‹‹ከአንተ በፊትም ከአንተ በኋላም የሚመስልህ የለም›› (፩ኛነገ.፫፥፲፪)

ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በምድራዊ አገዛዝና የሥልጣን ዘመን ታሪክ ውስጥ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ያህል ጥበበኛ እንዳልተነሣ የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ምስክር ነው፡፡ ‹‹እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ።ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ፡፡›› (፩ኛነገ.፫፥፲፪-፲፫)

የንጉሥ ሰሎሞን ግዛት እስከ ግብጽ ምድር ዳርቻና ፍልስጤም ይደርስ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል፤ እነርሱም ግብር ያመጡለትና ይገዙለት ነበር፡፡ ‹‹ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ኮር መልካም ዱቄትና ስድሳ ኮር መናኛ ድቄት፥ ከዋላና ከሚዳቋ ከበረሀ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር ዐሥር ፍሪዳዎች፣ ሀያም፣ የተሰማሩ በሬዎች፣ አንድ መቶም በጎች ነበሩት። ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ከወንዙም ወዲህ ባለው ሀገር ሁሉ ላይ ከቲፍሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤ በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር።…ለሰሎሞንም በአርባ ሽህ ጋጥ የሚገቡ የሰረገላ ፈረሶች፣ ዐሥራ ሁለትም ሽህ ፈረሰኞች ነበሩት። እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሰጠው። የሰሎሞንም ጥበብ በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብጽ ጥበብ ሁሉ በለጠ። ከሰውም ሁሉ ይልቅ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ። እርሱም ሦስት ሽህ ምሳሌዎች ተናገረ፤ መኃልዩም ሽህ አምስት ነበረ። ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ ሂሶጵ ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ስለተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።›› (፩ኛነገ.፬፥፳፩-፴፬)

የጠቢቡ ሰሎሞን ጥብብ መደነቅና ተሰሚነትም በሰዎች ዘንድ ብቻ አልነበረም፤ ‹‹አራዊትና ወፎች ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ፣ ቃሉን ይሰሙ፣ ጥበቡንም ያደንቁ፣ ከእርሱ ጋር ይነገጋሩና ወደ ሥፍራቸው ይመለሱ ነበር፡፡›› (ክብር ነገሥት ገጽ ፳)

ከዕለታትም አንዱ ቀን ሁለት ጋለሞታዎች ተጣልተው ወደ ለፍርድ ወደ እርሱ መጡ፤ አንደኛይቱም ሴት ‹‹ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ። እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም። እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች። ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ እነሆ ሞቶ ነበር፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፤ እነሆም የወለድሁት ልጄ አልነበረም›› በማለት ተናገረች። ሁለተኛይቱም ሴት ‹‹ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች።›› ይህችም የሞተው ‹‹የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው›› አለች፤ እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር። በዚያን ጊዜም ንጉሡ ‹‹ይህች ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው›› ትላለች፤ ያችኛይቱም ‹‹አይደለም፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች›› አለ። ከዚያም ‹‹ሰይፍ አምጡልኝ›› አለ፤ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ። ንጉሡም ‹‹ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ›› አለ። ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና ‹‹ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል›› ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን ‹‹ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን›› አለች። ንጉሡም መልሶ ‹‹ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት›› አለ። ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ። (፩ኛነገ.፫፥፲፮-፳፰)

በግዛቱ ሥር ያሉትም ‹‹የምድሩም ሹማምት ወርቅና ብር ወደ ሰሎሞን ያመጡ ነበር።… ከዙፋኑም ጋር ተጋጥመው ወደ ዙፋኑም የሚያስሄዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ የወርቅ ብርኩማም ነበረ፤ በዚህና በዚያም በመቀመጫው አጠገብ ሁለት የክንድ መደገፊያዎች ነበሩበት፤ በመደገፊያዎችም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር። በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። ንጉሡም ሰሎሞን የሚጠጣበት ዕቃ ሁሉ የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር በተባለውም ቤቱ የነበረው ዕቃ ሁሉ ጥሩ ወርቅ ነበረ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ከቶ አይቈጠርም ነበር። ለንጉሡም ከኪራም ባሪያዎች ጋር ወደ ተርሴስ የሚሄዱ መርከቦች ነበሩት፤ በሦስት ዓመትም አንድ ጊዜ የተርሴስ መርከቦች ወርቅና ብር የዝሆንም ጥርስ ዝንጀሮና ዝጕርጕር ወፍም ይዘው ይመጡ ነበር፤ ንጉሡም ሰሎሞን ከምድር ነገሥታት ሁሉ በባለጠግነትና በጥበብ በለጠ፤ የምድርም ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ሊያዩ ይመኙ ነበር። እያንዳንዱም ገጸ በረከቱን፣ የወርቅንና የብርን ዕቃ፣ ልብስንና የጦር መሣሪያን፣ ሽቱውንም፣ ፈረሶችንና በቅሎችን እየያዘ በየዓመቱ ያመጣ ነበር።›› (ዜና መዋዕል ፱፥፲፬-፳፪)

