‹‹ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው›› (ማቴ.፬፥፩)

ዲያቆን መልእኩ ይፍሩ

የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በወንጌል ቅዱስ ማቴዎስ ስለ ጌታችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐቢይ ጾም ሲጽፍ  ‹‹ከዚያ ወዲያ›› በማለት ከጀምረ በኋላ እርሱ ለሰዎች ድኅነት ሲል ለዐርባ ቀንና ሌሊት ያለ መብልና መጠጥ በጾም በምድረ በዳ እንደቆየ ይገልጽልናል፡፡

አስቀድሞ በምዕራፍ ሦስት ላይ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል እንደወረደ እና ከደመናም ‹‹የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው›› እንደተባለ ተናግሯልና ይህ ከሆነ በኋላ ተጠምቆም ከወጣ በኋላ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ወደ ምድረ በዳ መሄዱን ለመናገር ነው። ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹መንፈስ ወሰደው›› ማለቱ መንፈስ ያላት የገዛ ፈቃዱ ናት፤ ‹‹ወሶበ ትሰምዕ እንዘ ይብለከ ወሰዶ ገዳመ ኢትሐሊኬ ከመ ፍጡር ውእቱ አላ መንፈስሰ ሥምረቱ ይእቲ፤ ገዳም ወሰደው ሲል በሰማህ ጊዜ ፍጡር እንደሆነ አታስብ፤ መንፈስ ያለው የገዛ በጎ ፈቃዱ ነው እንጂ›› እንዲል፤ ዳግመኛም መንፈስ ብሎ መንፈስ ቅዱስ የሚል አብነት ያመጣል። ይህስ ሰማዕታትን ለደም ጻድቃንን ለገዳም እንደሚያነሣሣቸው በፈቃድ አንድ መሆናቸውን ለመናገር  እንጂ አነሣሣው ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ማለት ያስፈልጋል። (ማቴ.፬፥፩)

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት በ፲፫ኛው ክፍለ ትምህርት ላይ ጌታችን ይፈተን ዘንድ የፈቀደበትን አመክንዮ እንዲህ ገልጾልናል። ‹‹ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ሁሉን አድርጎ አሳየን። ወደዚያ ምድረ በዳ ሄዶ ይፈተን ዘንድ ጸንቶ ሂዷል። ስለዚህም ከተጠመቀ በኋላ ታላላቅ ፈተናዎችን በጽናት ይቋቋም ዘንድ እንዳለው ለመናገር ነው። ስለዚህ ክንዶች ተሰጠተውሃል፤ ትሰንፍ ዘንድ ሳይሆን ትፈተን ዘንድ ነው እንጂ፤ ስለዚህ ምክንያት ፈጣሪ ፈተናዎቹ በመጡ ጊዜ አልከለከላቸውም ነበር፡፡››

‹‹ወጾመ አርብዓ መዓልተ ወአርብዓ ሌሊተዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ›› (ማቴ ፬፥፪)

አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሣ ጠላት ዲያብሎስ በገነት ድል ስለነሣው መድኅን ዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም በአፍአ በሆነች በገዳም ድል ይነሣለት ዘንድ ወደ ገዳም ሄዶ ተራበለት፤ ተጠማለት፤ በዲያብሎስ ተፈትኖም ጠላቱን ድል ነሣለት፡፡ ሠራዔ ሕግ በመሆኑም ጾምን የመጀመሪያ ሕግ አደረገ። መባልዕት የኃጣውእ መሠረት እንደሆኑ ሁሉ የበጎ ምግባራት የትሩፋት ሁሉ መሠረት ጾም ናትና። ‹‹እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ አንብዕ ወጥንተ ኲሉ ገድል ሠናይት፤ የጸሎት እናት እና የአርምሞ እኅት የእንባም ምንጭ የሆነች የበጎ ተጋድሎ ሁሉ መሠረት ናት›› እንዲል፤ (ማር ይስሐቅ)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ በዳ የሄደበት ሌላ ምክንያትም ነበረው፤ የመነኰሳት እንዲሁም የባሕታውያን ተጋድሎአቸው ከዚህ ዓለም በአፍአ በሆነ በገዳም በበረሓ ነውና ተጋድሎአቸውን ይባርክላቸው ዘንድ ነው። ዐርባ ቀን መጾሙም አስቀድመው አበው ነቢያት ዐርባ ቀን ጹመው ስለነበር ከዚያ ቢያተርፍ ወይም ቢያጎድል አይሁድ ምክንያት ፈላጊዎች በመሆናቸው ደገኛይቱን ሕገ ወንጌልን ከመቀበል ወደ ኋላ ባሉ ነበር። ዛሬ እባብ አካሉ የደገደገበት እንደሆነ ዐርባ ቀን ከምግብ ተከልክሎ ይሰነብታል። ከዚያም በስቁረተ ዕፅ(በእንጨት ቀዳዳ)በስቁረተ እብንም ቢሉ (በደንጊያ ቀዳዳ) አልፎ ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል፤ ይታደሳል። እናንተም ዐርባ ብትጾሙ ተሐድሶተ ነፍስን ታገኛላችሁ ለማለት ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ። ፍጻሜው ግን አዳም በዐርባ ቀኑ ያገኛትን ልጅነት አስወስዷት ስለነበር ካሣ መካሱን ለመናገር ነው። ጌታችን እንዲህ ማድረጉ ‹‹ለእኔ ይጥቀመኝ፤ ይበጀኝ›› ብሎ አይደለም። ነገር ግን ለደካማዎቹ ልጆቹ ለእኛ ሠርቶ አብነት ይሆን ዘንድ ነው። ‹‹ከእኔ ተማሩ›› እንዳለን ሁሉ እርሱን አብነት አድርገን ጾሙን በተገባ ክርስቲያናዊ ምግባር ልንጾም ያስፈልገናል። (ማቴ.፲፩፥፳፱)

‹‹ወእምዝ ርኅበከዚህም በኋላ ተራበ›› (ማቴ.፬፥፪)

ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹ዐርባ ሌትና መአልት ከጾመ በኋላ ተራበ›› በማለት የተናገረው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ረኃቡን ቢራብም በበጎ ፍቃዱ በተዋሐደው ሥጋ ነው። እርሱ አምስት ሺህ ሕዝብ የመገበ በብሉይ ለእስራኤል ዘሥጋ መናን ከሠማይ ያወረደና የመገበ፣ አዕዋፍን ሳይዘሩ ሳያጭዱ ሳያከማቹ እርሱ አኃዜ ኲሉ የሚመግባቸው ለሁሉ ፍጥረት አስተካክሎ የሚመግብ እርሱ አኃዜ ዓለማት በዕራሁ እንደምን ተራበ ለዚህስ አንክሮ በልባዎ ይገባል።

‹‹ወቀርበ ዘያሜክሮየሚፈትነውም ቀረበው›› (ማቴ.፬፥፫)

