሰማይ እንጂ፡፡ ይህ በአርባና በሰማንያ ቀን ልጅነትን የሰጠን አባት አለን፤ አባታችን ደግሞ ይቀበለናል፤ የሚቀበለን ግን ከእርሱ ርቀን ስንኖር ሳይሆን ስንመለስ ነው፡፡

ስለዚህም በአርባ በሰማንያ የተቀበልነው፣ በመንፈስ ቅዱስና በውኃ የተጠመቅን ክርስቲያኖች ልንሆን ይገባል፡፡ ብርሃነ ዓለም ክርስቶስ ለዓለም ብርሃንን ያበራ ክርስቶስ በውስጣችን እንዲኖር ልቡናችንን ንጹሕ እናድርግ፡፡ በቋንቋ፣ በዘር፣ በሃይማኖት የምንለያይ ሰዎች ግን መሆን የለብንም፡ እግዚአብሔር አምላክ ምክንያቱም ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት ጊዜ አለና ሁሉንም በሥራው ሊከፍለው ይመጣል፡፡ ሰዎችን መለየት ግን የእኛ ሥራ አይደለም፡፡

ታድያ ክርስቶስ በውስጣችን ካለ ምን እያደረግን ነው? ምን እየሠራን ነው? መመላለሳችን በከንቱ እናዳይሆን፣ ሊቀ መልአክት ቅዱስ ሚካኤል መጋቤ ብሉይ እንዲራዳን፣ ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር ወደ መንበረ ጸባዖት እንዲያደርስልን ንጹሕ ልብ ያስፈልገናል፤ ፍቅር ያስፈልገናል፤ አንድነት ያስፈልገናል፤ መተሳሰብ ያስፈልገናልና መነቋቈሩን መተው ያስፈልጋል፤ የዚህ ሰዓት ራሄልንም የሰማው እግዚአብሔር አምላክ ይሰማናል፡፡ ሁሉ ሴቶች ሳይቆጠሩ አንዷ ራሄል የእነዚያ ሁሉ እናቶች እንባ ይዛ ወደ ሰማይ ረጨቺው፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰማ፡፡ ያ! ጸሎት፣ ያ! ለቅሶ፣ ያ! እንባ እስራኤላውያንን ከ፬፻፴ ዘመን ባርነት አውጥቶ ወደ ምድረ ርስት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፤ አንድም ወዳዘጋጀልን ርስት ወደ ዘላለማዊ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለቅሶ ማልቀስ ያስፈልገናል፡፡

ቅድስተ ቅዱሳን ንጽሕተ ንጹሐን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአማላጅነቷ አትለየን! ሊቀ መልአክት መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልም ያማልደን! አባቶቻችንን ይዘን፣ ንስሓ ገብተን፣ ሥጋውን በልተን፣ ደሙን ጠጥተን፣ መንግሥቱን እንድንወርስ አምላካችን መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን፤ አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!