Kibre Gedamat2003 .jpg

ክብረ ገዳማት በፆመ ፍልሰታ መጀመሪያ

ሐምሌ 26 ፣2003 ዓ.ም.                                        
 
በገዳማትና በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን ነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም “ክብረ ገዳማት” በሚል መሪ ቃል የ10ኛ ዓመት የገዳማትን አገልግሎት የሚያዘክር ዐውደ ጥናት በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል ከ7፡30-11፡30 አዘጋጅቷል፡፡ ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ ዓውደ ጥናቱንና የክፍሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሰብ ተጠባባቂ ኃላፊ ከሆኑት ከዲ/ን ደረጀ ግርማ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሥራ ሲጀምር በየትኛው ደረጃ ነበር የጀመረው?

ሥራው የተጀመረው በ1992 ዓ.ም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ነው፡፡ አገልግሎቱን ሲጀምር አነስተኛ ጊዜያዊ እርዳታ በመስጠት፣ ለገዳማትና አድባራት ያለባቸውን የመባ እጥረት ከመቅረፍ አንጻር ጧፍ፣ ዕጣን ዘቢብ በመላክ እና አነስተኛ ኘሮጀክቶች ላይ መነኮሳትን ሊያበረታታ በሚችል መልኩ ድጎማ በማድረግ ነው፡፡

ክፍሉ እስከ አሁን በምን ያህል ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ እንቅስቃሴ አድርጓል? 

የዛሬ 10 ዓመት ይህ እንቅስቃሴ ሲጀመር ገዳማትና አድባራት ያለባቸውን ችግር በማጥናት ነው፡፡ አንድን ነገር ከመረዳት በፊት የጥናት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ችግርን ማወቅ ግማሽ መፍትሔ ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ ሰዓት ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ችግር ምን እንደሆነ አውቀናል፡፡ እነዚህ ገዳማትና አድባራት መጀመሪያ በነበረባቸው የድርቅ አደጋ እንዲሁም በመሬት ላራሹ አዋጅ ምክንያት በርካታ ቦታዎች ሲወሰዱ ባዷቸውን ቀርተው ነበሩ፤ ከዛ ውጭ በሰፈራና ከአስተሳሰብ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ። እነዚህን ችግሮች ከመቅረፍ አኳያ ጅምራችን በጥቂት የአብነት ትምህርት ቤቶች ነበር፡፡ አሁን ግን በ100 የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ፕሮጀክት ጀምረናል፡፡ በጊዜያዊ እርዳታ ደግሞ ከ70 እና 80 በላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ እያደረግን ነው። በአጠቃላይ ባደረግነው ቅኝት ከ250 በላይ የሆኑትን ችግራቸውን መለየት ተችሏል፡፡ ከአቅም ውስንነት አኳያ ሥራ እየሠራን ያለነው በ100 የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ገዳማት ላይ ያለባቸውን ችግር በመቅረፍ ግን በ26 ገዳማትና አድባራት ላይ የመጀመሪያ ጥናት ተደርጎ ነው ሥራ የተጀመረው፤ ከዛ በኋላ ግን በቋሚ ፕሮጀክት ደረጃ ከ60 በላይ በሆኑ ገዳማት ተተግብሯል፡፡ የንብ ማነብ፣ የከብት ማድለብ፣ የሽመናና የግንባታ ሥራዎች ከተተገበሩት ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በየአቅጣጫው ከ100 በላይ የሆኑ ገዳማትን በቅኝትና በዳሰሳ  ደረጃ ለይተናል። በተለይ ጥንታዊያኑን ለመቃኘት ተችሏል፡፡

ነሐሴ አንድ ቀን “ክብረ ገዳማት” በሚል መሪ ቃል ሲምፖዚየም አዘጋጅታችኋል፤ ሲሞፖዚየሙ የተዘጋጀው ለገዳማት ብቻ ነው ወይስ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ያካትታል?

Kibre Gedamat2003 .jpgይህ ክፍል ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ገዳማት ላይ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ቢያፈስም፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ትውልድ የማትረፍ ሥራ በመሥራት ትኩረት አድርገን ብዙ ሲሞፖዚየሞችን አድርገናል፡፡ ለምሳሌ አብነቱ ያለ አብነት እንዳይቀር፣ ቅኔ፣ በእንተ ስማ ለማርያም፤ እነዚህ ሲሞፖዚየሞች ቀጥታ የሚያመለክቱት የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው፡፡ አሁን ግን እራሱን ችሎ ገዳማትን በተመለከተ ዓውደ ጥናት ሲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አነስተኛ ዓውደ ጥናቶች በተለያዩ ቦታዎች አድርገናል፡፡ ነገር ግን እጅግ በጣም ብዙ ምዕመናን ጠርተን እንደዚህ ዓይነት መርሐ ግብር ከማድረግ አኳያ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሲሞፖዚየም ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ?