በሀገራችን በኢትዮጵያም ነግሣ የነበረችው ንግሥት ሳባ ከእነዚህ ነገሠታት መካከል ተጠቃሽ ናት፤ እርሷም የንግሡን ጥበብና ዝና ሰምታ በዓይና ለማየትና በጆሮዋ ለመስማት እጅጉን በመጓጓት ወደ ሀገረ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘች መጽሐፈ ክብረ ነግሥት ይጠቅሳል፡፡ የነጋዴዎች አለቃ ከሆነው ከባለሟሏ ታምሪን የጥበቡን ነገር ሰምታ ዝናውንም አድንቃ በአካል ታየው ዘንድ የልቧ መሻት ነበር፤ በዚህም ጊዜ ሕዝቦቿን ሰብስባ እንዲህ አለቻቸው፤ ‹‹ወገኖቼ! ነገሬን አድምጡ፤ እኔ ጥበብ እሻለሁ፤ ልቤም እውቀትን ትፈልጋለች፤ በጥበብም ፍቅር ተነድፌአለሁ፤ በጥበብ ገመዶችም ተይዣለሁ፡፡›› (ክብረ ነገሥት ፳፬)

ነጋዴው ታምሪንም ምኞቷን አሳካላት፤ ለስድስት ወር ያህል ተጉዛ ወደ ጥበበኛው ደረሰች፡፡ ‹‹የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ስም፤ የእግዚአብሔርን ስም በሰማች ጊዜ ሰሎሞንን በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች፤ በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፤ ወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው። ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም፤ የሳባም ንግሥት የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፥ ሠርቶትም የነበረውን ቤት፣ የማዕዱንም መብል፣ የብላቴኖቹንም አቀማመጥ፣ የሎሌዎቹንም አሠራር አለባበሳቸውንም፣ ጠጅ አሳላፊዎቹንም፣ በእግዚአብሔርም ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ባየች ጊዜ ነፍስ አልቀረላትም፤ ንጉሡንም አለችው። ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፥ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል። በፊትህ ሁልጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችህና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች ናቸው። አንተን የወደደ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘላለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ። ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር። ከኦፊርም ወርቅ ያመጡ የኪራም መርከቦች እጅግ ብዙ የሰንደል እንጨትና የከበረ ዕንቍ ከኦፊር አመጡ።…ንጉሡም ሰሎሞን በገዛ እጁ ከሰጣት ሌላ የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ ለሳባ ንግሥት ሰጣት፡፡›› (፩ኛነገ.፲፥፩-፲፫)

