እውነት ከመስቀሉ ጋር እየተጓዝን ነውን?

መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ

‹‹ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ.. መስቀል ተሸክሞ ያልተከተለኝ አገልጋዬ ሊሆን አይችልም›› በማለት መምህረ ዓለም ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል በአስተማረው መሠረት፥ በክርስቶስ ክርስቲያን ተሰኘ፡፡

ዛሬ ያለውም ሆነ ወደፊት እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የሚነሣው ትውልድ ሁሉ በየደረጃው ባለበት ሓላፊነት፥ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ሞት ድረስ መስቀሉን ተሸክሞ የማይጓዝ ከሆነ የመምህረ ዓለም ክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለት አይገባውም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡

መምህረ ዓለም ክርስቶስ ‹‹የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድትወርሱ ንስሓ ግቡ፤ እውነተኛውን መንገድ ተከተሉ›› ብሎ ወንጌለ መንግሥትን በማስተማሩ ብቻ አንዳችም ኃጢአት ሳይኖርበት ኃጢአተኞች አይሁድ እንደ ኃጢአተኛ ቆጥረው፥ ለስቅላትና ለሞት አብቅተውታል፡፡ የእርሱን ዓሠረ ጽድቅ በመከተል መከራ መስቀሉን ተሸክመው የተጓዙት ቅዱሳን ሐዋርያትም መምህራቸው ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ መስቀሉን ደረጃ በደረጃ ተቀብለው ነው ያለፉት፡፡ እነ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን የመሳሰሉት ቅዱሳን ሐዋርያት ቁልቁል በመስቀል፥ እነ ቅዱስ ቶማስን የመሳሰሉት ቅዱሳን ሐዋርያት ደግሞ ቆዳቸውን በመገፈፍ፥ ሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት በተለያዩ መንገድ የመስቀሉን ፀዋትወ መከራ በመቀበል፥ ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ነው የክርስትናን ሕይወት ሊያራምዱ የቻሉት፡፡

በአሁኑ ጊዜም የመስቀሉ ፀዋትወ መከራ በየአይሁድ ርዝራዦች በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ይገኛል፡፡ ከ፲፱፻፷፮  ዓ.ም ወዲህ ሳይባንን ባንኛለሁ ብሎ የተነሣውን ትውልድ ፊደል አስቆጥራ፥ አፉን አስፈትታ ከእግዚአብሔር ጋር ያስተዋወቀችውንና ለዘመናዊ ሥልጣኔ ያበቃቻቸውን እናት ቤተ ክርስቲያን ውለታዋን ዘንግቶ የፊውዳሉ ሥርዓት አቀንቃኝ አድርጎ በመፈረጅ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር፤ እህል ላበደረ አፈር›› እንዲሉ፥ ሲገፋትና ሲያንገላታት እስከዚህ ዘመን ድረስ ያደረሳት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ይህም በመሆኑ በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ፥ በሰሜንም ሆነ በደቡብ ከለውጡ ጋር በተያያዘ ሕዝቡ ለመንግሥት የሚያቀርባቸው የተለያዩ ራስን የመቻል ጥያቄዎች ሁሉ መልስ የሚያገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፥ አገልጋዮች ካህናትንና ተከታዮቿ ምእመናንን በመጨፍጨፍ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጸም እየተስተዋለ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፥ በአገልጋዮች ካህናትና በተከታዮቿ ምእመናን በኩል ‹‹ዝም በሉ የእኔን እግር ነው የሚበላው›› እንደተባለው ዓይነት ‹‹ቄሱም ዝም፤ መጽሐፉም ዝም›› ነው፡፡

በምንም ይሁን በምን ችግሩ በተከሰተባቸው አህጉረ ስብከት የተመደቡት የሃይማኖት አባቶችና የበላይ አካላትም፤ ሲሆን ሲሆን አስቀድመው ከቦታው ተገኝተው አቅማቸው የፈቀደውን በመከላከልና በመታገል እነሱም የሰማዕትነቱን ጽዋዕ አብሮ
መጎንጨት ሲገባቸው፥ ካልደፈሩም ወይም ለሥጋቸው ከሳሱም አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ የተጎዱትን ካህናትና ምእመናን መርዳትና ማጽናናት ሲገባቸው፥ የሚደረጉላቸው ርዳታና ማጽናናትም ይህን ያህል አመርቂ አይደሉም፡፡

