ክብረ ቅዱሳን እና ዐሥሩ መዓርጋት

በሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ

ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹ቅዱሳን› ማለት ‹የተቀደሱ፣ የከበሩ፣ የተመሰገኑ፣ የተለዩ፣ የተመረጡ፣ ንጹሐን የኾኑ፣ የጠሩ› ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና የጌትነቱ መገለጫ የኾኑ ዂሉ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ቅዱሳን፣ በሃይማኖት ጸንተው፣ በምግባር ጐልምሰው፣ የሥጋ ምኞታቸውን ትተው ሲገኙ የቅድስና ባለቤት ቅዱስ እግዚአብሔር እነርሱን (ቅዱሳንን) መሣሪያ አድርጐ ኀይሉንና ሥልጣኑን የገለጸባቸው ማኅደረ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ማደሪያ) ናቸው፡፡ ቅዱሳን እንደ መላእክት ውሉደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ልጆች) ይባላሉ (ኢዮ. ፩፥፮፤ ሮሜ. ፰፥፲፬)፡፡

ቅዱሳን፣ በግብር መላእክትን መስለው፣ ኾነው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽመው በመገኘታቸውና ከዚህ ዓለም ፈቃድ በመለየታቸው ቅዱሳን፤ የፈጣሪያቸውን መንግሥት ወራሾች በመኾናቸው ደግሞ ‹ውሉደ እግዚአብሔር› (የእግዚአብሔር ልጆች) ይባላሉ፡፡ በሌላም ቃል ‹ውሉደ ብርሃን› (የብርሃን ልጆች) ተብለው ይጠራሉ (ሉቃ. ፲፮፥፰)፡፡ ‹ውሉደ ሕይወት› (የሕይወት ልጆች) ይባላሉ፤ ሞትንና የሞት ከተማ የኾነውን ይህን ዓለም ንቀውታልና፡፡ በክብር ተነሥተው ዳግመኛ ሊሞቱ የማይገባቸው ናቸውና (ሉቃ. ፳፥፴)፡፡ ቅዱሳን፣ ‹ውሉደ ጥምቅት› (የጥምቀት ልጆች) ተብለዋል፤ ሀብተ ወልድናን (የእግዚአብሔርን ልጅነት)፣ ስመ ክርስትናን ተጐናጽፈዋልና፡፡ ‹ውሉደ መንግሥትም› ተብለዋል፤ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናቸውና፡፡

ቅዱሳን፣ በጸጋ እግዚአብሔር በመበልጸጋቸው ወይም የእግዚአብሔር የምሕረቱ ዓይኖች በመኾናቸው ‹አዕይንተ እግዚአብሔር› (የእግዚአብሔር ዓይኖች) ተብለዋል (መዝ. ፴፫፥፲፭)፡፡ ልመናቸው፣ ጾማቸው፣ ምጽዋታቸው ዂሉ የተወደደ መሥዋዕት ነው፡፡ ቅዱሳን በዓላማቸው ጾምን ግብዣ (ድግስ)፣ ለቅሶን ደስታ፣ ደስታን ሐዘን አድርገው በመኖራቸው ይህ ተለዋዋጭ ዓለም በየጊዜው የሚያቀርብላቸው መርዶ በእነርሱ ዘንድ ዋጋ የለውም፡፡ ዓለምም ለእነርሱ የሚያቀርበው ዓለማዊ የምኞት ስጦታ እንደ ኢ ምንት የተናቀ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ወደ ዓለማውያን ሰነፎች እንደ ኾነ ዂሉ ገጸ ምሕረቱ ደግሞ ወደ ቅዱሳን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድና ቸርነት መገለጫዎችም ናቸውና፡፡ ስለዚህ አማላጅነታቸው፣ ጸሎታቸው ጠቃሚ ነው፡፡