ጠላት ዲያብሎስ ጌታችንን ሊፈትነው ወደ እርሱ ሊቀርብ የቻለው ጾም እርሱን ክፉኛ የምታርቀው ሰይፍ እሳት፣ የምትከለክለው አጥር ቅጽር ስለሆነች ነው፤ ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ተናገሯል። ቀድሞ በጾሙ ጊዜ ወደ እርሱ ባለመቅረቡ ጾም እንዴት ፍቱን የጾር መድኃኒት እንደሆነ ከዚህ ላይ መረዳት ያስፈልጋል። በረኃቡ ጊዜ ዐውቆ ሊቀርበው የቻለው ተራብሁ ሲል ቢሰማው ፍሬ ሲሻ ቢመለከተው ገጹን አጸውልጎ ቢታየው እንደተራበ ተረድቶ ቀረበው።  ጌታም ይህን ትምህርት እንድንወስድ እና እንድናስተውል ተራበ። ሰይጣንም ወደርሱ ቀርቦ ‹‹እመሰ ወልደ እግዚአብሔር አንተ በል ከመ እላ አዕባን ኅብስተ ይኩና፤ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ደንጊያዎች እንጀራ ይሁኑ ብለህ እዘዝ›› አለው፡፡ ሰይጣን ይህን ፈተና ሲያመጣ አስቀድሞ ትርጓሜ ወንጌሉ እንደሚለን የቀረበው በተቀደደ ስልቻ ሁለት ትኩስ ዳቦ አስመስሎ ደንጊያዎችን ይዞ ነበር። የጠየቀውም ‹‹እሺ›› ብሎ ቢያደርግ ‹‹የሰይጣን ተአዛዚ አሰኘዋለሁ›› ብሎ ባያደርገው ‹‹ደካማ አሰኘዋለሁ›› በማለት ‹‹አንድም ቢያደርገው ሌላ ጾር እሻበታለሁ(ሌላ ፈተና አመጣበታለሁ) ባያደርገው ድካሙን አይቼ እገባበታለሁ›› ብሎ አስቦ ነበር። ‹‹ዲያብሎስ ከየት አምጥቶ ወልደ እግዚአብሔር ከሆንህ አለው እንዴት ዐወቀ›› ያላችሁ እንደሆን፣ ቀድሞ በባሕረ ዮርዳኖስ እግዚአብሔር አብ በደመና ሁኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር›› ያለውን ሰምቶ ነው። አምላካችን በነቢያቱ ‹‹ይፈትን ልበ ወኩልያተ›› የተባለለት ማእምረ ኅቡዓት ስለሆነ ይህን ሐሳቡን ዐውቆበት የመጣበትን የስስት ፈተና በትዕግሥት እንዲህ በማለት ድል ነሥቶልናል። ‹‹ወአውስአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ጽሑፍ ከመ አኮ በኅብስት ከመ ዘየሐዩ ሰብእ አላ በኲሉ ቃል ዘይወጽእ እም አፉሁ ለእግዚአብሔር፤ እርሱም መልሶ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም‹‹ ተብሎ ተጽፏል ብሎ መለሰለት፡፡›› (ማቴ. ፬፥፬)

እግዚአብሔር ዳን ያለው ይድናል ሙት ያለው ይሞታል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ጌታችን አልዓዛርን ‹‹አልዓዛር ውጣ›› በማለት ዐራት ቀን የሞላውን ሬሳ ቀስቅሷል። ዳግመኛም በስደቱ ጊዜ የዮሴፍ ልጅ ለእመቤታችን የኄሮድስ ወታደሮች እየመጡባቸው እንደሆነ በነገራት ጊዜ እመቤታችን ስትደነግጥ ጌታችን መልሶ ‹‹መልእክቱን መናገርህ በጎ አደረግህ ዳሩ ግን እናቴን ስላስደነገጥሃት እስክመጣ ድረስ ይህን ደንጊያ ተንተርሰህ ቆየኝ›› ብሎት ለፍሱን ከሥጋው ለይቶ አሳርፎታል።

‹‹ወእምዝ ነሥኦ ወወሰዶ ውስተ ቅድስት ሀገርከዚህ በኋላ ወደ ቅድስት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው›› (ማቴ.፬፥፬)

ጌታችን ኢየሱስ የዲያብሎስን ሐሳብ ዐውቆ በበጎ ፈቃዱ ወደ ምድረ በዳ ሄደለት እንጂ እርሱስ ይወስደው ዘንድ እንደምን ይችላል። ፈቃዱን ዐውቆ ሄደለት ለማለት ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹ወወሰዶ›› በማለት በሐሳቡም ‹‹ካህናትን ድል በማልነሣበት በገዳም ቢሆን ድል ነሳኝ እንጂ ካህናትን ድል በምነሣበት በቤተ መቅደስ ቢሆን መች ድል ይነሣኝ ነበር›› ብሎ ማሰቡን ዐውቆ ሄደለት። ‹‹ወዓቀሞ ውስተ ተድባበ ቤተ መቅደስ ወይቤሎ እመሰ አማን ወልደ እግዚአብሔር አንተ ቅንጽ እምዝየ ወተወረው ታሕተ፤ በቤተ መቅደስ ጫፍ አቆመው አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ከዚህ ዝለልና ራስህን ወደታች ተወርውር አለው፡፡›› (ማቴ.፬፥፮)

