“ከሁሉ በላይ በምትሆን፤ ሐዋርያት በሰበሰቧት፤ በአንዲት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን”

ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም.


ይህ አንቀጸ ሃይማኖት የጉባኤ ቁስጥንጥንያ አንቀጸ ሃይማኖት ነው፡፡ የእውነተኛዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታወቂያ ትእምርትም ነው፡፡ ይህን አጉድሎ መገኘት የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዐት ማፍረስ ብቻ ሳይሆን እምነትንም እንደማጉደል ይቆጠራል፡፡ እንዲህ ዐይነት ማንነታዊ ተክለ ቁመናን ገንዘብ ያደረገ ግለሰብም ሆነ ማኅበር ራሱን የክርሰቶስ አካልና አባል አድርጎ አለመቀበሉን ያሳየናል፡፡ በክርስቶስ ብቻ አምኖ በግለኝነት መኖር በቂ አይደለም፡፡ የክርስቶስ አካል በሆነችው ሐዋርያት በሰበሰቧት፣ በአንዲት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም አምኖ አባል መሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡

 

ይሁንና ይህን አንቀጸ ሃይማኖት ያለ ዐውዱና ከተሸከመው መልእክት ውጪ በመለጠጥና አዲስ የትርጓሜ ቅርጽ በመስጠት በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ቅላጼና ወዝ “ማኅበራት አያስፈልጉም” የሚል እና ራሱን “ጉባኤ አርድእት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብሎ የሚጠራ የቤተ ክርስቲያናችን ሕመም የሆነ ቡድን ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅናና ይሁንታ ከሰሞኑ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መሽጎና የተለያዩ ስብሰባዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ችለናል፡፡

 

ይህን ተከትሎም ከሰሞኑ የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንም ዓይነት ስብሰባ ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና በግቢ ውስጥ እንዳይካሄድ የሚከለክል ደብዳቤም ለሚመለከታቸው አካላት ማሰራጨቱንም ለማወቅ ችለናል፡፡

 

የዚህ የጥፋት ቡድን ዋነኛ ዓላማም ራሱን የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪ አድርጎ በመሰየም እና በተቆርቋሪነት ሽፋን ሐዋርያት የሰበሰቧትን አንዲት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መከፋፈልና የዚሁ ግብር ተዳባይ የሆኑትን እውነተኛ ማኅበራት ህልውና ማክሰምና ጥብዓት ያላቸውን ብፁዓን አበውንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መገዳደር ነው፡፡

 

እንዲህ ዐይነቱን የጥፋት ዓላማ ያነገበው እና “ማኅበር አያስፈልግም” እያለ ራሱን ወደ ማኅበርነት ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ የሚንሳቀሰው ቡድን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ጥቂት የመምሪያ ሓላፊዎችንንና ሠራተኞችን እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ ግለሰቦችን በመሰብሰብ በመመሥረቻ ሰነዱ ላይ ማስፈረሙንም ከሰነዱ ለማወቅ ችለናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አብዛኞቹ ስብሰባው ላይ በመገኘት የጥፋት ግንባሩ የተደራጀበት መንገድና ዓላማ ለቤተ ክርስቲያን አደጋ እንዳለው አቋማቸውን ገልጠው የወጡ እንዳሉም መገንዘብ ችለናል፡፡

 

የአደራጆቹን ማንነት ስንመለከት ደግሞ ያው መልኩንና ስልቱን በየጊዜው የሚቀያይረው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች መሆናቸውንም አረጋግጠናል፡፡ እየተጓዙበት ያለው የጥፋት መንገድም የተለመደው የተሐድሶ መናፍቃን ስልተ መንገድ ነው፡፡

 