‹‹አፍቅርዎ ለእግዚአብሔር ኵልክሙ ጻድቃኑ እስመ ጽድቀ የኀሥሥ እግዚአብሔር፤ ቅዱሳን፣ እውነትን ይዛችሁ ትሕትናን ተላብሳችሁ እግዚአብሔርን ውደዱት፡፡ እግዚአብሐር እውነትን፣ ትሕትናን ይወዳልና፤›› (መዝ. ፴፥፳፫) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ የቅዱሳን ፍሬ ትሕትና ነው፡፡ በዓይነ ሕሊናቸው ፈጣሪያቸውን፣ በዓይነ ሥጋቸው የእነርሱን ምንነት እንደዚሁም የዓለምን ከንቱነት ይመለከታሉ፡፡ ፍሬ የያዘ ተክል ዂሉ ቁልቁል የተደፋ መኾኑ ትሕትናን ያስተምራል፡፡ ይህም የጻድቃን ምሳሌ ነው፡፡ በፈሪሃ እግዚአብሔር ልቡ የተሰበረ፣ እሱርነቱን (ማንነቱን፣ ምንነቱን) የመረመረ ሰው በዓይነ ሕሊናው የፈጣሪውን ቸርነት፣ በዓይነ ሥጋው የራሱን ውድቀት ይመለከታል፡፡

ይህ አመለካከት ለጸጋ እግዚአብሔርና ለፍሬ ክብር ያደርሰዋል፡፡ በመቅረዝ ላይ ያለች መብራት መሰወር እንዳይቻላት፣ የመቅረዙ ከፍታ እንደሚገልጻት በተራራ ላይ ያለች ቤትም ለእይታ እንደማትሰወር፣ የተራራው ከፍታ እንደሚገልጻት በጥበበ እግዚአብሔር ከብረው በጸጋ እግዚአብሔር ተውበው የሚኖሩ ቅዱሳን ጻድቃንም ደረጃ በደረጃ መዓርጋትን አልፈው ከመለኮት ባሕርይ ተካፍለው የተአምራት መገለጫ ይኾናሉ፡፡ ‹‹መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ፤ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ በወዳጆቹ አድሮ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነው፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፷፯፥፴፭፤ ፪ኛ ጴጥ. ፩፥፫)፡፡

ቅዱሳን፣ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ሙታንን ማስነሣት፣ ዕውራንን ማብራት፣ በአጠቃላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ማድረግ የዘወትር (የዂልጊዜ) ተግባራቸው ነው፡፡ የጸጋና የክብር ባለቤቶች ኾነዋልና በዓለም ላይ ሳሉ የሚመጣባቸውን ፈተና ዂሉ ተቋቁመው የጸጋ መቅረዞች ይኾናሉ፡፡ በዚህ ጸጋቸውም የአናብስቱን አፍ ዘጉ (ዳን. ፯፥፩-፰)፡፡ ውኃውን ወደ ኋላው መለሱ (ዘፀ. ፲፬፥፳፪)፡፡ ዝናም እንዳይሰጥ ሰማይን ለጎሙ (፩ኛ ነገ. ፲፯፥፩፤ ያዕ. ፭፥፲፯)፡፡ ነበልባለ እሳትን አበረዱ (ዳን. ፫፥፩-፲፫)፡፡ የቅዱሳን ወዳጅ እግዚአብሔር አምላካችን ሥጋዊ ሀገረ ተድላን ጥለው፣ ኃላፊ ጠፊ ምድራዊ ምቾታቸውን ንቀው ጸጋውን ከሚጠባበቁት ጋር ዂሉ አብሮ ይኖራል፡፡ ትዕግሥትን የጠዋት ቍርስ፣ የቀን ምሳ፣ የማታ እራት አድርገው የሚመገቧትን ዂሉ ማደሪያ ቤተ መቅደሱ ያደርጋቸዋል፡፡