ገዳማትና አድባራት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብሎም ለሀገራችን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የጎላ ነው፡፡ ግን ይህ የጎላው አስተዋጾአቸው ገሀድ ወጥቶ ትውልዱ እየተረዳው ነው ማለት በጣም ይከብዳል፡፡ ይህን ለማለት ያስደፈረን፥ ባጠናነው ጥናት መሠረት ከከተማ የራቁና በተለይ በጣም ትልልቅ የሆኑ ገዳማትና አድባራት የሚረዳቸው አጥተው አብዛኛዎቹ አንድነታቸው ተፈትቷል፡፡ ስለዚህ እነዚያን ታላላቅ ገዳማት በማስታወስ ትውልዱ በነዚህ ገዳማት ላይ ሥራ እንዲሠራ ለማስቻል ነው፡፡

ሁለተኛ ደግሞ በገዳማትና አድባራት ላይ በርካታ ጥናት ያጠኑ ምሁራን አሉ፡፡ በዩኒቨርስቲ ደረጃም ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ያጠኑት ጥናት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ነው፡፡ ግን የሚያቀርቡበት ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ አልነበራቸውም። ለሕዝቡም ሊደርስ በማይችል ሁኔታ ነበር። አሁን ግን እነዚህ ሰዎች በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ሁኔታዎችን ብናመቻችላቸው ለሕዝቡ የገዳማትንና አድባራትን አገልግሎትና ጥቅም እንዲሁም የነበራቸውን ሀገራዊ ፋይዳ ማሳየት ይቻላል፡፡ በዚህም ትውልዱ ይህን ተረድቶ ገዳማት ላይ ለመሥራት ትልቅ አቅም ይኖረዋል ብለን ስላሰብን ነው፡፡

ሌላው ማኅበረ ቅዱሳን  በዓመት ቢያንስ ከ12 በላይ ትልልቅ የገዳማት ፕሮጀክቶችን ይዞ ይሠራል፡፡ ስለዚህ በ2004 እና በ2005 ዓ.ም ለትግበራ ጥናታቸው የተጠናቀቀላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እነዚህን ማስተዋወቅም አስበናል፡፡

ከዚያ ውጭ እስከ አሁን ቅኔ፣ አብነቱ ያለአብነትና በእንተ ስማ ለማርያም የሚሉ ዘጋቢ ፊልሞች አዘጋጅተናል፡፡ በገዳማት ላይ ግን ወጥ አድርገን የሠራነው ሥራ የለም፡፡ ስለዚህ አጠር ብሎ ስለገዳማት በቂ መረጃ ሊሰጥ የሚችል ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅተን ለሕዝቡ በማሳየት ገዳማት የእርሱ እንደሆኑ፣ የቅርስ ማደርያ እንደሆኑ፣ በተፈጥሮ ሀብት ደኑን ተንከባክበው ያቆዩ መሆናቸውን በማዘከር፣ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡

ከዛ በላይ ደግሞ በዚህ አስር ዓመት እንቅስቃሴ ውስጥ አብረውን የነበሩ ገዳማት Gedamat_Vegetable.JPGአሉ፡፡ እነዚህ ገዳማት ያላቸውን ተነሳሽነት፣ በተሰጣቸው ትንሽ ድጋፍ ተጠቅመው ገዳማቶቻቸውን ለመለወጥ ባደረጉት ጥረት ማበረታታት ይጠበቅብናል። ከያሉበት ጠርተን ከእኛ ጋርም ተገኝተው፥ የቀደመ ክብራቸውን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ «ክብረ ገዳማት» በሚል እንቅስቃሴ ለመጀመር አስበን ነው ነሐሴ 1 ቀን መርሐ ግብር ያዘጋጀነው፡፡

በዚህ በ10 ዓመት ውስጥ በገዳማት ላይ ምን ለውጥ አመጣን ብላችሁ ታስባላችሁ?

ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ግን ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አኳያ የገዳማትና አድባራትን ችግር ቀርፈናል ብሎ ለመናገር ደግሞ አይቻልም፡፡ በ10 ዓመት ጉዞ ውስጥ በርካታ የተፈቱና ጠፍ ሆነው የነበሩ ገዳማት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በተደረገላቸው አነስተኛ ድጋፍ ብዙ ለውጥ ተገኝቷል፡፡ ለምሳሌ በባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም አንድነቱ ተፈትቶ መነኮሳትም መንምነው መተዳደሪያ ሳይኖራቸው በጣም ተቸግረው ነበር፡፡ ዛሬ ግን በአትክልት ልማትና በወተት ልማት በተደረገላቸው ድጋፍ መነኮሳቱ በወር ከ27,000 ብር በላይ ገቢ የሚያገኙበት ሕይወት ተፈጥሮ፥ ወንበር ዘርግተው መምህራን ቀጥረው የተማሪ በጀት እንኳ በጅተው ዛሬ ገዳሙ የመነኮሳቱ ቁጥር ሰፍቶ እንመለከታለን፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ላይ በተደረገው ተደጋጋሚ ድጎማ ሁለገብ ሕንፃ በመገንባቱ ምንም እንኳ ሕንፃው በሂደት ቢሆንም አራት ቀርተው የነበሩ መነኮሳት ዛሬ ከአርባ ስድስት በላይ ሆነው ቀለብ እያነሳቸው ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ገዳም አንድና ሁለት መነኮሳት ብቻ ቀርተው ነበር፡፡ በዚያው አካባቢ የነበሩ ሰዎች አስተባብረው የሙአለ ሕፃናት ግንባታ በገነቡበት ወቅት ከ400.000 ብር በላይ በዚህ በገዳማት ክፍል ድጎማ ተደርጎ ትምህርት ቤቱ በማለቁ በዚያ ኪራይ ዛሬ ገዳሙ እየተጠቀመ የመነኮሳቱ ቁጥራቸው እየተበራከተ ጥንታዊውን ገዳም ከጥፋት ለመታደግ ተችሏል፡፡

በዝርዝር ብንቆጥራቸው በጣም በርካታ ናቸው፡፡ በአምስትያ ተክለ ሃይማኖት የውሃ ፕሮጀክት፣ በእማ ምዑዝ ገዳም የነበሩትን ችግሮች መደጎም በመቻላችን እነዚህ ገዳማት እንዲያንሠራሩና ለውጥ እንዲያመጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመርዳት ስታስቡ መነሻና መሥፈርታችሁ ምንድን ነው?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ሕግና ደንቡ ጸድቆ ከተሰጠው ጊዜ ጀምሮ በገዳማት በአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ነው፡፡ እንዲደግፍም ሲባል አህጉረ ስብከት ወይም ገዳማት በአካልም በደብዳቤም መጠተው ይረዳ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እኛም ጥያቄአቸውን ተቀብለን ዝም ብለን አንረዳም፡፡ ቦታው ድረስ በመሄድ፣ ባለሙያዎችን በመላክ ቦታው ካለው ጥንታዊነትና ቅርስ አኳያ፣ የመነኮሳት ማኅበራዊ ሕይወትስ ምን ይመስላል የሚለው በስፋት ከታየና ከተጠና በኋላ ይህን ገዳም ብናጠናክር የቤተ ክርስቲያኒቷን እሴቶችና ጥንታዊነቷን ጠብቀን እናቆያለን፣ የትውልድ የሀገር ቅርሶችን ባሉበት እናጸናለን፣ መነኮሳትን ደግሞ ከፍልሰት መታደግና ባሉበት በልማት አሳትፎ ከማቆየት አኳያ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ከዚያም ሀገረ ስብከቱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አማራጭ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከመነኮሳቱ ፍላጎትና ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በሚሰናሰል መልኩ፥ ከአካባቢው የአየር ጠባይ ሁኔታ፣ መነኮሳትን በማሳተፍ እንተልምና ፕሮጀክቱ ከጸደቀ በኋላ የሚረዳ አካል ይፈለግለታል፡፡ ይህም ማኅበራትን፣ ሠራተኛ ጉባኤያትን፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችን፣ የማኅበሩን አባላት በማስተባበር ፕሮጀክቶቹ ይተገበራሉ፡፡ ከተተገበሩም በኋላ ይህ ሥራ ከተሠራለት ገዳም ጋር ውል/ሰነድ ተፈራርመን ሥራ እንጀምራለን፡፡ በውል ሠነድ ደግሞ እናስረክባለን፡፡

ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ላይ ፕሮጀክት ስትሠሩ ከገዳማቱ ከመቀበላቸውና ከመተግበራቸው አንፃር ተነሳሽነታቸውን እንዴት ታዩታላችሁ?