ጥበበኛው ንጉሥም የሳባን ንግሥት በልቡ ተመኝቶ ከእርሳም ዘር ለማግኘት ወደደ፤ የእብራውያን፣ የግብጻውያን፣ የከነአንያን፣ የኤዶማውያን፣ የኢዮባውያን፣ የአሞሪፍ፣ የኮርጎ የደማስቆሳውያንና የአርማንያን ቆነጃጅት ሚስቶችን በማግባት እግዚአብሔር ዘርን እንዲሰጠው ይመኝ ነበር፤ ሆኖም ግን ልጅ አልወለደም፡፡ ንግሥቲቱ ወደ ሕዝቦቿ ለመመለስ ወስና መልክእት በላከችበት ጊዜም እንዲህ አላት፤ ‹‹እዚህ ከመጣሽ በኋላ ሕገ መንግሥቱንና ለመንግሥቱ እራት ግብዣ እንደሚደረግ አሕዛብም ለኃጥአን ምሳሌ እንዴት እንደሚሰደዱ ሳታይ ለምን ትሄጃለሽ? ከዚህ ትምህርት ታገኛለሽና በኋላዬ ነይ፡፡ በድንኳኖችም ውስጥ በብርሃኔ ትቀመጫለሽ፡፡ እጨርስልሽማለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱንም ታውቂያለሽ፡፡ ጥበብን ወደሻታልና እስከ መጨረሻው ድረስና ለዘለዓለሙም ከአንቺ ጋር ትኖራለች፡፡ ትንቢት በንግግር ይገለጣልና›› ብሎ ወደ እርሷ መልእክት ላከ፡፡ ንግሥት ሳባም መልእከቱን እንደደረሳት እንዲህ በማለት መሰለች፤ ‹‹እኔ ሰነፍ ሳለሁ ጥበብህን በመከተል ጥበበኛ ሆንኩ፡፡ የተናቅሁም ሳለሁ በልቤ ውስጥ ባለችው በዚህች እምነት ምክንያት ከእስራኤል አምላክ ዘንድ የተመረጥኩ ሆንኩ፡፡ ከእንግዲህስ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ አላመልክም፡፡ ጥበብና ክብርን ትጨምርልኝ ዘንድ ስለወደድከው ግን እንደ ፈቃድህ እመጣለሁ፡፡›› ንጉሡም ይህን ሰምቶ ደስ አለው፡፡ ቤቱንም በምርጥ እቃዎች ካስዋበ በኋላ ማዕድን ከወትሮው በእጥፍ እንዲዘጋጅ አደረገ፡፡ ንግሥት ሳባም በደረሰች ጊዜ በዝግጅቱ ተማረከች፤ ወደ ንጉሡም በታላቅ ብርሃንና ክብር ገባች፡፡ የቤቱ ጣራ ላይም በባህርያቸው እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የሚያበሩ እንቁዎችን በጥበብ አድርጎበት ነበርና የሰሎሞን ቤት በምሽት እንደ ቀን ያበራ ነበር፡፡ (ክብረ ነገሥት ከገጽ ፳፩)

