ወረደ መንፈስ ቅዱስ

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መንፈስ ቅዱስ ማለት ከሦስቱ አካላት (ከቅድስት ሥላሴ) አንዱ፤ የእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር ወልድና የራሱም አካላዊ እስትንፋስ የኾነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

*ወረደ መንፈስ ቅዱስ* የሚለው የግእዝ ዓረፍተ ነገርም *መንፈስ ቅዱስ ወረደ* የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን፣ ይህ ሲባልም በሰዉኛ ቋንቋ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከሩቅ ወደ ቅርብ መምጣቱን ወይም መውረዱን ሳይኾን የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ አድሮ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብን መግለጹንና ልዩ ልዩ ጸጋን ማደሉን ያመላክታል፡፡

ይህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሰጥም፣ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይገደብ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በምእመናን ላይም አድሮ ይኖራል፡፡

ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ወረደ የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን በቦታ፣ በጊዜና በወሰን መገደቡን አያመለክትም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለሙ ኹሉ የሞላ ነውና፡፡ በሰው ላይ አድሮ ጥበብን ሲገልጽ ግን ሞላ፤ አደረ፤ ወረደ ተብሎ ይነገራል፡፡ ይኸውም ሥራዉን በሰው ላይ መግለጡን፣ ጸጋዉንም ማብዛቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቋንቋ ነው፡፡

ከላይ እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ፍርኃትን አስወግዶ ጥብዓትን (ጭካኔን)፣ ስጋትን አጥፍቶ ቈራጥነትን (ድፍረትን) ማሳደሩን፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ጸጋን እንዲያገኙ ማድረጉን፤ በዚህም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌልና ለሰማዕትነት የሚያበቃ ቅድስና ላይ መድረሳቸዉን ያመለክታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት፣ በተጠመቀባትና ከሞታን ተለይቶ በተነሣባት በዕለተ ሰንበት (በሰንበት ክርስቲያን) ሲኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ሰንበት (ከኀምሳኛው ቀን) ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰንበት ያለው ጊዜም (ስምንቱ ቀናት) ዘመነ ጰራቅሊጦስ ወይም ሰሙነ ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ስለ መውረዱና በምእመናን ላይ ስለ ማደሩ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ ሰሙን በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር፣ የሚሰጠውም ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ መውረድ የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህም ከኀምሳኛው ቀን (ከበዓለ ጰራቅሊጦስ) ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ (በስምንተኛው ቀን) በሌሊት በሊቃውንቱ የሚዘመረው መዝሙር፡- *ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኵሉ በሐውርት* የሚል ሲኾን፣ ትርጕሙም መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ መውረዱንና በእርሱ ኃይል በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገራቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡

በዚህ ዕለት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም፡- የሚከተሉት ናቸው፤ ኤፌ.፬፥፩-፲፯፤ ፩ኛዮሐ.፪፥፩-፲፰፤ ሐዋ.፪፥፩-፲፰፤ መዝ.፷፯፥፲፰ (ምስባክ)፤ ዮሐ.፲፬፥፩-፳፪ (ወንጌል)፡፡

የምንባባቱ ፍሬ ዐሳብም የጳውሎስ መልእክት፡- እያንዳንዳችን መንፈስ ቅዱስ በገለጸልን መጠን የየራሳችን ልዩ ልዩ ጸጋ እንዳለን፤ የዮሐንስ መልእክት፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘለዓለም ሕያው እንደ ኾነ፤ የሐዋርያት ሥራ፡- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ እንደ ወረደና በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገር እንደቻሉ፤ መዝሙረ ዳዊት (ምስባኩ)፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልዩ ልዩ ጸጋን እንደሚሰጥ፤ የዮሐንስ ወንጌል፡- እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን እንደ ወላጅ አልባ እንደማይተወን ያስረዳሉ፡፡

ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን፣ ይህም ምሥጢረ ሥላሴን፣ የጌታችንን ሰው መኾን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና መንፈስ ቅዱስን መላኩን ይናገራል፡፡

ቅድስት በኾነች በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በኹላችን ላይ ይደር፤ እጽፍ ድርብም ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