አስቸጋሪም ጥሩም ነገር አለ። አንድ ገዳም ላይ ስትገባ የምትጠየቀው ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ለምን መጣችሁ? ለምን ትረዱናላችሁ? ሥራ ካማረን ከቤታችን አንኖርም ነበር ወይ? እዚህ ለጸሎት ነው የመጣነው። እንደውም በአንዳንድ ገዳማት ዘመናዊ ነገር አይግባባችሁ ተብለናል፡፡ አንፈልግም አንሠራም የሚሉበት ጊዜ አለ፡፡ በጉዳዩ እስክንግባባ ከአህጉረ ስብከት ጋር ብዙ የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ አንድ ፕሮጀክት ከተጀመረ በኋላ የገዳሙ አበምኔት ሲቀየር ጉዳዩን እንደ አዲስ የማየት ነገር አለ፣ አንዳንድ ጊዜም ፕሮጀክቱ ከተሠራ በኋላ የማኅበረ ቅዱሳን ፕሮጀክት ነው እንጂ የገዳሙ ፕሮጀክት ብሎ አለመቀበል፡፡ ከግንዛቤ እጥረትና ከዕውቀት ማነስ የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ ያን ግን በሂደት በማስተማርና በመመካከር የሚፈታ ሲሆን ሌሎች በማኅበረ ቅዱሳን ታቅፈው እድገት ያሳዩ ገዳማትን አርአያነት በመመልከት እየተሳቡ ለእኛም ይሠራልን ይህን አድርጉልን የማለት ነገር አለ፡፡

ከትናንት ዛሬ ይሻላል፡፡ አሁን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ገዳማት መምሪያ ጋር አብረን ለመሥራት አንዳንድ ውጥኖች አሉ፡፡ ተቀናጅተን የምንሠራባቸው ነገሮች የመነኮሳትን ቅበላ በየጊዜው እየተሻሻለ ነው የመጣው ለማለት እደፍራለሁ፡፡

ክፍሉ ለወደፊት ግቡ ምንድን ነው?

የመጨረሻ ግባችን ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው ነው፡፡ በአብነት ትምህርት ቤት ተቋማዊ ይዘት ኖሮት በዩኒቨርስቲ ደረጃ አድጎ በኮሌጅና በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርቱ እየተሰጠ የተማሪው ሕይወት ተሻሽሎና የራሱ ገቢ ማስገኛ ሊኖረው እንዲገባ የምናደርግበትን አጋጣሚ መፍጠር ነው፡፡ ድሮ ሕዝቡ “ስኮላር/scholar” ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ያን አቋረጠ፡፡ ስለዚህ ተማሪው ለልመናና ለጉልበት ሥራ ነው የተዳረገው፡፡ ይህን ለማስቀረትና በራሳቸው ገቢ እንዲተዳደሩና ትኩረት ተሰጥቶት ተቋማዊ የሆነ ይዘት እንዲኖረው እንመኛለን፡፡

Gedamat_Aba.JPGገዳማትም ከልመና ወጥተው በራሳቸው የልማት ሐዋርያ የሚሆኑበት፥ በእደ ጥበብ ሆነ በሌላውም ዘርፍ የተሻለ አደረጃጀትና የተሻለ ገቢ ምንጭ ኖሮአቸው የአካባቢውን ኅብረተሰብ የሚረዱ፥ ወላጅ አልባ ሕፃናትን የሚያሳድጉ፥ በሀገር ላይ የተከሰቱ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ላይ ምላሽ በመስጠትና ኅብረተሰቡን በመንከባከብ፣ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ተገናኝተው ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ የሚችሉ፣ ሥልጠና የሚሰጥባቸው፣ ለዓለም የጥበብ መሠረትነታቸውን የሚያሳዩበት ምዕመናኑም በገዳማት ላይ አእምሮውን ለማደስ፣ እረፍት ለመውሰድና መንፈሳዊ ሕይወትን ለማበልጸግ የሚሔድባቸው፣ ዋናውና ትልቁ ነገር ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤት ማዕከል እንዲሁም የጥናትና የምርምር ማዕከል የሚሆኑበትን ሁኔታ ማየት ነው፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

እኔም አመሰግናለሁ፡፡