ንግሥቲቱ የተቀመጠችበት ቦታም በትክክል በምትመለከትበትና ሁሉንም በምትረዳበት ከንጉሡ ኋላ ነው፡፡ ባየችውና በሰማችውም ፈጽሞ ትደነቅና የእስራኤልንም አምላክ ታመሰግን ነበር፡፡ የቤተ መንግሥቱን ክብር ታደንቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሷ ሁሉን ብታይም እርሷን ግን ማንም አያያትም ነበር፡፡ የመመልከቻ ሥፍራውንም በግምጃና መጋረጃንም ዘርግቶ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በፈርጥ አድርጎ፣ ሚዓና ሰሊክ የተባሉ ሽቶዎችን ረጭቶና ቅንአትና ስሂናት በተባሉ ሽቶና ዕጣን እንጨቶች አስውቦ ሠርቶት ነበር፡፡ በብልሃትና በጥበብም የተዘጋጀ የአሳና የበርበሬ ዓይነቶችንና የተሞከቱ ዶሮዎችን ትመገበው ዘንድ ለንግሥቲተ ይልክላት ነበር፡፡ የንጉሡ ማዕድ በተፈጸመ ጊዜም መጋቢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ አሳላፊዎቹና አገልጋዮቹ ተመለሱ፡፡ ንጉሡም ተነሥቶ ወደ ንግሥቲቱ ሄደ፡፡ ለብቻቸውም በሆነበት ጊዜ ‹‹እስከ ንጋቱ ድረስ ስለ ፍቅር እዚሁ ተጽናኚ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ትንሿ የሰው ሕግ ብሳሳት በመንገድ ላይ ወደ ድካም፣ ሕመምና ችግር ውስጥ እገባለሁና እንዳትደፍረኝ በአምላክህ በእስራኤል አምላክ ማልልኝ!›› ንጉሡም መለሰ፤ ‹‹እንዳልደፍርሽ እምልልሻለሁ፡፡ ነገር ግን አንቺም በቤተ ውስጥ ያለውን ሁሉ እንዳትደፍሪ ማይልኝ›› አላት፡፡ ንግሥቲቱም ሳቀች፤ ‹‹አንተ ብልህ ሳለህ ስለምን እንደ ሰነፍ ትናገራለህ? እሰርቃለሁ? ወይስ ንጉሡ ያልሰጠኝን የንጉሡን ቤተ እቀማለሁ? ጌታዬ ሆይ! በገንዘብ ምክንያት እዚህ የመጣሁ አይምሰለህ፡፡ መንግሥቱም በንብረት ሃብታም ናት፡፡ ከምሻው ሁሉ የሚጎድለኝ አንዳችም የለም፡፡ ጥበብህን ብቻ በመሻት መጣሁ እንጂ›› አለችው፡፡ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እንዲህ አላት፤ ‹‹በሁለት ሰዎች መካከል እንዳይካካዱ መሐላ ይገባልና ካማልሽኝ አንቺም ደግሞ ማይልኝ። ካላማልሽኝ ግን እኔም አላማልሽም›› አላት፡፡ እርሷ ግን እንዳትደፍረኝ ማልልኝ፤ እኔም ደግሞ ገንዝብህን ላልደፍርህ እምላላሁ›› አለችው፡፡ እርሱም ማለላት። እርሷንም አማላት፡፡ ንጉሡም በአንድ በኩል ወደ መኝታው ወጣ፡፡ ለእርሷም ደግሞ በሌላው በኩል መኝታ አዘጋጀላት፡፡ ከአልጋዮቹ ውስጥም አንዱን ጠርቶ ‹‹ጋን አጥበህ ንግሥቲቱ እያየች ማድጋ ውኃ አስቀምጥበት፡፡ በሩንም ዘግተህ ተኛ›› አለው፡፡ ይህንንም ያለው ንግሥቲቱ በማታውቀው ቋንቋ ነው፡፡ ወጣቱ አገልጋይም እንደታዘዘው አድርጎ ተኛ፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ግን የተኛ ቢመስልም አልተኛም ነበር፡፡ ንግሥት ሳባ ግን ጥቂት ተኛች፤ ውኃን የሚያስጠሙ ምግቦችን በብልሃቱ አብልቷት ስለነበር በነቃች ጊዜ አፏ በጥማት ደረቀ፡፡ እጅግም ተጠማች፡፡ ካየችውም ውኃ ለመጠጣት አሰበች፤ ወደ ንጉሡም በተመለከተች ጊዜ የተኛ መሰላት፤ በእግሯም ድምጽ ሳታሰማ ተነሥታ ወደ ጋኑ ውኃ ሄደች፤ ውኃውንም ለመጠጣት አነሣች፤ እርሱም ውኃውን ገና ሳትጠጣ እጇን ይዞ ‹‹በቤቴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ላለመድፈር የማልሽውን መሐላ ለምን ተላለፍሽ?›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ውኃን መጠጣት መሐላን መተላለፍ ነው?›› በማለት በፍርሃት መለሰች፡፡ ንጉሡም ከሰማይ በታች ከውኃ የሚሻል አይተሻልን?›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ራሴ በድያለሁ፡፡ አንተ ግን ከመሐላህ ንጹህ ነህ፡፡ ይሁንና ለጥማቴ ውኃን እጠጣ ዘንድ ተወኝ›› አለችው፡፡ ንጉሡም እነሆ ካማልሽኝ መሐላ ንጹሕ ነኝ?›› በማለት ጠየቃት፡፡ ንግሥቲቱም ‹‹ከመሐላህ ንጹህ ሁን፡፡ ነገር ግን ከውኃው እንድጠጣ ተወኝ›› አለችው፡፡ ጥበበኛው ንጉሥም ውኃ እንድትጠጣ ተዋት፡፡ ውኃ ከጠጣችም በኋላም ፈቃዱን ፈጸሙ፤ አብረውም ተኙ፡፡ (ክብረ ነገሥት ከገጽ ፳፪-፳፫)