ቅዱሳን በዚህ ዓለም ይጠበቡበታል፤ ወጥተው ወርደው ሰውነታቸውን ከስስት፣ ኃጢአት ጠብቀው ለወዲያኛው ዓለም ደግሞ በትዕግሥት ደጅ ይጠኑበታል፡፡ ‹‹ፈሪሃ እግዚአብሔር ትፍሥሕተ ልብ ውእቱ ወይሁብ ሐሤተ ወያስተፌሥሕ ወያነውኅ መዋዕለ ሕይወት ለፈራሄ እግዚአብሔር ይሤኒ ደኃሪቱ ወይትባረክ ዕለተ ሞቱ፤ እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፡፡ ፍጹም የሥጋና የነፍስን ደስታ ይሰጣል፤ በሕይወትም ያኖራል፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ፍጻሜው ያምርለታል፡፡ እንደ ኢዮብ ከደዌው ተፈውሶ ልጅ የልጅ ልጅ አይቶ ይሞታል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው ይህ ዂሉ በረከት የቅዱሳን ፍሬ ነው (ኢዮብ ፴፩፥፲፮)፡፡

ቅዱሳን በሚሠሩት ሥራ በያዙት ቅን መንገድ፣ ኢዮባዊ ትዕግሥት፣ አብርሃማዊ ኂሩት፣ ይስሐቃዊ ፈቃደኝነት፣ ያዕቆባዊ ቅን አገልግሎት፣ ዮሴፋዊ ኀዳጌ በቀልነት ሙሴአዊ ለወገን ተቆርቋሪነት እየጨመሩ በመኖራቸው የፈጣሪአቸው ኃይልና ጌትነት እንደዚሁም የድንቅ ሥራው መገለጫዎች ይኾናሉ፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ እየተጨመረላቸው ወደ ዐሥሩ መዓርጋት ይወጣሉ፡፡ ማዕረጋቸውንም ከዚህ ላይ ይናገሩታል፡፡ ዐሥሩ መዓርጋት የሚባሉት በሦስት ይከፈላሉ፡፡ ሦስቱ የንጽሐ ሥጋ መዓርጋት፣ አራቱ የንጽሐ ነፍስ መዓርጋት፣ እና ሦስቱ የንጽሐ ልቡና መዓርጋት ናቸው፡፡

  • ሦስቱ የንጽሐ ሥጋ መዓርጋት የሚባሉት፡- ጽማዌ፣ ልባዌ እና ጣዕመ ዝማሬ ናቸው፡፡
  • አራቱ የንጽሐ ነፍስ መዓርጋት፡- አንብዕ፣ ኵነኔ፣ ፍቅር እና ሑሰት ናቸው፡፡
  • ሦስቱ የንጽሐ ልቡና መዓርጋት ደግሞ፡- ንጻሬ መላእክት፣ ተሰጥሞ እና ከዊነ እሳት (ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ) ናቸው፡፡ በጠቅላላው ዐሥር ይኾናሉ፡፡

ሀ. የንጽሐ ሥጋ መዓርጋት

፩ኛ መዓርገ ጽማዌ

ይህ የመጀመሪያው መዓርግ ነው፡፡ በዚህ መዓርግ ማስተዋል፣ ውስጣዊ ትዕግሥት፣ ውስጣዊ ትሕትና፣ ውስጣዊ የራስ ሚዛንን ይዞ ማሰላሰል ይጀምራል፡፡ ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ እግዚአብሔርን ብቻ መዘከር ይችሉ ዘንድ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድ ከማውራት ይከለከላሉ፡፡ በዚህ መዓርግ ላይ ሳሉ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያየሉ፡፡ ነገር ግን ለምን እንደሚወጡና እንደሚወርዱ አያውቁም፡፡ ዮሐንስ ሐፂር የሰፋውን ስፌት ገበያ ላይ ለመሸጥ ተቀምጦ እያለ በተመስጦ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን እንደዚሁም ሌሎች መላእክትን በየመዓርጋቸው እያየ ያደንቅ ነበር፡፡ ስፌቱን የሚገዛ ሰው ቁሞ ‹‹እንቅቡ ዋጋው ስንት ነው?›› ብሎ ሲጠይቀው እርሱ የሚያየውን የሚያይ መስሎት ‹‹ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል ሚካኤል፤ ይበልጣል ወይስ ገብርኤል?›› ብሎ በአንክሮ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ‹‹ይኼስ እብድ ነው›› ብሎ ትቶት ሔዷል፡፡

