‹‹እግዚአብሔር በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ቅርብ ነው፥ በመንፈስ ትሑታን የሆኑትንም ያድናቸዋል›› (መዝ.፴፫፥፲፰)

በመጽሐፍ ቅዱስ የዋህነት እና ትሕትና ወይንም ገርነት ተመሳሳይ ዓላማ አላቸው፤ እነዚህም የመንፈስ ፍሬን ያስገኛሉ፡፡ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ምጽዋት፥ ቸርነት፥ እምነት፥ ገርነት፥ ንጽሕና ነው›› እንዲል፡፡ (ገላ. ፭፥፳፪)

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፥ የዋህና ጸጥ ያለ መንፈስ ያለው፥ የማይጠፋና የተሰወረ የልብ ሰውነት ይሁንላችሁ›› እንዳለው ሰዎች ሊኖረን ከሚገባው ጠባይዕ አንዱ መሆኑን ከቃሉ እንረዳለን፡፡ የዋህነት ወደ አምላካችን እግዚአብሔር የምንቀርብበት የድኅነት መንገዳችን ነው፡፡

የየዋህነት መገለጫ ጥሩነትና መልካም አሳቢነት ነውና በትሕትና መኖር ወይንም ራስን ዝቅ አድርጎ ለፈጣሪ መገዛትን ያመጣል፡፡ በምድራዊ ሕይወታችንም ራሳችንን ዝቅ በማድረግ እና ከምድራዊ የበላይነት ውድድር በመቆጠብ መኖር ይጠበቅብናል፤ ለሥጋችን ብቻ ሳይሆን ለነፍሳችንም ክብር መስጠት ነውና፡፡ ይህንንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ለጠየቁት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው ካቆመ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹…እንደዚህም ሕፃን ራሱን ዝቅ ያደረገ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ ይህ ነው›› በማለት ገልጾልናል፡፡ (ማቴ. ፲፰፥፬)

ትሑታንና የዋሃን ለሆኑ እንዲሁም ቃሉን ለሚፈጽሙ ጻድቃን እግዚአብሔር በእውነት መንገድ እንደሚመራቸውም ጌታችን በወንጌል አስተምሯል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል›› እንደተባለውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው የድኅነት መንገድ እንደሆነ እንረዳለን፤ እርሱም ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ብሏልና፡፡  ትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ጥበብ እንደሆነ በመጽሐፈ ምሳሌ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹እግዚአብሔርን መፍራት፥ጥበብን ባለጠግነትንና ክብርን፥ ሕይወትንም ትወልዳለች›› በማለት ገልጿል፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥ ፮፣ምሳ. ፳፪፥፬)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ሲያስተምርም ሆነ በእጁ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግ ከትሕትና ጋር ነበር፤ ይህም ለእኛ ትሕትናን ለማስተማር ነው፡፡ ትሕትናና ፍቅርም የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ትሕትና ባለበት ቦታ ፍቅር አለ፤ ሰዎች ትሑታን በሆኑበት ስፍራ ሁሉ በፍቅር መኖር ይቻላል ማለት ነው፡፡

አምላካችን እግዚብአሔር እኛን የፈጠረን ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለመውረስ በመሆኑ በትሕትና ለእርሱ ተገዝተን መኖር አለብን፡፡ ለሌሎች መዳንም ምክያት እንድንሆን በሕይወት ውስጥ የሚገጥሙንን ሰዎች በየዋህነትና በትሕትና መቀበል እንዲሁም አብሮ በፍቅር መኖር አስፈላጊ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይከተሉት ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ መኖርና ማገልገል ያለባቸው በትሕትና መንፈስ መሆን እንዳለበት እንዲህ ሲል ይገልጻል፤ ‹‹ነገር ግን ከእናንተ የሚበልጠው አገልጋይ ይሁናችሁ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፡፡ ራሱንም ዝቅ የሚያደረግ ሁሉ ይከብራልና፡፡ (ማቴ. ፳፫፥፲፩-፲፪)

አምላካችን ያዘዘን እንዲህ ሁኖ ሳለ በዚህ ጊዜ ከፈጣሪያቸው የራቁ ብዙኃን ሰዎች ግን የዋህነትም ሆነ ትሕትና በውስጣቸው ባለመኖሩ ትዕቢት በላያቸው ሰልጥኖባቸዋል፤ ልባቸውም በክፋት ደንድኗል፡፡ ይህም በድፍረት የእግዚአብሔርን ቃል እንዲተላለፉና ኃጢአት አብዝተው እንዲሠሩ ስለሚያደርጋቸው ከእውነተኛ መንገድ የራቁ ከመሆናቸውም በላይ ለሌሎችም ጥፋት መንሥኤ ይሆናሉ፡፡ በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ሲገባ፤ ጥያቄም ሆነ እርዳታ ሲጠየቁ በትሕትና ከመመለስ ይልቅ ክፋትና ጥላቻ በተሞላበት አንደበት ምላሽ ይሰጣሉ፤ በአብዛኛው ጊዜም በጎ ሥራንም ለመፈጸም ፍቃደኛ አይደሉም፡፡

ሰዎች የዋህነት ወይንም ትሕትና ሲጎላቸው ከፍቅር ይልቅ መጥፎነት ያስባሉ፡፡ በቤተሰባዊም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው መከባበር እንዳይኖር፣ መናናቅ እንዲፈጠርና ክፋት እንዲስፋፋ ይጥራሉ፡፡ በዚህም  ፍቅርና ሰላም አጥተው ዘወትር በስጋትና በጥላቻ ስሜት ይኖራሉ ማለት ነው፡፡

ነገር ግን የሰው ልጅ በምድራዊ ጉልበቱ ተመክቶ የኋላኛውን ዓለም ሳያስብ ቢኖርና ለኃጢአቱ ስርየት ሳያገኝ ቢሞት ዘለዓለማዊ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡  ነቢዩ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ቅርብ ነው፥ በመንፈስ ትሑታን የሆኑትንም ያድናቸዋል›› ብሎ በመዝሙሩ እንደነገረን በምድር የሚገጥሙንን መከራና ፈተና ለማለፍ እንዲሁም ድኅነተ ነፍስን ለማግኘት በንስሓ ወደ ፈጣሪ ተመልሰን የዋህነትን ልንለብስ ትሑትም ልንሆን ይገባናል፡፡ (መዝ.፴፫፥፲፰)