ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጋር የሚጻረር የሥልጣኔ ተጽእኖ

በሕይወት ሳልለው

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርን፤ ጥበብን፤ ጽሕፈትን፤ ሥነ ጥበብንና ኪነ ሕንፃን የምታስተምር፤ አንድነትን፤ ፍቅርን እና መተሳሰብን የምትሰብክና ምእመናን ሰብስባ የምትይዝ የክርስቶስ ቤት ናት፡፡

ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን የሀገር መሪም ነበረች፡፡ ልጆቿንም በሥርዓት ታሳድግና ታስተምር ነበር፡፡ ነገሥታት በቤተ ክርስቲያን ሕግ በሚመሩበት ወቅት ዜጎቿም በሥነ ምግባር የታነፁ ነበሩ፡፡ የአክሱምና የጎንደር ዘመነ መንግሥትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ውጭ ሀገራትም ተስፋፍታለች፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና ትውፊት ያልሆኑ ሥርዓቶች  በተለይም የበዓላት አከባበርና የክርስቲያናዊ አለባበስ ላይ ሥልጣኔ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ለምሳሌ የልደት በዓል አከባበር መቀየር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የምዕራባውያን ተፅእኖ ካሳደረው የአመለካከት ለውጥ የተነሣ ያልተለመዱ ምግባሮችን ከፈረንጆች በመውረስ ከክርስትና ጋር የሚጻረር ሥርዓት መከተል የጀመሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የገና ዛፍ በሚል ስያሜ፤ ፅድ መሰል ሰው ሰራሽ ዛፍ በማስጌጥ አላስፈላጊ ክብር እየሰጡ፤ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ምግባሮችን በመዘንጋት አብዛኛውን ጊዜ ትኩረታቸውን የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ በማድረግ ግለኝነትና እራስ ወዳድነትን በመላበስ ከቤተሰብ ፍቅርና ከቀኖናዊ ሕይወት የራቁ በርካቶች አሉ፡፡ ከገና በዓል አከባባር ጋር ተያይዞም ከምዕራባውያን  የወሰዱትን ልምድ ማለትም፤ የገና አባትን በመምሰልና ለሕፃናት ማጫወቻ በአሻንጉሊት መልክ በመሥራት አላስፈላጊ ወጪ ከማውጣታቸው ባሻገር የእኛን ሥርዓት እንደሚበርዝ ባለማስተዋል የተሳሳተ መንገድ ይከተላሉ፡፡

የአለባበስ ሥርዓትን ስንመለከት ሥነምግባርን የሚገልፅ በመሆኑ ከክርስቲያናዊ አለባበስ ውጪ ከሆነ ሰውነትን የሚያዋርድ ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ በክብሩ በገነት ሲኖር፤ ልብሰ ብርሃንን /የፀጋ ልብሱን/ ሲገፈፍበትና ራቁቱን መሆኑን ሲያውቅ ሰውነቱን ለመሸፈን ቅጠል ለብሷል፡፡ ሥልጣኔ ራቁት የሚያስኬድ ከሆነ የሰውን ልጅ ክብር ይገፋል፡፡ ክርስቲያናዊ አለባበስን የሚጻረር ልብስ፤ (ሴቶች  እኅቶቻችን የተቦጫጨቀ ሱሪ፤ ከጡታቸው በታች የሆነ ልብስ ሲያደርጉ፤ ወንዶች ደግሞ ሱርያቸውን መቀመጫቸው እስኪታይ ድረስ ወደታች በጣም ዝቅ አድርገው) ይለብሳሉ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያንንና ትምህርተ ሃይማኖትን አለማወቅም ጭምር ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ያስተማረችን ሰውነትን የሚሸፍን፤ ረጅም ቀሚስ እና ነጠላ መልበስ ነው፡፡ ሴቶች አንዳንድ ጊዜ በጣም አጭር ነጠላ በመልበስ ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ከግራና ቀኝ ትከሻቸው ላይ ለመልበስ በሚሞክሩ ጊዜ ስለማይበቃቸው ሲጨናነቁ እናያለን፡፡ ወንድ የሴት፤ ሴት ደግሞ የወንድን ልብስ ማድረግ ሕጉ ይከለክላል፤ (ዘዳ ፳፪-፭)፡፡ ካህናትም ይህንን ተግባር ላይ ለማዋል በቤተ ክርስቲያን ከራሳቸው ጀምሮ የአለባበስ ሥርዓትን መጠበቅ፤ ሌሎችንም ማስተማር፤ማሳወቅና መገሰፅ አለባቸው፡፡ ትውልዱ ከግማሽ ወደሙሉ ራቁትነት ከመሻጋገሩ በፊት ማስተማር ይገባል፡፡

የማስተማር ኃላፊነት የአለባቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መሪዎች፤ የቤተ ክርስቲያን  አገልጋዮች እንዲሁም ወላጆችና ቤተስቦቻቸው ናቸው፡፡ በልጆችና ወጣቶች ምግባረ ብልሹነት ተጠያቂ በመሆናቸው መገሰፅ፤ ማስተማርና ትክክለኛውን ሕግ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡

ወደ ቅደስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ለማስቀደስና ጉባኤ ለመካፈል ሲመጡ ክርስቲያናዊ አለባባስ መልበስ እንዳለባቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ካህናቱም ቢሆን ደፍረው አይገስፁም፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳንድ የነፍስ ልጆች የሌላቸው ካህናት እንዲሁም የንስሐ አባት የሌላቸው ክርስቲያኖች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አልቻሉም፡፡ እውነቱን መንገር ግን ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፉ “ሕዝቤ ዕውቀት በማጣቱ ጠፍቷል” ይላል (ሆሳዕ ፬፥፮)፡፡

የአለባበስ ሥርዓትን ለማስተካካል ኃላፊነት ያለባቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ ወላጀችም ጭምር በመሆናቸው ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚፈቅደውን የአለባበስ ሥርዓት ለልጆቻቸው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የመንፈስ ቅዱስ ልጁን ጢሞቴዎስን አርአያ እንዲሆን መክሮታል፤ (፩ኛጢሞ ፬፥፲፪)፡፡