“ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አታሸነፍ” (ሮሜ ፲፪፥፳፩)

መምህር ሳምሶን ወርቁ
ጥር ፲፯፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ክፉና በጎ የሰው ልጆች ባሕርያት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ለመልካም ነበረ፡፡ (ዘፍ.፩፥፲፪) ምንም እንኳን የፍጥረት አክሊል የሆነው ሰው ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ከብርሃን ጨለማን፣ ከሕይወት ሞትን፣ ከመታዘዝ አለመታዘዝን ቢመርጥም እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረው ስሙን እንዲቀድስ ክብሩን እንዲወርስ ነበረ፡፡ ለዚህም ክፉና ደጉን መለየት ይችል ዘንድ አስቀድሞ የሚያስተውል አእምሮ ሰጥቶት ነበር፡፡ በኅሊናው መመራት ተስኖት የሰው ልጅ ከወደቀ በኋላ ዳግመኛ የተጻፈ ሕግ ሰጥቶታል፡፡ ሰዎች ራሳቸው ላይ የክፉ ብድራት እንዳይደርስባቸው አስበው በባልንጀራቸው ላይ ክፉ እንዳያደርጉ ክፉ ላደረጉ የክፉ ብድራት እንዲከፈላቸው ሙሴ ሕግን ጻፈላቸው፡፡

ክፉ የሚያደርጉ ሁሉ ቅጣት ነበረባቸው፤ “ሕይወት በሕይወት፥ ዓይን በዓይን፥ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥መቃጠል በመቃጠል፥ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል” እንዲል። (ዘፀ.፳፩፥፳፬) በተመሳሳይ ሙሴ ለእስራኤል ሲናገር “ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት። ስብራት በስብራት ፋንታ፥ዓይን በዓይን ፋንታ፥ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት። እንስሳውንም የሚገድል ካሳ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል” በማለት ሕግን አስተምሯል፡፡ (ዘሌ.፳፬፥፲፱)

የሕግ መምህር ሐጋጌ ሕግ የሆነው አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱን ወንጌል በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር አስቀድሞ የነበረው በሙሴ የተነገረው እንዳለፈ ሲናገር “ዓይን ለዓይን ጥርስ ለጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ ክፉን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጨህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ፡፡” (ማቴ.፭፥፴፰) ክፉን በክፉ ሳይሆን በበጎነት ማሸነፍ እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡

ክፉን በክፉ መመለስ ምን ያስከትላል?

ዛሬ ላይ በቤተሰባዊ ሕይወታችን ባል በሚስት፣ ሚስት በባል፣ ወላጆች በወላጆች፣ ልጆች በወላጆች ላይ በክፋት ተነሣስተው አንዱ ሌላው ላይ “እንዲህ አደረጉ ሲባል እንሰማለን፡፡ ለጥፋታቸው እንዲህ አድርጋኝ ነው፤ እንዲህ አድረጎኝ ነው” የሚሉ ምክንያቶችን ሲደረድሩም እንሰማለን፡፡ ክፉን በክፉ መቃወም ሰዎችን የበለጠ እልኸኛ ያደርግ ይሆናል እንጂ ክፉ አድራጊዎችን ከክፋት ለመመለስ አይችልም፡፡ ክፉን በክፉ በመመለስ ሰዎች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነትን ማቋረጥ፣ ከዚያም ባለፈ ትልቁን ተቋም ቤተሰብ እስከማፍረስና ልጆች እስከመበተን ያደርሳቸዋል፡፡ ክፉን በክፉ መመለስ ለጊዜው የአሸናፊነት ስሜት በመፍጠር ደስ የሚያሰኝ ቢመስልም ፍጻሜው ጸጸት ነው፡፡ አንዳንዶች ደረሰብኝ ለሚሉት ክፉ ነገር በክፉ መልሰው ከጸጸት ለመሸሽ ሲሉ አደንዛዥ ዕፅንና መጠጥን መደበቂያ የሚያደርጉት ለዚህ ነው፡፡