ንጉሡም ከተኛ በኋላ ለንጉሡ የምታበራ ፀሐይ ከሰማይ ወርዳ በእስራኤል ላይ ስታበራ ታየው፡፡ ጥቂት ቆይታም ተነጠቀች፡፡ እስከ ምድረ ኢትዮጵያም በረረች፡፡ እዚያም ከበፊቱ የበለጠ ለዘለዓለሙ አበራች፡፡ ወደ እስራኤል ሀገር ትመለስ እንደሆን ጠበቀ፡፡ እዚያ መቀመጥን ወዳለችና አልተመለሰችም፡፡ ደግሞ ቆይቶ ብርሃን ወጣ፡፡ ከሰማያት ወደ ምድረ በዳ ይሁዳ ወረደ፡፡ ከፊቱም የበለጠ አበራ፡፡ እስራኤልን ግን ከሙቀቱ የተነሣ አጥላሉት፡፡ በብርሃኑም አልሄዱም፡፡ ፀሐዩም እስራኤልንም ችላ አላችው፡፡ እነርሱም በእርሱ ላይ ቀኑ፡፡ በመካከላቸውና በፀሐይም መካከል ሰላም ጠፋ፡፡ ፀሐዩንም ያጠፉት ዘንድ ወደዱ፡፡ መላውንም ዓለም በንውፅውፅታ እና በጉም አጨለሙት፡፡ ደግሞም የማይወጣላቸው መሰላቸው፡፡ ብርሃኑንም አጠፉት፡፡ ከመሬት ላይማ ጣሉት፡፡ ከጨመሩበትም ቦታ ጉድጓዱን ጠበቁ፡፡ እርሱ ግን እነርሱ ባልጠረጠሩበት በኩል ወጣ፡፡ በቅድሚያም ለዓለም ሁሉ ለሁለተኛ ጊዜ ለኢትዮጵያና ለሮም አበራ፡፡ እስራኤላውያንን ግን ፈጽሞ ችላ አላቸው፡፡ በዘለዓለማዊ ዙፋኑም ተቀመጠ፡፡ ንጉሡ ሰሎሞንም ይህን ራእይ ባየ ጊዜ ነፍሱ ደነገጠች፡፡ ሐሳቡም እንደ መብረቅ ተነጠቀች፡፡ ደንግጦም ተነሣ፡፡ ደግሞም ስለ ንግሥቲቱ ተደነቀ፡፡ ኃይሏ ብርቱ ለዛዋም ያማረ በድንግልናዋ ንጽሕት ነበረችና ስድስት ዓመት ነገሠች፡፡ (ክብረ ነገሥት ከገጽ ፳፫-፳፬)

ንግሥቲቱም ‹‹እሄድ ዘንደ ተወኝ›› አለችው፡፡ ወደ ቤቱም ገባ፡፡፡ ለሀገረ ኢትዮጵያም የሚገባውን ኃብትና ክብር ለዓይን ያማረ ጥሩ አልባሳትን ሁሉ ሰጣት፡፡ የግመል ባዝራዎችን፣ የክብር እቃ የተጫኑ ስድስት ሽህ ሰረገላዎችን፣ በአሸዋ ላይ የሚጫኑ ሰረገላዎችን፣ በባህር ላይ የሚንሳፈፉ ሰረገላዎችን፣ በነፋስ ላይ የሚበሩ ሰረገላዎችን እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ጥበብ መጠን ሰጣት፡፡ ንግሥቲቱም ደስ ተሰኘች፡፡ ትሄድም ዘንድ ወጣች፡፡ በብዙ ግርማም ሸኛት፡፡ ለንግሥቲቱም የእጁን ቀለበት አውልቆ ‹‹እንዳትረሽኝ፤ ዘርን ብታገኚ ምልክት ይሆናል፡፡ ወንድ ከሆነ ወደ እኔ ይምጣ፡፡ የእግዚአብሔር ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን›› አላት፡፡ ስለ ሕልሙም ነገራት፡፡ እርሷም ወደ ሀገራ ተመለሰች፡፡ (ክብረ ነገሥት ከገጽ ፳፬)