እናም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሁለት ሺሕ ዓመት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ቤተ ክርሰቲያን ትሁን እንጂ መንበሯን ከሊቀ ጵጵስና ወደ ፕትርክና ለማሳደግ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ መራራ ዓመታትን ገፍታለች፡፡ በዚህ ማለፏ ደግሞ ሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበት የአደረጃጀት ችግር እንዳጋጠማትና ልጆቿን ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ ለመሥራት የሚያስችላትን አካሄድ እንዳትጠቀም አድርጓት መቆየቱን በሚገባ እንገነዘባለን፡፡

 

ያለማቋረጥ የተደራረበባት ችግር ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እንዳዳከመውና ሊቃውንቷንም ተጠራጣሪና ተከላካይ ብቻ እንዳደረጋቸው ሁሉ የራሷ ሲኖዶስ ሳይኖራት ለረጅም ዓመታት መምጣቷም አሁን ያሉባት ችግሮች የአሁን ብቻ ላለመሆናቸው ጠቋሚ መሆናቸውንም እንረዳለን፡፡

 

እነዚህን ዘመናትን ተሻግረው የመጡ ችግሮች ደግሞ ገና ለጋ ለሆነውና የሃምሳ ዓመታት ተሞክሮ ላለው ቤተ ክህነት ብቻ ትቶ “ብትችል ተወጣው፣ ባትችል የራስህ ጉዳይ” የሚያሰኝ አለመሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

እንኳን የእኛ ቤተ ክርሰቲያን በጠንካራ ሲኖዶስ በመምራትና በሠለጠኑና በተማሩ አማኞቿ የምትታወቀው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ለተደቀነባት የዓለማዊነትና የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ፈተና፣ የርእይ ብዥታና የአስተዳደር ለውጥ ታላቁን አዎንታዊ ድጋፍ ያገኘችው በዘመኑ በነበረው ሊቀ ሐቢብ ጊዮርጊስ አደራጅነት ከተቋቋሙት ማኅበራት እንደነበረም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

ይህ ሊቅ አሁን ባለው የግብጽ ሲኖዶስም ታላቅ ከበሬታ ያለውና እርሱ ባስጀመረው እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሁኗ የኢስላም ሀገር ግብጽ ላይ ታላቅ ሚና እንድትጫወትና ከዓለም ሁሉ የሚመጡባትን ፈተናዎች ተቋቁማ ብቻ ሳይሆን ድል እያደረገች እንድትጓዝ አስችሏታል፡፡

 

በተሳሳተና በፈጠራ መረጃ የተሳከሩት የዚህ የጥፋት ቡድን አደራጆች ሊረዱት የሚገባው ነጥብ፤ ለጠንካራዋ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራት አስፈላጊነት ይህን ያህል ከሆነና የሶርያና የሕንድ አብያተ ክርስቲያናት ከመቶ ዓመት በፊት ጀምረው ማኅበራትን በዘመናዊ መንገድ እያቋቋሙ ተጠቃሚ ከሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንማ እንዴት አያስፈልጓት? አንድ ብቻ አይደለም ገና ብዙ ማኅበራት ያስፈልጓታል፡፡

 

ማኅበራቱም ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት ለሰበሰቧት፤ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግብ የሚንቀሳቀሱ፣ ተልእኮአቸውና ዓላማቸው ተለይቶ የሚታወቅ፣ መንፈሳዊ ተግባርን ብቻ የሚፈጽሙ፣ የሚናበቡና በስልት ለአንድ ውጤት የሚተጉ ሊሆኑ እንደሚገባም እናምናለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ሰጥታቸው የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትም አስፈላጊነትም የሚነሣው ከዚሁ ነጥብ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትመራበት ቃለ ዓዋዲ የተገለጡትን የወጣቶች ተግባራት መፈጸም እንደተጠበቀ ሆኖ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ያልሸፈናቸውን ክፍተቶች ለመሙላት ከማገዝ አንጻር አይደለም አንድና ሁለት ማኅበራት የሌሎች ተጨማሪ ማኅበራት አስፈላጊነት ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

 

