ክብር ለኢትዮጵያውያን ሰማዕታት!

የቂሳሪያ ሊቀ ጳጳሱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውስብዮስ የሰማዕታት ደም የክርስትና ዘር እንደሆነ በለገጸበት አንደበቱ ሰማዕታትን አክብራቸዋል፡፡ እነርሱን ማክበር የክርስቲያኖች ግዴታ ብቻ ሳይሆን በረከትና ጸጋን የሚያሰጥ እና በእግዚአብሔር ፊትም ዋጋ ያለው ተግባር ነው በሚልም ገልጿቸዋል፡፡ ቅድስት ቤተክርስያንም በተደነገገው የቅድስና ማዕረግ መሠረት ቀኖናትን አዋሕዳና አስማምታ ታሪካቸውን እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

ከሁለት መቶ ሰባ ስድስት እስከ ሦስት መቶ አምስት ዓ.ም. (እ.ኤ.አ) ደግሞ በቄሣር ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በቤተክርስቲያኖች ትልቅ የታሪክ ክስተት በመሆኑ ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ይህም በሮማውያን ቄሣሮች ዘመን ከቄሣር ኔሮ ጀምሮ እስከ በዲያቅልጥያኖስና መክስምያስ ዘመን ድረስ በክርስቲያኖች ላይ የታወጀው ጅምላ ጭፍጨፋ ለማውሳት የተሰየመ ነው፡፡ በተለይም የኮፕቲክ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ስለ ቀናች ሃይማኖታቸው ሲሉ የተቀበሉትን ሰማዕትነት ለዘለዓለም ለማክበር ተብሎ የተደረገው ነው፡፡

ሰማዕታት እንደየሥራቸው ሲዘከሩ ይኖራሉ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያም ምእመናን ለእምነታቸውና ለሃይማኖታቸው ችግር መከራን በመቀበላቸውና በመገደላቸው ለእነርሱ ክብር ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያን ታስባቸዋለች፡፡ እነዚህ ምእመናንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመገደላቸውም ትውልዱም ያስታውሳቸው ዘንድ ስማቸውን ታወሳለች፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት ታኅሣሥ ወር ፳፬ ቀን ጸጥታ አስከባሪዎች በሁለት ወጣት ኦርቶዶክሳውያን ላይ በግፍ የገደሉትን ስፍራ የ ‹‹፳፬ ቀበሌ›› ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲሠራበት በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት መጋቢት  ፮ ፳፻፲፪ ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡

ሃይማኖቱን በግልጽና በድፍረት መመስከር እንዲሁም መስዋዕት መክፈል ለፈጣሪያችን ፍቅርን የምናሳይበት ተግባር ሰማዕትነት ነው፤ ‹‹እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ›› ብሎ ክርስቶስ የተነገረላቸው እነርሱ ናቸው፡፡ (ማቴ. ፲፥፴፪) በመከራቸው ጊዜ ብትመስላቸው ስለ ቁርጥ ሀሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡

አስቀድሞ ጌታችን እንደተናገረው እና በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፳፤ ቁ.፯፻፶ እንደተጠቀሰው ዳግመኛ እንዲህ አለ፤ ‹‹በዚህ ዓለም መከራና ኀዘን ያገኛችኋል፡፡ ወደ አደባባይ ያገቧችኋል፡፡ ለእናንተ ምስክር ሊሆንላችሁ ስለ እኔ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ያደርሷችኋል፤ እስከ መጨረሻ የታገሠ እርሱ ይድናል፡፡ ለክርስቶስ እንዳልሆነ የሚክድ ከእግዚአብሔር ይልቅ ፈጽሞ ራሱን የወደደ ሰው ግን ይቅርታ አያገኝም››፡፡

ሰማዕታትን በማክበር ለቤተክርስቲያን ሕልውናና ለምእመናን መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚሰጠውን ብርታት እንወቅ፤ በረከትና ጸጋ በማግኘት ሁላችንም እንበርታ፤ ሰማዕታትን በማሰብ በደማቸው ያጸኑትን ሃይማኖት እናስጠብቅ!

ምንጭ፤ ከአባ ሳሙኤል (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ) ስብከት