፪ኛ መዓርገ ልባዌ

መዓርገ ልባዌ፣ ማስተዋል፤ ልብ ማድረግ፤ አሰሙኝ እንጂ ስሙኝ አለማለት፤ ልማር እንጂ ላስተምር አለማለት፤ የተነገረው ትንቢትና ተግሣፅ ምዕዳን ዂሉ የራሱ እንደ ኾኑ መገመት፤ መመርመር፤ ዓይነ ሥጋን ከመጽሐፍ፣ ከሥነ ፍጥረት፣ ዓይነ ነፍስን ከምሥጢር ማዋል ነው፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን ቸርነት ማድነቅ፣ ለሰው ልጅ ያደረገዉን ውለታ ማሰላሰል፣ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከሰው መወለዱን፣ በገዳም መጾሙን፣ መገረፉን፣ ሥጋውን መቍረሱን፣ ደሙን ማፍሰሱን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን፣ መነሣቱን፣ እያሰቡ ልብን በፍቅረ እግዚአብሔር፤ አንደበትን በመንፈሳዊ ሕይወት መስበር፤ ዓላማን በገጸ መስቀል (ትዕግሥት) መትከል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

፫ኛ መዓርገ ጣዕመ ዝማሬ

ከዚህ ደረጃ ሲደረስ አንደበትን ከንባብ፣ ልቡናን ከምሥጢር ማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ አንደበታቸው ዝም ቢልም በልባቸው ግን ዝም አይሉም፡፡ ከአፍ እስትንፋስ፣ ከአፋፍ ላይ ነፋስ እንደማይለይ ዂሉ ቅዱሳንም ከአንደበታቸው ትዕግሥት፣ ከእጃቸው ምጽዋት፣ ከልቡናቸው ትሕትና፣ ከሰውነታቸው ንጽሕና አይለይም፡፡ የሚጸልዩትና የሚያነቡት ቃል ዂሉ ምሥጢሩ እየገባቸው ስለሚያደርጉት አይሰለቻቸውም፡፡ ከዚህ መዓርግ የደረሰ አንድ ባሕታዊ ለብዙ ዘመናት ‹‹አቡነ ዘበሰማያት›› እያለ ብቻ ሲጸልይ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ‹‹‹ይትቀደስ ስምከ› በል እንጂ›› ቢለው ‹‹ኧረ ጌታዬ፥ እኔስ ‹አቡነ ዘበሰማያት› የሚለው ኃይለ ቃል ምሥጢሩና ጣዕሙ በአፌ እንደ ጨው እየሟሟ አልጠገበኝ ብሏል፤ እንዴት አድርጌ ወደ ፊት ልሒድ?›› ብሎታል፡፡

ለ. የንጽሐ ነፍስ መዓርጋት

፩ኛ መዓርገ አንብዕ

ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ (እግዚአብሔር) ለሰው ልጅ ያደረገውን ፍቅር፣ እስከ ሞትና መቃብር የተጓዘውን የመከራ ጉዞ እያሰቡ በአንጻሩም ምረረ ገሃነመ እሳትን ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን እያሰላሰሉ ውሉደ አዳም ይህን ዂሉ መከራ ባለመገንዘብ ወደ ሰፊው የፈቃደ ሥጋ መንገድ ሲጓዝ በማየታቸው ያለቅሳሉ፡፡ ያለምንም መሳቀቅ ሲያለቅሱ እንባቸው እንደ ምንጭ ይፈሳል፤ እንደ ሰን ውኃ ይወርዳል፡፡ ሰዎች ለዚህ ዓለም ድሎት ብለው የሚያለቅሱት ልቅሶ ፊትን ያንጣጣል፤ ዓይንን ያመልጣል፡፡ የቅዱሳን ልቅሶ ግን ፊትን ያበራል፤ ኀጢአትን ያስወግዳል፡፡ እርጥብ እንጨት ከእሳት ጋር በተያያዘ ጊዜ እንጨቱ ከነበልባለ እሳት ሲዋሐድ እንጨቱ እርጥብነቱን ትቶ ውኃውን በአረፋ መልክ እያስወገድ ይነዳል፡፡ ቅዱሳንም በግብር (በሥራ) ከመለኮት ጋር ሲዋሐዱ የዚህ ዓለም ምስቅልቅል ሥራ በሰማያዊ የረጋ ሕይወት ተለውጦ አሠራራቸው፣ አካሔዳቸው ፍጹም፤ ሕይወታቸው መልአካዊ ይኾናል፡፡