ንግሥት ሳባም ከእርሱ ከተለየች ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በኋላ ዲሳሪያ ውስጥ ባላ ከተባለ ከተማ ስትደርስ ምጥ ያዛት። ወንድ ልጅንም ወለደች፡፡ ወደ ሀገራም ወስዳ አሳደገችው። ስሙም ‹ምኒልክ› ተባለ፡፡ የንጉሡ ልጅ በአደገ ጊዜም አባቱን ማወቅ እጅጉን በመሻቱ እናቱ ልታግደው አልቻለችም፡፡ ሃያ ሁለት ዓመቱ በሆነው ጊዜም አባቱን ለማየት ወደ እስራኤል ተጓዘ፡፡ ምኒልክም መልኩ እጅጉን አባቱን ስለሚመስል ሕዝቡ ሁሉ እርሱ መስሏቸው ተምታታባቸው፡፡ ንጉሡም ልጁን ባየ ጊዜ እጅጉን ተደሰተ፤ በክብር ተቀበለው፤ ምኒልክም እናቱ የሰጠችውን ምልክት አሳየው፡፡ ንጉሡ ግን መልካቸው መመሳሰሉ ብቻ በቂ ማስረጃ በመሆኑን በፍቅር አቅፎም ሳመው፡፡ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ የወርቅ ግማጃንና የወርቅ ዝናርም አለበሰው፤ በራሱ ላይም ዘውድ፣ በጣቱ ላያ ቀለበትና ለዓይን የሚያጥበረብር የክብር ልብሰ አለበሰው፤ ከእርሱም ጋር በሚታይ ቦታ በዙፋን ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ሰሎሞንም ልጁ ምኒልክ በእስራኤል እንዲነግሥ ቢፈልግም እናቱ ግን በነጋዴው ታምሪን በኩል ቀብቶ፣ ቀድሶና መርቆ በሀገሩ ልጇን እንዲያነግሥላት መልእክት ልካበት ነበር፡፡ ንጉሡ ግን የበኩር ልጁን መልሶ ሊልከው አልፈቀደም፡፡ የጣሙ ልብሶች ይመግበውና ያማሩ ምግቦችን ያለብሰው ነበር፡፡ ልጁ ምኒልክ ግን ወደ ሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ ደጋግሞ ነገረው፡፡ ከምግቦቹና ከአልባሳቱም ይልቅ ሀገሩ ትባረክ ዘንድ የታቦቱን የልብስ ጫፍ እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ ንጉሡም ልጁን እሺ ማሰኘት እንደማይቻለው ባወቀ ጊዜ ከሹማንቶቹ ጋር ተማክሮ ልጁን ቀብቶ ካነገሠው በኋላም የእነርሱንም ልጆች አብሮ ወደ ኢትየጵያ እንዲሄዱ አዘዛቸው፡፡ በዚህም ጠቢቡ ሰሎሞን ሳይወድና ሳይፈቅድ ልጁን አጣ፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፤ የንጉሡ ባለሟል አዛርያስ ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ በነገረው መሠረት ከወንደሞቹ ጋር በመማከር ታቦተ ጽዮን ከመንበረ ክብራ ወስደው በኢትዮጵያ አክሱም ጽዮን አኖሯት፡፡ (ክብረ ነገሥት ገጽ ፵፮)

ንጉሡ ታቦተ ጽዮንንና የበኩር ልጁን በአንድ ጊዜ ሲያጣም መሪር ኀዘን ቢገጥመውም የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ ተረዳ። ከሕጋዊ ሚስቱም የወለደው ኢዮርባም የተባለ የስድስት ዓመት ልጅ ነበረው፡፡ ንጉሡ ለአባቱ ነቢዩ ዳዊት ከቤርሳቤህ የተወለደ የበኩር እንደሆነ ልጅ ሁሉ እርሱም ምኒልክ በሀገሩ እስራኤል ለማንገሥ ቢመኝም ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ሆኖም ግን ጥበበኛው ንጉሥ በ፵ ዓመት በነገሠበት ዘመነ መንግሥት ሁሉ እንደ እርሱ ኃያልና ሕዝቡን በፍቅር የመራ አልተኘም፡፡ በእነዚህም ዘመናት ፴፻ (ሦስት ሽህ) ምሳሌዎችንና አምስት መቶ መዝሙራትን ጽፏል፡፡ በነገሠ በዐራተኛው ዓመትም የእግዚአብሔርን ቤት ካገኘ በኋላ ለዐሥራ አንድ ዓመታት ቤተ መቅዱሱን ገንብቶ ጨርሷል፡፡ ታቦተ ጽዮን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመምጣቷ በፊት በዚያ ትቀመጥ ነበር፡፡ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እያቀረበ አምላኩን ሲያሰገልግል እንደኖረ ታሪኩን የመዘገቡት ቅዱሳት መጻሕፈት ይጠቅሳሉ፤ በመጨረሻም በ፶፪ ዓመቱ በሰላም ዐርፏል፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጎብኘን፤ አሜን!