የመስቀል መገለጫዎች የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ከማያሸንፉት ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት መግጠም ከመሆኑም ባሻገር የአብያተ ክርስቲያናቱን ዐውደ ምሕረት በደን በመሸፈን በምድር ላይ የመጀመሪያውን ሪከርድ ሰባሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች የሰው ልጆች በደን አማካይነት ዝናመ ምሕረቱን፥ እክለ በረከቱን አግኝተው እንዳይበለጽጉ ወይም ለዝንተ ዓለም ከድኅነት አዘቅት እንዳይወጡ ማድረግና በአሁኑ ጊዜም ሕዝቡ በነፍስ ወከፍ ለችግኝ ተከላ የሚያደርገውን ርብርብ መቃወም ይሆናል፡፡

ያም ሆነ ይህ በየምክንያቱ አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ሰውንና እግዚአብሔርን መለያየት፥ የሰው ልጆችን መጉዳትና በጸሎቷና በደን ሽፋኗ ዝናመ ምሕረትን፥ እክለ በረከትን አግኝተው መላው የሰው ዘሮችና ግዑዛን የሆኑት ሥነ ፍጥረቶች ሁሉ እንዲጠቀሙ የምታደርገውን ቤተ ክርስቲያን ጸሎቷን እንድታቋርጥ፥ ምድርም ከደን ተራቁታ ሕይወት አልባ እንድትሆን የሚያደርግና ተፈጥሮንም ጭምር የሚቃወም አውዳሚ ተግባር ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ጠቅላላው ሕዝብ የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ በኅብረት ሊታገለውና ሊኮንነው፥ ብሎም ሊያወግዘው ይገባል፡፡

ቤተ ክርስያናችን በጸሎቷም ሆነ በደን ሽፋኗ ፈጣሪዋን ዘወትር በመማፀን ለአዳም ዘሮች ሁሉ ዝናመ ምሕረትን፣ እክለ በረከትን ስታስገኝ እንደኖረች ማንኛቸውም የሰው ዘሮች ሁሉ ሲመሰክሩት የኖሩት ሐቅ ነው፡፡ በአንድ ዘመን አንድ ሀገር ጎብኝ የውጭ ዜጋ እየተዘዋወረ ሀገር ሲጎበኝ በየተራራው ጥቅጥቅ ያሉትን ደኖች ተመልክቶ ‹‹እነዚህ ደኖች ምንድን ናቸው?›› ብሎ ቢጠይቅ፤ ‹‹የአብያተ ክርስቲያናት አፀዶች ናቸው›› የሚል መልስ በማግኘቱ፥ ‹‹ምድርን በደን ለመሸፈን በየቦታው አብያተ ክርስቲያናትን መትከል ነው መድኃኒቱ›› ብሎ ተናገረ ይባላል፡፡ በአባቶቻችን አባባልም ቢሆን ‹‹በአርኣያ ሥላሴ የተፈጠረው የሰው ልጅ ይቅርና ዛፍ እንኳ የሚጸድቀው ከቤተ ክርስቲያን ተጠግቶ ነው›› የሚል አባባል አለ፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሻሻልም ሆነ በየክልሉ ለሚነሡ እራስን የመቻል ጥያቄ በሚከሰቱ ችግሮች ላይ የፓርቲ አባላትም ሆኑ የተለያዩ ምሁራን ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ገንቢ አሳብና አስተያየት በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃን ለመንግሥት ሲያቀርቡ ይስተዋላል፤ ችግሩ በቶሎ ካልተፈታ ወደፊት በመንግሥትና በሕዝቡ ላይ የከፋ አደጋ እንደሚደርስ እስከ መተንበይም ድረስ አሳብ ያቀርባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንስ በፖለቲካ ጥያቄ መንስኤ በየክልሉ ለሚፈጠረው ግጭት ሁሉ የመጠናቀቂያ ግብአት ስትሆን ግን አገልጋዮቿ ካህናትና ተከታዮቿ ምእመናን ድምፃቸውን ለመንግሥትና ለሰፊው ሕዝብ የማያሰሙት ለምንድን ነው? ከሁሉም በላይ አምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያዎች አብያተ ክርስቲያናት በተቃጠሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚገኙት የሃይማኖት አባቶች፥ ካህናትና ምእመናን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለመንግሥትና ለቅዱስ ሲኖዶስ ለምን አያሰሙም? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስስ አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቶ በመነጋገር ለምን ድምፁን ለሕዝብና ለመንግሥት አያሰማም? ከጥቀምቱና ከግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውጭ በቤተ ክርስቲያን ላይ ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር በአዘቦት ቀንም ቢሆን አስቸኳይ ጉባኤ መጥራት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይፈቀድምን? ይፈቀዳል፡፡

የክርስትናን አሻራ ለማጥፋት ሆነ ተብሎ በሚደረግ ዘመቻ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል በሚፈጠር ግጭት በማሳበብ በአንዳንድ ክልሎች የመስቀሉ መገለጫዎች የሆኑት አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደመራ በእሳት ሲጋዩ፥ ቀሳውስትና ዲያቆናት በቤተ መቅደስ ሲታረዱ፥ ተከታዮች ምእመናንም በዐውደ ምሕረት ሲጨፈጨፉ እየተመለከቱ ዝም ማለት ከአደጋው ፈጻሚዎች ጋር ተባባሪ አያሰኝምን? የእምነቱ ተከታዮችንስ ተስፋ አያስቆርጥምን? በዚህ አያያዝ የክርስትና ሕይወት እንዴት ነው መቀጠል የሚችለው? ከተግባሩ ሳንኖርበት ቆብ ደፍተን፥ አምመንና ጠምጥመን በመታየታችን ብቻ ሓላፊነታችንን መወጣት እንችላለን? አንችልም፡፡

በአጠቃላይ የአይሁድ ርዝራዦች የክርስትናን አሻራ ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚያደርጉት ዘመቻ የመስቀሉ መዘከሪያና መገለጫ የሆኑት አብያተ ክርስቲያናት የመስቀሉ ደመራ ሆነው በየክልሉ ሲቃጠሉ፥ ካህናት በቤተ መቅደስ ሲታረዱ፥ የእምነቱ ተከታዮችም በዐውደ ምሕረት ሲጨፈጨፉ እጅ እግርን አጣጥፎ ዝም ብሎ በመቀመጥ፣ የፊተኞቹ አይሁድ የዓለም ቤዛ ክርስቶስን ሰቅለው ከገደሉት በኋላ በመስቀሉ ተአምራት እንዳይደረግበት ለዘመናት ቀብረው ያስቀመጡትን የጌታችንን መስቀል ንግሥት ዕሌኒ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ በዕጣን ጢስ ጠቋሚነት አስቆፍራ ያወጣችበትን ዕለት በየዓመቱ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን ደመራ እየደመሩ በማቃጠል መስቀሉ የወጣበትን ታሪካዊ የመታሰቢያ ዕለት መዘከሩ ብቻ የክርስቶስን መከራ መስቀል ተሸክሞ ለመጓዝ ግብረ መልስ ሊሆነን ይችላልን? ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት›› እንደተባለው ዓይነት ነገር አይሆንምን?

የፊተኞቹ አይሁድ መስቀሉን ቀበሩት እንጂ አላቃጠሉትም፤ ይህም በመሆኑ ነው ንግሥት ዕሌኒ በኋለኛው ዘመን አስቆፍራ ባስወጣችው ጊዜ እንደ ትንሣኤ ሙታን ወጉ ደርሶት ከመቃብር ሲወጣ ወይም ሲነሣ የዓለም ቤዛ ክርስቶስን በመወከል ሙታንን ሊያስነሣ፥ ድውያንን ሊፈውስ፥ አጋንንትንም ሊያስወጣ የቻለው፡፡ ዛሬ ግን በሀገራችን አብያተ ክርስቲያናትን የሚያቃጥሉ ሙታንን የሚያስነሣውን፥ በሰው ሠራሽ ሕክምና ለመዳን የማይችሉትን ሕሙማንን የሚፈውሰውንና አጋንንትን ሊያስወጣ የሚችለውን የክርስቶስን መስቀል በእሳት የሚያጋዩ፥ ለሀገር ልማትም ሆነ ለሰው ሕይወት ፍጹም ደንታ የሌላቸው ከፊተኞቹ አይሁድ የከፉ አይሁድ ስለተነሡ ቀጣይ ሀገርና ቀጣይ ቤተ ክርስቲያን ሊኖሩ የሚችሉት በምን ሁኔታ ነው?

ያም ሆነ ይህ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሀገራችንን ለዘለቄታው ማዳን የምንችለው እንደ ቀሬናዊው ሰምኦን መስቀሉን ተሸክመን ሰላምን፣ በረከትንና ፈውስን ሊያስገኝልን ከሚችለው ከመስቀሉ ጋር አብረን ስንጓዝ ነውና፤ ከመስቀሉ ጋር እንጓዝ፡፡

ምንጭ፡- ክብረ መስቀል በኢትዮጵያ