“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፤ ሠላም እምይዕዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሐ ወሠላም፡፡”

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ሠላም ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ” ይህ ቃል የትንሣኤው የምሥራች ለምእመናን የሚታወቅበት ነው የሚቀድስ ካህን፣ ሰባኪ በዘመነ ትንሣኤ ከስብከቱ አስቀድሞ በዚህ ቃል የክርስቶስን መነሣት ያውጃል፡፡ የሚቀድሰው ካህንም በኪዳን ጊዜ ህዝቡን ከመባረኩ አስቀድሞ ይህንኑ ቃል ይናገራል ሰላምታ የሚቀባበሉ ምእመናንም ሰላምታ ከመስጠት አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ከጥንት በነቢያት የተነገረ ኋላም እርሱ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከመሞቱ አስቀድሞ ያስተማረው ደግሞም በመነሣት የገለጠው ሐዋርያትም በግልጥ ለዓለም የመሰከሩት ነው፡፡

ትንሣኤ በትንቢተ ነቢያት

“እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ” “እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላው መታ” መዝ.77፥6 “እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር አሥነስቶኛልና ተነሣሁ” መዝ.3፥5 “እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ ይላል መድኀኒት አደርጋለሁ

ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ የክርስቶስን ከሙታን መነሣት ተናግሯል፡፡ እርሱን መሰል ነቢያት ክርስቶስ እንዲሞት በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ ገልጸዋል፡፡ ምሳሌ ተመስሏል፤ ትንቢትም ተነግሯል፤ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ እንደ አደረ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ እንደሚነሣ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ወልድ ተናግሯል፡፡ ዮና.2፥1 ማቴ.12፥4ዐ ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕ “ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፡፡ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል በፊቱም በሕይወት እንኖራለን” ሆሴ.6፥2 ብሎ የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን፣ ሕይወታችን መሆኑን ገልጾ ተናግሮታል፡፡ ሆሴዕ በተጨማሪም “ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ /መቃብር/ ድል መንሳትህ ወዴት አለ?” ሆሴ.13፥14 ብሎ ሞት እና መቃብር ሥልጣናቸው እንደተሻረ ይዘው ማስቀረታቸው እንደቀረ በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ትንሣኤ እንደተገለጸ ይነግረናል “ልጄ ሆይ ከመሰማሪያህ /ከመቃብር/ ወጣህ እንደ አንበሳ ተኛህ አንቀላፋህም እንደ አንበሳ ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም” ዘፍ.49፥9 ከላይ በተመለከትነው ጥቅስ የሚቀሰቅስህ የለም የሚለው ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አስነሽ ሳይሻ የተነሣ መሆኑን ይነግረናል ይህንም ክርስቶስ በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡፡ “እንደገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና ከእኔ ማንም አይወስዳትም ነገር ግን እኔ በፍቃዴ እሰጣታለሁ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና” ዮሐ.10፥17 ይህ የሚያስረዳን ክርስቶስ በፈቃዱ ለዓለም ቤዛ ሆኖ እንደ ሞተ በሥልጣኑ እንደተነሣ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በሐዲስ ኪዳን

አራቱም ወንጌላውያን ትንሣኤውን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በወንጌል ጽፈውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ 28፥1-16 በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዷልና ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ” ይላል በዕለተ ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማየት መላእክት እንዲሁም ቅዱሳት አንስት ተገኝተዋል ሲወለድ የመወለዱን ዜና ለዕረኞች የተናገሩ መላእክት በትንሣኤው ዕለትም ዜና ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት ለመንገር በመቃብሩ አካባቢ ተገኝተው የትንሣኤው ምስክሮች ሆነዋል፡፡
“ወእምግርማሁ ተሀውኩ ወኰኑ ከመ አብድንት እለ የአቅቡ መቃብረ “እርሱን ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ እንደ በድንም ሆኑ” ማቴ.28፥4 መልአኩም መልሶ ሴቶችን እንዲህ አላቸው “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና በዚህ የለም እርሱ እንደተናገረው ተነሥቶአል፡፡ ነገር ግን ኑና የተቀበረበትን ቦታ እዩ ፈጥናችሁም ሂዱ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብሎ የትንሣኤውን የምስራች ለሴቶች መግለጡን ጽፎአል፡፡

ቅዱስ ማርቆስም በምዕራፍ 16፥1-16 ትንሣኤውን አስመልክቶ ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረውን መሰል የትንሣኤ መልእክት ሲናገር ቅዱስ ሉቃስ በምዕራፍ 24፥1-24 ዜና ትንሣኤውን ጽፎልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌል አጻጻፍ ስልቱ ከሦስቱ ወንገላውያን ረቀቅ ያለ ስልት ያለው ቢሆንም ትንሣኤው በመመስከር ከሦስት ወንጌላውያን ጋር ተባብሯል፡፡ ዮሐ.20፥1 ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ወደመቃብሩ ገስግሰው በመሄድ ትንሣኤውን ለማየት እንደበቁ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራቹን እንደተናገሩ ዘግቦልናል፡፡ ከሦስቱ ወንጌላውያን በተለየ መልኩ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በዝግ ደጅ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሉበት መግባቱን ትንሣኤው እንደገለጠላቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ የሰላም አምላክ ከሀዘናቸው እንዲጽናኑ ፍርሀታቸውን አርቆ አይዞአችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ እጄን እግሬን እዩ በማለት ፍጹም ፍቅሩን ገልጾላቸዋል፡፡