እንደሀገርም ከገባንበት የፖለቲካ አዙሪት መውጣት የተሳነን ክፉን በክፉ የመመለስ ደዌ ስለተጠናወተን ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን አሳጥቶ ሁለንተናዊ ቀውስ እያስከተለብን ይገኛል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ግለሰቦችና ቡድኖች “ደረሰብን ቆመንለታል” በሚሉት ማኅበረሰብ ላይ ደረሰ ለሚሉት ክፉ ነገር አማራጭ መፍትሔ አድርገው የሚያስቡት መልሶ ክፉን በክፉ መመለስ የሆነው ለዚህ ነው፡፡ ክፉን በክፉ መመለስ ለተጠቃው አካል ምን ይጨምርለታል? መቼስ ይህንን ለመረዳት የተለየ ዕውቀት አይጠይቅም፤ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ክርስቲያን መሆን ደግሞ ተጨማሪ ኃላፊነት ነው፡፡ የደረሰብን ክፉ ነገርን በክፉ እንዳንመልስ የወንጌል ሕግ ግድ ይለናል፡፡ “ተወዳጆች ሆይ፥ራሳችሁ አትበቀሉ፥ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፏልና።” (ሮሜ ፲፪፥፲፱)

ክፉን በመልካም መመለስ ለጠላት ጊዜያዊ ድል ሊያስገኝ ይችላል!

ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ይሆናል እንጂ ከክፉዎች ፍላጻ ዕረፍት ያገኘችበት ዘመን አለ ማለት ይቸግራል፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን የክፉዎች ጥቃት ተቋማዊ ሆኖ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል፣ የምእመናን ደም ማፍሰስና ማሳደድ በስፋት እየተመለከትን ነው፡፡ ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያን በልጆቿ መሥዋዕትነት ሀገርን አጽንታ ብታቆይም መብቷን በድርድር በቸሮታ እንድትቀበል ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ከመሀል ሀገር እስከ ጠረፍ እየተመለከትን ነው፡፡ በጌታችን ሞት እንደተባበሩት እዚህም እዛም ከኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት በአፍአ ያሉ የእምነት ቡድኖች ተባብረው ቀድሞ የነበረውን ስውር ጦር በግልጽ መወርወር ጀምረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን በዐደባባይ የምታከብራቸውን ቦታዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳት፣ በበዓላት ላይ እንዲህ ዓይነት ቀለም ለበሳችሁ በማለት ምእመናንን ማንገላታት ማስቆጣት፣ ምክንያት እየፈለጉ በኦርቶዶክሳዊ ማንነት ማሸማቀቅ፣ መደብደብ ፣ ማቁሰልና መግደል የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ ሁሉ ጠላት ለጊዜው ድል ያገኘ እንዲመስለው ያደርግ ይሆናል እንጂ ፍጻሜው ጥፋት ውድቀት ነው፡፡ “የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኃጥእ ግን በኃጥአቱ ይወድቃል” እንዲል፤ (ምሳ.፲፩፥፭) ለጊዜው ከፍ ከፍ ብሎ መታየቱ የውድቀቱ መጀመሪያ እንደሆነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ “ኃጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት፡፡ ብመለስ ግን አጣሁት ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም” እንዲል፡፡ (መዝ.፴፯፥፴፭)

ክፉን በመልካም መመለስ ትዕግሥታችንን ይፈትናል!

ባለንበት ዘመን አብያተ ክርስቲያናት እንደ ጣፍ ሲነዱ፣ ንዋየ ቅድሳት እንደ ደረቅ እንጨት ሲማገዱ፣ አገልጋይ ካህናትና ምእመናን እንደ መጻተኛ ሲሳደዱ፣ ይባስ ብሎ እንደ በግ ሲታረዱ፣ ደማቸው ክረምት ከበጋ እንደማይደርቅ ጅረት ሲፈስ እየተመለከተ የማይቀና ኦርቶዶክሳዊ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ቅናታችን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊሆን አይገባም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ክፉን በክፉ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ገሥጾታል፤ “ስምዖን ጴጥሮስም ሰይፍ ስለ ነበረው መዘዘው፥የሊቀ ካህናቱንም ባሪያ፡መቶ፟ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የባሪያውም ስም ማልኮስ ነበረ። ኢየሱስም ጴጥሮስን፦ ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው፤ አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣትምን አለው።” (ዮሐ. ፲፰፥፲) ክፉን መታገሥ ስሜታችንን የሚፈታተነን ቢሆንም ራሳችንን ገዝተን ክፉን በመልካም በመመለስ ክፉን ማሸነፍ ይገባል እንጂ ክፉን በክፉ በመመለስ በክፉ መሸነፍ አይገባም፡፡ በሰውኛ አስተሳሰብ ክፉን በመልካም መመለስ ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ ፈቃደኝነቱ ካለን እግዚአብሔር ኃይል ብርታት ሆኖ ያስችለናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ፡፡” (ፊል.፬፥፲፫)

ክፉን በመልካም መመለስ በጠላት ላይ ድል ያስገኛል!