ሰይጣን በቀደመው ፈተናውም ላይ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ›› በማለት ሲፈትነው እንመለከታለን። ዳግመኛም ሰይጣን ከሰማይ የተሰማውን የአብን እና ከምድር ደግሞ የዮሐንስን ምስክርነት ቢሰማም እንዲሁም ሲራብ በማየቱ ግራ ተጋብቶ ነበር። ቢሆንም ግን ሽንፈትን ስለማይወድ ዳግመኛ ይህን ፈተና ይዞ ቀረበ። ይህንም ፈተና ያመጣው ‹‹ቢሰበር አርፈዋለሁ ባይሰበር ምትሐት ነው አሰኝበታለሁ›› ብሎ ዳግመኛም ቢያደርገው ሌላጾር እሻበታለሁ (አመጣበታሁ) ብሎ ዳግመኛም ቢያደርገው የሰይጣን ተአዛዚ አሰኘዋለሁ፣ ባያደርገው ድካሙን አይቼ እገባበታለሁ›› ብሏል፡፡

ሰይጣን ሁል ጊዜም በአንድ ጾር ሲፈትነን በዚያ ከጣለን በኋላ ዐርፎ እንደማይቀመጥ ከዚህ ማስተዋል ያስፈልጋል። ‹‹የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል›› እንዲሉ አበው በወደቅንበት የመነኰሳት አቅም እንስካናገኝ ድረስ በጾር ላይ ጾር እየደራረበ ያደክመናል። ዲያብሎስ ሁለተኛውን ፈተና ሲያቀርብ ዝም ብሎም ባዶውን አልነበረም። ለእርሱ ያግዘኛል ብሎ ያሰበውን የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር አለቦታውና አለአገባቡ ጠቅሶ ነበር እንጂ። ‹‹እስመ ጽሑፍ ከመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይእቀቡከ በኩሉ ፍናዊከ ወበእደዊሆሙ ያነስኡከ ከመ ኢትትዐቀፍ በዕብን እግረከ፤ መላእክቱን ስለአንተ ያዝዝልሃል በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ እግርህም እንዳይሰናከል በእጆቻቸው ያነሱሃል›› ተብሎ ተጽፏል አለው፡፡ (መዝ.፺(፺፩፥፲፩)

ሁለተኛውን ፈተና ሰይጣን ሲያመጣ ጌታችንን ወደየት እንደወሰደው ማስተዋል ያሻል። ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ቤተ መቅደስ እንደወሰደው ይነግረናል። ሰይጣን እኛን ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ለማስወጣትና ለመጣል ሲፈልግ ክፋትን ብቻ እያሠራ አይደለም፡፡ በጎ ምግባራትን ወደ መሥራት ሊወስደንም ይችላል። ፈተናዎችም ሲመጡብንና ስንደክም በዚያ በደከምንበት ሰዓት እንኳን ንስሓ እንዳንገባ አመክንዮ(ምክንያት)እየደረደረ በጥቅስ እያስደገፈ ሊያደክመን ይቃጣልና በማስተዋል እንራመድ። ‹‹ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ካዕበ ጽሑፍ ከመ ኢታመክሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ፤ ጌታ አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ተጽፏል›› በማለት መለሰ፡፡ (ማቴ.፬፥፯)