፪ኛ መዓርገ ኵነኔ

ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ላይ ሲደርሱ ሥጋዊ ፈቃድ ዂሉ ለነፍስ ፈቃድ ይገዛል፡፡ ነፍስ በሥጋ ባሕርያት ላይ ትሠለጥናለች፡፡ ምድራዊ (ሥጋዊ) ምኞት ዂሉ ይጠፋና መንፈሳዊ (ነፍሳዊ) ተግባር ቦታውን ይወርሳል፡፡ ያለምንም ማወላወል መንፈሳዊ ተግባር ዂሉ ይከናወናል፡፡

፫ኛ መዓርገ ፍቅር

ቅዱሳን ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ እንደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ዂሉን አስተካክለው ይወዳሉ፡፡ አማኒ፣ መናፍቅ፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ፣ ዘመድ፣ ባዕድ፣ ታላቅ፣ ታናሽ፣ መሐይም፣ መምህር፣ ሳይሉ ዂሉንም አስተካክለው በመውደድ የመፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ልጆች መኾናቸውን ይገልጻሉ፡፡

፬ኛ ማዕረገ ሑሰት

ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ላይ ሲደርሱ ባሉበት ኾነው ዂሉን ማየትና መረዳት ይችላሉ፡፡ ጠፈር ሳይከለክላቸው ርቀት ሳያግዳቸው ዂሉን በዂሉ ይመለከታሉ፡፡ 

ሐ. የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት

፩ኛ ማዕረገ ንጻሬ መላእክት

ከዚህ ማዕረግ ሲደርሱ መላእክትን ለአገልግሎት ሲወጡ ሲወርዱ ማየት፤ ተልእኳቸውን ያለ ምንም አስተርጓሚ መረዳት፤ ማነጋገርና ማማከር የመሳሰሉትን ዂሉ መፈጸም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ መልአኩን ዐሥር ዓመት እንዳቆመው እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ማለት ነው፡፡

፪ኛ መዓርገ ተሰጥሞ

ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ በባሕረ ብርሃን መዋኘት፣ ባሉበት ኾነው ወደ ላይም ወደ ታችም መመልከት ይቻላቸዋል፡፡

፫ኛ መዓርገ ከዊነ እሳት (ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ)

መዓርገ ከዊነ እሳት በሌላ አጠራር ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ይባላል፡፡ ይኸውም ሥላሴን በዓይነ ሥጋ ለማየት የሚቻልበት መዓርግ ነው፡፡ ቅዱሳን ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር ኾነው፣ ረቀው እግዚአብሔርን ማመስገን ይቻላቸዋል፡፡ የለበሱትን ሥጋ ለብቻቸው ለይተው ማየት፤ በአካለ ነፍስ ሰማየ ሰማያትን መጐብኝት፤ ገነት ውስጥ መግባት ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ኩኑ ቅዱሳነ እስመ ቅዱስ አነ›› (ዘሌ. ፲፱፥፪) ተብሎ እንደ ተጻፈው፣ ቅዱሳን የቅዱስ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸውና ሕይወታቸው የቅድስና ነው፡፡ ዐሥሩ የቅዱሳን መዓርጋት የሚባሉትም ከላይ የዘረዘርናቸው ናቸው (ዮሐ. ፩፥፵፤ ፪ኛ ጴጥ. ፩፥፬-፲)፡፡ እነዚህም የዐሠርቱ ትእዛዛት ምሳሌዎች ናቸው (ዘፀ. ፳፥፫-፲፯፤ ዘሌ. ፲፱፥፲፰)፡፡ አንድም የዐሥሩ ብፁዓን ምሳሌዎች ናቸው (ማቴ. ፭፥፫-፲፪፤ ዮሐ. ፲፫፥፫፯)፡፡ የቅዱሳን በረከት አይለየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