ከሰዎች ጋር በሚኖረን ማንኛውም ግንኙነት የሚያጋጥሙንን ክፉ ሐሳቦችን፣ ክፉ ንግግሮችንና ክፉ ድርጊቶችን በበጎ በመመለስ ክፉ አሳቢዎችን፣ ክፉ ተናጋሪዎችንና ክፉ አድራጊዎችን ማስተማርና ወደ መልካም መንገድ መመለስ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” ተብለናልና ክፉዎች የሠለጠኑበት አልጫው ዓለም የሚጣፍጠው እኛ ጨው ሆነን ስንገኝ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ (ማቴ.፭፥፲፫) እንዲሁም ክፋት የበረታበት ጨለማው ዓለም በብርሃን የሚመላለሰው በእኛ ክርስቲያኖች ብርሃንነት ነው፡፡ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡” ስለዚህ ክፉን በመልካም በመመለስ ለአልጫው ዓለም ጨው፤ ለጨለማው ዓለም ብርሃን መሆን የእኛ ድርሻ ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፲፬) ክፉን በመልካም መመለስ በጠላት ላይ ድል ያስገኛል፤ ምክንያቱም እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡

ክፉን በመልካም ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

በወንጌል ትርጓሜ ክፉን በበጎ ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያስረምር ታሪክ አለ፡፡ ታሪኩ የአንድ ባሕታዊ ሲሆን እርሱ በበዓቱ ሳለ ወንበዴዎች እንግዶች መስለው መጡበት፤ እግራቸውን አጥቦ አብልቶ አሳደራቸው፤ ሌሊት ተነሥተው እርሱን አሥረው መብራት አብርተው ያለ ገንዘቡን ይዘው ሄዱ፡፡ ከሄዱ በኋላ መብራት አብርቶ ቢያይ ሁለት ድሪም የምታወጣ ፀምር አገኘ፡፡ “ይህችም ለአንድ ጉዳይ ትሆናችኋለች” ብሎ ተከትሎ ወስዶ ሰጣቸው፡፡ ይህ ሰው እንዲህ ማድረጉ ከዚህ የበለጠ ዋጋ እንዳለ ቢያውቅ እንጂ ነው ብለው ተመልሰው ንስሓ ገብተው የሚኖሩ ሁነዋል፡፡ ሰዎች የቱንም ያህል ለክፋት ቢሠለጥኑ እግዚአብሔር ኅሊናን የሚያህል ዳኛን ሰጥቷልና የጊዜ የሁኔታ ጉዳይ ይሆናል እንጂ መመለሳቸው አይቀርም፡፡

ክፉ አድራጊዎች ላይ እንኳን ብድር መመለስ ይቅርና መጥላት እንደማይገባ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡፡ “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህን ጥላ እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ በሰማይ ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግማችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞች ላይ ዝናብን ያዘንባልና፡፡ የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ፤ ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን፡፡” (ማቴ.፭፥፵፫) ክርስቲያኖች ሰዎች በጠላትነት ተነሥተውባቸው ሲረግሟቸውና ሲያሳድዷቸው ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን ባያውቅ ባታውቅ ነው ብለው መታገሥ እንደሚገባ፣ የሚወዱንን ብቻ ሳይሆን የማይወዱንን በመውደድ ለማያምኑ ሃይማኖታችንን በተግባር በመግለጥ የድኅነት ምክንያት መሆን ከእኛ ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ክፉን በመልካም ማሸነፍ ማለት ክፉ ግብር ይዘው የነበሩ ሰዎችን መልካም ግብር እንዲይዙ ማድረግ ነው፡፡ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።” (ማቴ.፲፰፥፴፭)

ወንጌል አዲስ ሕግ አዲስ ትእዛዝ ናት፤ ጌታ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ ያለው “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።” (ዮሐ.፲፫፥፴፬) አዲስ ትእዛዝ የተባለው ፍቅር ሲሆን አንዱ ለአንዱ ይሞትለት ዋጋ ይከፍልለት ዘንድ የወንጌል ሕግ ተሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም ሰዎች ክፉ ሲያደርጉብን በክፉ ከመመለስ ይልቅ “ባያውቅ ባታውቅ ነው” በማለት ክፉን በመልካም በመመለስ ፍቅርን በተግባር መግለጥ ክፉን በመልካም ማሸነፍ ይገባል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር