“እግዚአብሔር ኃያል ነኝ ሲል እሳትን ፈጠረ“ (መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ኅዳር ፳፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንዱ እሳት ነው፡፡ የእሳትን አፈጣጠር በተመለከተ ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ሊቀ መዘምራን ዕቁበ ጊዮርጊስ ሲናገሩ “እግዚአብሔር ኃያል ነኝ ሲል እሳትን ፈጠረ“ ይላሉ፡፡ (መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ገጽ ፲፭) አምላካችን እግዚአብሔር እሳትን ያለ ምክንያት አልፈጠረውምና ከእሳት ጋር የተመሰሉትን በጥቂቱ እንናሣ፡-

፩. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ

እግዚአብሔር እጅግ ልዑል ምጡቅና ረቂቅ እንዲሁም የማይመረመር አምላክ ሆኖ ሳለ የሰውን ልጅ ይወዳልና ሰው በሚረዳው መልኩ ራሱን በልዩ ልዩ ምሳሌዎች ገልጧል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ እሳት ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ለእስራኤል ዘሥጋ ሲያስተምራቸው “አምላክህ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት ቀናተኛም አምላክ ነውና” በማለት ነግሮዋቸዋል፡፡ (ዘዳ.፬፥፳፬) ይህ ቃል አምላካችን እግዚአብሔር ራሱን በእሳት መስሎ እንደገለጠ ያስተምረናል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእሳት ተመስሏዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ተብላ በምትጠራው ዕለተ ጰራቅሊጦስም በአምሳለ እሳት ተገልጧዋል፡፡ (ማቴ.፫፥፲፩፣የሐዋ.፪፥፩-፫) በብሉይ ኪዳን “የሚበላ እሳት” የተባለ አምላካችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለምን በእሳት ተመሰለ? ለሚለው ጥያቄ ሊቃውንቱ በትርጓሜያቸው ምክንያቶችን ገልጸውልናል፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹን ለማንሣት፡-

  • እሳት ረቂቅ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ረቂቅ ነው፡፡
  • እሳት በብሉይ ኪዳን ያጠፉ ሰዎች ተቀጥተውበት ነበርና ሰዎች ያንን አይተው እሳት የተፈጠረው ለቁጣ ብቻ ነው እንዳይሉ ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለማስረዳት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ራሱን በአምሳለ እሳት ገለጠ፡፡
  • እሳት ዱር ይገልጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጣል፡፡
  • እሳት ከቡላድ ወይም ከክብሪት ሲወጣ በመጠን ይወጣል፤ ከዚያ በኋላ ግን በማገዶ ያስፋፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ጊዜ ጸጋውን የሚሰጠው በመጠን ነው፤ በኋላ ግን ምግባር እየሠሩ ትሩፋት እያሰፉ ለሚሄዱ ሰዎች ጸጋውን እያበዛ ይሄዳልና፡፡
  • እሳት በመጠን ከሞቁት ሕይወት ጤና ይሆናል፤ መጠን አልፈው ከሞቁት ግን ጥፋትን ያመጣል፤ እግዚአብሔርም በእምነት ሆነው በአንክሮ ከመረመሩት ሕይወት ይሆናል፤ በድፍረት ከመረመሩት ግን ይቀጣልና፡፡ (፩ቆሮ.፪፥፲፪-፳፣ ኢዮ.፲፩፥፬-፰፣ ሮሜ ፲፩፥፴፫)
  • እሳት ውኃ ካልገደበው ያቀረቡለትን ሁሉ ያቃጥላል፤ አምላካችን እግዚአብሔርም ቸርነቱ ምሕረቱ ካልከለከለው ሁሉን ሊያደርግ ሊያጠፋ ይችላልና፡፡
  • እሳት ምግብን ያጣፍጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችንን በጸጋው ያጣፍጣልና፡፡ ሸክላ ሠሪ የሠራችው ሸክላ የነቃባት እንደሆነ እንደገና አፍርሳ በውኃ ለውሳ በእሳት ተኩሳ ትሠራዋለች፤ የነፍስ መታደስም በመንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ (ወንጌል ትርጓሜ ገጽ ፺፮)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም መንፈሳዊ ድርሰቱ የሙሴን ቃል ይዞ “ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚባላ እሳት ነው፡፡ እሳታውያን የሚሆኑ ሱራፌልና ኪሩቤል ሊነኩት የማይቻላቸው በእውነት እሳት ነው” በማለት በአንክሮ ይዘምራል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ገጽ ፻፷፪)

፪. ሃይማኖት     

ሃይማኖት ሃይመነ አመነ ተቀበለ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ማመን መታመንና ጽኑ ተስፋ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኤርም ያስ አስቀድሞ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመንገድ ላይ ቁሙ፤  ተመልከቱም፤ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ፤ በእርስዋም ላይ ሂዱ፤  ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን አንሄድባትም አሉ” በማለት የተናገረውን (ኤር.፮፥፲፮) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሐዲስ ኪዳን “ንቁ በሃይማኖት ቁሙ፤ ጎልምሱ፤ ጠንክሩ፤ ሁሉ በእናንተ ዘንድ በፍቅር ይሁን” ብሎ ተርጉሞታል፡፡ (፩ቆሮ.፲፮፥፲፫)

ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳም “ወዳጆች ሆይ ስለምንካፈለው ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት እንዳስተማረው ሃይማኖት ለመዳናችን የተሰጠን የቅዱሳን መንገድ ነው፡፡ (ይሁዳ ፩፥፫) ይህን ለመዳናችን የተሰጠንን ሃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእሳት መስሎ ሲያስተምር “በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ” ብሎዋል፡፡ (ሉቃ.፲፪፥፵፱) ይህን ቃል ያለ ትርጓሜ ቀጥታ እንውሰደው ብንል እንሳሳታለን፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ሰው የሆነው ከሲኦል እሳት ሊያድነን ነውና፡፡ ታዲያ ምን ማለቱ ነው? ብንል እሳት ያለው እርሱን ፍጹም የባሕርይ አምላክ ፈጥሮ የሚገዛ ጌታ ብላ የምታምን ለቅዱሳን የተሰጠች ሃይማኖትን ነው፡፡ ምድር የተባለም ከምድር አፈር የተገኘ የሰው ልጅ ነው፡፡ “በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ” ማለቱም፡- ምድር በተባለ በልበ ሐዋርያት እንክርዳድ ኃጢአትን የሚያጠፋ እሳት ሃይማኖትን ልጥል መጣሁ፤ እርሷም ከነደደችልኝ ማለት፡- ፍሬ ካፈራችልኝ ምንን እፈልጋለሁ? ማለቱ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በልበ ቅዱሳን ነዶ ፍሬ ያፈራውን ሃይማኖትና ጸጋ እግዚአብሔር በእሳት መስሎ ተናግሯዋል፡፡ (፪ጢሞ.፩፥፮) ቅዱሳን የዚህ ዓለም ዐላውያን ነገሥታት ጣዖታትን ካላመለካችሁ በማለት ያነደዱባቸውን የዚህ ዓለም እሳት በእሳት በተመሰለ ሃይማኖታቸው አጥፍተዋል፡፡ ሐዋርያው ይህን በተመለከተ ነገረ ቅዱሳንን አስፋፍቶ ባስተማረበት የዕብራውያን መልእክቱ ሲያስተምር “እነርሱ (ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎ) በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትንም ኃይል አጠፉ” በማለት ይናገራል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፴፬)

የእግዚአብሔር የቁጣ ቀን

እግዚአብሔር ቸርነቱና ምሕረቱ የበዛ አምላክ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም ቸርነቱ ገዶአቸውና አሸንፎአቸው በማይመለሱት ላይ ግን ቁጣውን ያፈሳል፡፡ በናሆም ትንቢት ይህ የበዛ ቸርነቱም ለማይመለሱትም ያለው ቁጣ ተገልጻል፤ “እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና ቁጣን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፤ እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ ኃይሉም ታላቅ ነው፤ በደለኛውንም ንጹሕ ነህ አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለው” ተብሎ ተገልጦአል፡፡ (ናሆም ፩፥፪-፫) እርሱ ከቁጣው ትዕግሥቱ ከመዓቱ ምሕረቱ ይበልጣል፡፡ ይሁን እንጂ በቸርነቱ ተሸንፈን ክፉ ሥራችንን ትተን ዓመፃችንን አስወግደን ወደ እርሱ በንስሓ ካልተመለስን ቅጣት የሚቀርልን ነገር አይደለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከቱ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፡፡ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ” ይለናል፡፡ (ሮሜ ፲፩፥፳፪)

“ጭከናው በወደቁት ላይ ነው” ማለት ምን ማለት ነው? ያልን እንደሆነ ወድቀው ቸርነቱን ተስፋ አድርገው ምሕረቱን ተመርኩዘው ከውድቀታቸው ከመነሣት ይልቅ ከጀመረ ይጨርሰኝ ካፈርኩም አይመልሰኝ ብለው በኃጢአት ላይ ኃጢአት፤ በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመሩ የሚሄዱትን ሰዎች ነው፡፡ (ኤር.፰፥፬-፰)  ይህ ቁጣውም በእሳት ተመስሏዋል፡፡ ይህንም ነቢዩ ሚልክያስ “እነሆ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም” ይላል፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት ገልጦታል፡፡ (ሚል.፬፥፩)

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም በመዝሙሩ ይህን አስመልክቶ ሲናገር “ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነጻል“ (መዝ.፵፱፥፪) ይላል፡፡ እሳት እግዚአብሔር ንስሓ በማይገቡ እልከኞች ላይ ያለውን ቁጣ የሚያመለክት መሆኑን ይህ የነቢዩ ቃል ያስተምረናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ መምጫ ቀንና ሁኔታው ሲገልጥ “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና” በማለት አስተምሮዋል፡፡ (፩ተሰ.፩፥፯)

አንደበት

እሳትን ስናስታውስና ስንመለከት በዓይነ ኅሊናችን ሊታሰበን የሚገባው ሌላ ጉዳይ የአንደበታችን ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን ሞትና ሕይወት፣ ማዳንና መግደል፣ መስበርና መጠገን በአንደበታችን አለ፡፡ (ምሳሌ ፲፰፥፳) በመሆኑም መጽሐፍ አንደበታችንን እንድንጠብቅ ካስተማረን በኋላ ምክንያቱን ሲነግረን “እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል፡፡ አንደበት እሳት መሆኑንና ክፉ ክፉውን ልብና ቅስም ሰባሪውን ነገር እንዲሁም ዕርግማንን ብቻ የሚናገሩበት ከሆነ ለገሃነም እሳት እንደሚዳርግ አውቀን አንደበታችንን በማስተዋል ልንገራው ይገባናል፡፡

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!