ትንሣኤው ምትሐት አለመሆኑን ይገልጥላቸውም ዘንድ “ደቂቅየ ቦኑ ብክሙ ዘንበልዕ” ጥቂት የሚበላ አላችሁን? ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በሕቱም መቃብር መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል የተፈጸመ ኀይሉን የገለጠበት ነው ጌታ ባረገ በስምንት አመት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስም ትንሣኤውን ሐዋርያትን መስሎ መስክሮአል “ስለ ኃጢአታችን የተሰቀለውን ሊያስነሳንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ባስነሣው ስለምናምን ስለ እኛም ነው እንጂ” ሮሜ. 4፥25 በዚህ መልእክቱ ትንሣኤው ለእኛም ትንሣኤያችን መሆኑን ይነግረናል ትንሣኤው ለእኛ ሕይወት መሆኑንም ጭምር ሲነግረን “እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን” ሮሜ.6፥4 እንግዲህ በሞቱን ሞትን እንደሻረ በትንሣኤው ትንሣኤያችን ያበሠረ መሆኑን ደግሞም የትንሣኤያችን በኩር ጀማሪ እንደሆነ እኛ በሞቱ ብንመስለው የትንሣኤ ተካፋዮች መሆናችንን ያሳየናል፡፡

ጌታችን በአምስት ነገር በኩራችን መሆኑን መጻሕፍት ይነግሩናል
  1. በጥንት ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ኖሮ እኛን ፈጥሮ ለማስገኘት በኩራችን ነው፡፡
  2. በተቀድሶ/በመመስገን/ በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን የጸጋ ምስጋና የሚመሰገኑት እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡
  3. በትንሣኤ በኩራችን ነው፡፡ እርሱን በኩር አድርገን እንነሣለንና “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ” 1ቆሮ.15፥20፡፡
  4. በዕርገት በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን አረጉ መባሉ እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡ “አርገ ከመ ያሌቡ ዕርገተ ጻድቃን ንፁሀን” የንፁሀን ጻድቃንን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ አረገ ቅዳሴ ዩሐንስ ወልደ ነጎድጓድ”
  5. ነፍሳትን ከሲዓል አውጥቶ ምርኮን ማርኮ ገነት መንግሥተ ሰማያት በመግባት በኩራችን ነው፡፡
ስለዚህ በአለ ትንሣኤውን ስናከብር የእኛም ትንሣኤያችን መሆኑን አውቀን ተረድተን ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን መልካም ሥራ በመሥራት መሆን አለበት እኛ ትንሣኤ ልቡና ሳንነሣ በየዓመቱ ትንሣኤን ብናከብር ፈሪሳውያንን ወይም ትንሣኤ የለም ፈርሰን በስብሰን እንቀራለን ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያን መምሰል ይሆናል፡፡
ትንሣኤውን ስናከብር እንዴት ማክበር እንደሚገባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል
ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኛ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ የላይኛውን አስቡ በምድር ያለውንም አይደለም እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ” ቆላ.3፥1-4 የክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤያችን ነው ብለን ለምናምን ሁሉ ከምድራዊ ዐሳብ ነጻ ሆነን ተስፋ የምናደርገው ትንሣኤ እንዳለን በማሰብ ከሞት በኋላ ሕይወት ከትንሣኤም በኋላ የዘለዓለም ሞት መኖሩን ሳንዘነጋ ማክበር እንደሚገባን ይመክረናል፡፡ ላይኛውን የማያስቡ መልካም ሥራ የማይሰሩ ሰዎች ትንሣኤ ምን እንደሚመስል መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡፡ “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ስለዚህ አታድንቁ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ” ዮሐ.5፥28 የትንሣኤያቸው በኩር ክርስቶስን አብነት አድርገው ቃሉን ሰምተው ሕጉን ጠብቀው ትዕዛዙን አክብረው ትንሣኤ ልቡና ተነሥተው የትንሣኤን ዕለት የሚያከብሩ ሥጋውን በልተው ደሙን ጠጥተው በንስሐ ተሸልመው በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢፅ /ወንድምን በመውደድ/ ጸንተው ቢኖሩ ላይኛውን ማሰብ ትንሣኤውን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ የትንሣኤውን ትርጉም አውቀዋልና፡፡ ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግሥቱን እንድንወርስ ስሙን እንድንቀድስ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡
መልካም ትንሣኤ ያድርግልን አሜን፡፡