በትዕቢት የመጣበትን ፈተና በታላቅ ትሕትና ድል ነሣልን።

ትዕቢት ‹‹ከእኔ በላይ ማን አለ፤ እኔ ነኝ ያለሁት፤ ማን ይልቀኛል›› ማለት ነው። ትዕቢት ብዙዎችን የጠቀመች በመምሰል እያታለለች ከመንግሥተ እግዚአብሔር ተለይተው እንዲጣሉ ያደረገች ጾር ናት። አስቀድሞም ሳጥናኤልን ከቅድስና እንዲወጣ ያደረገችው ታላቅ ጾር ናት። በርግጥም ደግሞ ምንጯ እርሱ ራሱ ነው። ስለዚህም ዕቡየ ልብ፣ የሐሰት አባት ይባላል። በትዕቢት የሚኖሩ እና በትዕቢት የሚናገሩ ከናፍር በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጽሞ የተጠሉ ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ ትሑት ልብን እንጂ በትዕቢት የተመላ ልቡናን አይወድም። ‹‹ጌታ እግዚአብሔር፦ የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖሩባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል›› በማለት የእስራኤልን ትዕቢት መጠየፉን ይነግረናል።(አሞ.፮፥፰)

ከሁሉም በላይ ግን ማንም የማይተካከለው የትሕትና መምህር መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሁሉ በእጁ የተያዘ እርሱ የፍጡራን ሁሉ ፈጣሪ መጋቢ የሚወሳነው የሌለ ሰማይ እና ምድር እንኳን ፍጡራንም ሁሉ ሱራፌልና ኪሩቤል በመንቀጥቀጥና በፍርኃት በፊቱ የሚሰግዱለት አምላካችን ራሱን ከኹሉ ያነሠ ድሃ ባዶ አደረገ። በሁሉ በተናቀው በበረት ተወለደ። እንደ ኃጢአተኛ ተቆጥሮ በዐደባባይ መከራ መስቀልን ተቀበለልን። እንደ ወንጀለኛ ዕርቃኑን በቀራንዮ ተራራ ላይ ሰቀሉት። ቅዱሳኑም ይህን እጹብ ድንቅ የሆነ ትሕትና ተመልክተው በማድነቅ እና በመሰቀቅ ‹‹ኦ ፍቅር ዘመጠነዝ ፍቅር ኦ ትዕግሥት ዘመጠነ ዝ ትዕግሥት ኦ ትሕትና ዘመጠነ ዝ ትሕትና›› ብለው እያለቀሱ አመሰገኑት። (ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ)

ትሕትና በጸሎት ሕይወታችንም ተመስጦን የምትጨምርልን ልቡናችንን ወደ ሰማይ ከፍ የምታደርግልን የፍቅር ልጅ፣ የመታዘዝ እናት የሆነች የመንፈስ ፍሬ ናትና ይህችን ታላቅና ድንቅ ጸጋ መድኃኒታችን በቸርነቱ ለሁላችንም ያድለን። የንስሓን ዕንባ ማፍለቅና ከልብ በማልቀስ እግዚአ ብሔርን መቅረብ እንችል ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ። ሁልጊዜም ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን እንጸልይ እናስተውል። ‹‹እስመ በትሕትና ይትረከብ ልዕልና፤ ልዕልና የሚገኘው በትሕትና ነውና፡፡››

‹‹ወእምዝ ነሥኦ ዲያብሎስ ወአእረጎ ውስተ ደብር ነዋኅከዚህም በኋላ ወደ ረጅም ተራራ አወጣው›› (ማቴ.፬፥፰)

ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን የሰይጣንን የልቡና ፍቃድ ዐውቆ ሄደለት እንጂ እርሱስ የሚወስደው ሁኖ አይደለም። ‹‹ነገሥታትን ድል በማልነሣበት በቤተ መቅደስ ቢሆን ድል ነሣኝ እንጂ ነገሥታትን ድል በምነሣበት በተራራ ቢሆን መች ድል ይነሣኝ ነበር›› ብሎ ማሰቡን ዐውቆ ሄደለት። ‹‹ወአርአዮ መንግሥታተ ኲሉ ዓለም ወኲሉ ክብሮ፤የዓለምን ሁሉ መንግሥታት ክብራቸውንም ሁሉ አሳየው›› ጠጠሩን ወርቅ ብር ቅጠሉን ግምጃ አስመስሎ አሳየው። አንድም ‹‹መንግሥታተ ኲሉ ዓለም›› ግዛቱን ሁሉ አሳየው ‹‹ወኲሎ ክብሮ›› እንስሳት አራዊቱን ፈረስ በቅሎ ሠራዊት አስመስሎ አሳየው። ሰይጣን ምንጊዜም ቢሆን ሐሰተኛና የሌለውን አለኝ እያለ የሚያታልል አታላይ ነው።  ሰይጣን የቱን ያህል ደፋር እንደሆነ እናስተውል። ሠራዔ ኲሉ የሆነውን አምላክ ስገድልኝና ይህን ልስጠህ አለው። እንደምን ያለ ድፍረትና ትዕቢት ነው። መጽሐፈ አክሲማሮስ ይህን የሰይጣንን ትዕቢትና ድፍረት ሲነግረን ‹‹መላእክት ሲያመሰግኑ እርሱ ዝም አለ አያመሰግንም። መላእክትም ምነው አታመሰግንም?‹‹ አሉት እርሱም ደፋር ነውና ‹‹ምን አደረገልኝ ብዬ አመሰግናለሁ። እናንተ ስታመሰግኑ ዐራተኛ እኔን አድርጋችሁ አመስግኑኝ›› አላቸው።

በአንድ ጊዜም ለእርሱ የወገኑትን መላእክት ከእነርሱ ዐራት እንደኪሩብ መርጦ ‹‹ተሸከሙኝና በሉ ኑ ተነሥተን እግዚአብሔርን እንውጋ‹‹ ብሎ ወደ ሰማይ መውጣት ጀመረ። እግዚአብሔር የልቡን የክፋት ጽናት ተመለከተና ከሰማይ ወደ ሰማይ ዝቅ እያደረገ ቢያወርደው ጽርሐ አርያምም ብትርቀው እርሱ ግን ‹‹እዩ! አምላካችሁ አርያሙን ጠቅልሎ ሸሸ›› ብሎ ተናገረ። ‹‹ወእምዝ ይቤሎ እግዚእ ኢየሱስ ሑር እምኔየ ሰይጣን፤ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ሂድ አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ወግድ አለው፡፡›› ይህ አቡሃ ለሐሰት የሆነው ሰይጣን አሁን የመጣው ለእርሱ በማይገባው በእግዚአብሔር የመለኮታዊ ባሕርዩ ገንዘብ በሆነችው አምልኮት ነውና ‹‹ወግድ›› አለው። ምክንያቱም እንዲህ ባለ አኳኋን እና አነጋገር የሚመጣ ባላጋራ ጽኑዕ ባላጋራ ነውና ጽኑዕ ባላጋራዬ ወግድ ሲለው ነው። ‹‹እምድኅሬየ›› በማለትም ከኔ በኋላዬ በሚነሡ ከምእመናን ወግድላቸው ብሎ ሰደደልን። ‹‹ወእምዝ ኀደጎ ዲያብሎስ፤ ከዚህ በኋላ ተወው፡፡›› (ሎቱ ስብሐት፤ ቁ.፲-፲፩)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን በአፍቅሮ ንዋይ በመጣበት ጊዜ በጸሊአ ንዋይ ድል ነሥቶታል። አፍቅሮ ንዋይ ማለት ገንዘብን አጥብቆ መውደድ ማለት ነው። ገንዘብን ከልክ ባለፈ መጠን መውደድ ለዳግማይ ሞት (ዳግም ሞት) የሚዳርግ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ የብዙዎቹን ተወዳጅ ወንድሞቻችንን ሕይወት ሰይጣን መጫወቻው እያደረገው ያለው በዚህ መንገድ ነው። ገንዘብን እኛ ሠራነው እንጂ እርሱ አልሰራንምና ለመኖር ለቁመተ ሥጋ ስንል እንሥራ እንብላ እንጂ ኑሯችንን ሁሉ ለገንዘብ አሳልፈን አንስጥ። ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ሁልጊዜም በማስተዋል እያሰብን እንጓዝ።

አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም አስጀምሮ ያስጨርሰን፤ ለሁላችንም ቸርነቱን ያብዛልን፤አሜን።