ሐዋርያት የሰበሰቧት አንዲት፣ ቅድስትና ኲላዊት የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን ሦስተኛውን ሺሕ ዘመን እንድትዘልቅ፣ ገዳማትንና አድባራትን የልሂቃን ምንጭ እና የልማት ማእከላት ለማድረግ የሚሠሩ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችንና መንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ዘመናዊ ትምህርትን በመጨመር የሚሰጡ የእውቀት ማእከላት ለማድረግ የሚጥሩ፣ ሁለገብ ዕውቀት ያላቸውና ችግር ፈቺ ካህናትን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ፣ ዘመናዊ አስተዳደርን በቤተ ክህነቱ በመዘርጋት ተየያዥ ችግሮችን ሁሉ ለመፍታትና ግንዛቤው ያደገና በዕውቀት የበለጸገ ምእመን ማፍራት ግባቸው ያደረጉ በርካታ ማኅበራት ለቤተ ክርሰቲያን ያስፈልጓታል እንላለን፡፡

 

በአንጻሩ ደግሞ “ከሁሉም በላይ በምትሆን፤ ሐዋርያት በሰበሰቧት፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን” ሳያምኑ እኲይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ቤተ ክርስቲያኒቷን ጥግ ያደረጉትን እንደ ሰሞኑን የተሐድሶ መናፍቃን መልክ ያሉትን የጥፋት ቡድኖች ደግሞ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በሃይማኖታዊ ጥብዓት የምንታገላቸው መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

 

ብፁዓን አባቶቻችንም ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው በፕሮቴስታንታዊ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና እንዲሁም አቀንቃኝ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ የማያዳግም ውሳኔ ይወስናሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

 

በተለይ ያለ ይሁንታችሁ እና ባለማወቅ የዚሁ የጥፋት ግንባር አባላት ተደርጋችሁ ስማችሁ የተዘረዘረ የቤተ ክርሰቲያናችን ሊቃውንትም ሆነ የመምሪያ ሓላፊዎች ጊዜው ሳይረፍድ ከዚህ የጥፋት ቡድን ራሳችሁን ነጻ በማድረግ ለቤተ ክርስቲያናችሁ ጥብቅና ትቆሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

ምእመናንም በየሰነዶቻቸው “ከሁሉም በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት፤ በአንዲት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” እያሉ ግብራቸው እንደማያምኑ ከገለጠባቸው የጥፋት ቡድኖች ራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁንና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁን ትጠብቁ ዘንድ ጊዜ አሁን ነው እንላለን፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን እንደ መንፈሳዊ ተቋምነቱ፤ አባላቱ ደግሞ እንደ አማኝነታቸው ትናንትም ሆነ ዛሬ እንዲሁም ነገ “ከሁሉ በላይ በምትሆን፤ ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማመን ብቻ ሳይሆን መስዋዕትነት እየከፈሉና የሚከፍሉባት ቤታቸው መሆኗንም ጠንቅቀው እንደሚያውቁ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

ማኅበሩም ሆነ አባላቱ ቤተ ክርስቲያናቸውን በዕውቀታቸውም ሆነ በገንዘባቸው የሚያገለግሉ እንጂ እንደ  ጥፋት ቡድኑ አፈ ቀላጤዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ እየበሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን በገዛ ገንዘቧ ለማፍረስ በመናፍቃን ደጅ የሚጠኑ አለመሆናቸውን እነዚሁ አካላት /እውነቱ እየመረራቸውም ቢሆኑ/ ሊያውቁ ይገባል፡፡

 

እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን አማኞች እንዲድኑባት ያዘጋጀ እግዚአብሔር ነው፡፡ በክርስቶስ መሠረትነት፣ በመንፈስ ቅዱስ አደራጅቶና ቀድሶ እውነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ሠርቷታል፤ አቋቁሟታል፡፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ ዝግጅት ክፍልም ሆነ እንደ አማኝ ከሁሉም በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት፤ በአንዲት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ 19ኛ ዓመት ቁጥር 20/2004 ዓ.ም.