“እንስሳትን ጠይቅ ያስተምሩህማል፤ የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል” (ኢዮብ ፲፪፥፯)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ
ጥር ፳፪፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በጻድቁ ኢዮብ መጽሐፍ የተጻፈ ኃይለ ቃል ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በዕለተ ሐሙስ “ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ” በማለት ቃል በተናገረ ጊዜ በልባቸው የሚሳቡ፣ በእግራቸው የሚሽከረከሩ፣ በክንፋቸው የሚበሩ ፍጥረታት ከባሕር ተገኙ፡፡ (ዘፍ.፩፥፳)

በባሕር ከተፈጠሩ ከነዚህ ፍጥረታት የሚበሉና የሚገዙ፣ የማይበሉ የማይገዙም አሉ፡፡ ከባሕር ጸንተው የሚኖሩ አሉ፤ አንድ ጊዜ በየብስ አንድ ጊዜ በባሕር የሚኖሩ አሉ፤ በክንፋቸው በረው ከባሕር ወጥተው የቀሩም አሉ፡፡ (መጽሐፈ ሥነፍጥረት ምስለ አምስቱ አእማደ ምሥጢር፤ ገጽ ፷፤ ሥነ ፍጥረት ክፍል ሦስት ለከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተማሪዎች የተዘጋጀ ገጽ ፵)

የሚበሉና እና የሚገዙ እንስሳት

በዕለተ ሐሙስ ከባሕር ከተገኙት ፍጥረታት ለሰው የሚገዙ ለምግብነትም የሚውሉ እንስሳት አሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው እንደምናገኘውም የተሰነጠቀ ሰኰና ያላቸውን፣ ጥፍራቸው ከሁለት የተከፈለውንና የሚያመሳኩትናን እንስሳ እንድንበላ ታዝዘናል፡፡ እነርሱም በግ፥ ፍየል፥ ዋላ፥ ሚዳቋ፥ የበረሃ ፍየል፥ አጋዘን፥ አጭ፥ በራይሌ፥ ድኵላ ናቸው፡፡ እንዲሁም ክንፍና ቅርፊት ያላቸውንና ንጹሕ የሆኑትን ወፎች ሁሉ እንበላለን፡፡ (ዘዳ.፲፬፥፭-፲፩) እነዚህም ከሰው ልጅ አኗኗር አንፃር ለእግዚአብሔር በፍቅር በትሕትና የሚገዙ የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚያ ሰውን ተላምደው ለሰው እየታዘዙ ለምግብነትም እየዋሉ እንደሚኖሩ ጻድቃንም ለእግዚአብሔር እየታዘዙ ይኖራሉ፡፡

እውነት እግዚአብሔርን አምልከው በእውነተኛ መንገድ ተጉዘው ለእውነትም እስከ ሞት ድረስ ታምነው በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቃን የተባሉ ደገኛ አባቶቻችንና እናቶቻችንም የጽድቃቸው አንዱ መሠረት ለእግዚአብሔር መታዘዝና መገዛታቸው ነው፡፡ መጽሐፍ “ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው” በማለት እንደመሰከረው ጽድቅን ሳይፈጽሙ በአንደበት ብቻ ጻድቅ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ (፩ኛዮሐ.፫፥፯) “መታዘዝ ከመሥዋዕት ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል” እንደተባለው አምላካችንን በመታዘዛችን የምናስደስተውን ያህል በምንም አናስደስተውም፡፡ መታዘዝ የበረከት ምክንያት ዐመፅ (እምቢተኝነት) ደግሞ የርግማን መነሻ ነው፡፡ “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ብታምፁም ግን ሰይፍ ይበላችኋል” እንዲል፡፡ (ኢሳ.፩፥፲፰)

ለእግዚአብሔር የሚታዘዙ ሰዎች መከራና ፈተና ኀዘንና ችግር ቢበዛባቸውም ያለ አንዳች መሳቀቅና መታወክ በደስታ ሆነው የምድርን በረከት ይበላሉ፡፡ ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሰዎች ግን ለጊዜው በምቾት የሚኖሩ ቢመስላቸውም ደስታቸውና ምድራዊ ሐሴታቸው ለጊዜው ነው፡፡ ልበ አምላክ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “በክፉዎች ላይ አትቅና ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና” በማለት መስክሯል፡፡ (መዝ.፴፮፥፩)

ስለሆነም እነዚህ በዕለተ ሐሙስ ተፈጥረው የሚበሉም የሚገዙትም እንስሳት ሰው ለፈጣሪው በመታዘዝ ሊኖር እንደሚገባው ያስተምሩታል፡፡ በመታዘዝ ውስጥ ክብር እንጂ ውርደት፤ ከፍታ እንጂ ዝቅታ የለም፡፡ በመታዘዝ ራስ እንሆናለን እንጂ የበታች አንሆንም፡፡ መታዘዝ የዘለዓለማዊ በረከት ምንጭ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ በኩል ልጆችና ወጣቶችን “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ ይህ የሚገባ ነውና መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” በማለት የመታዘዝ በረከት ታላቅ መሆኑን በእውነት አስተማረን፡፡ (ኤፌ. ፮፥፩)
አብርሃም ልጁን ለፈጣሪው መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ደርሶ በመታዘዙ ክብርን አግኝቷል፡፡ ይስሐቅም እስከ መሞት ደርሶ ለመታዘዝ ፈቃደኛ በመሆኑ ንጉሠ ሰማይ ወምድር አምላካችን “እኔ የይስሐቅ አምላክ ነኝ” ብሎ ራሱን በእርሱ ስም እስከ መግለጥ ደረሰ፡፡ (ዘፍ.፳፰፥፲፫) መታዘዝ በሌለበት የታላላቆች ኀዘን፣ የወላጆች ርግማን ይኖራል፡፡ ስለሆነም ወጣቶች ከፍጥረታት መታዘዝን እንማር፡፡

የማይበሉና የማይገዙ እንስሳት

በዕለተ ሐሙስ ከተፈጠሩት የማይበሉትና የማይገዙት እንስሳት ማለትም ከሚያመሰኩ ወይም ሰኰናቸው የተሰነጠቁትን እንስሳ አንበላም፤ ግመል፥ ጥንቸል፥ ሽኮኮ፣ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭልፊት፥ ጭላት፣ቍራ፣ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል፣ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ እርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ አይበሉም፡፡ (ዘዳ.፲፬፥፲፫-፲፰) ለእግዚአብሔርም ለሰውም አንገዛም እያሉ በትዕቢትና በዓመፅ የሚኖሩ የኃጥኣን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ እንስሳት “የኃጥኣን ምሳሌዎች” ተባሉ እንጂ በራሳቸው ኃጥአን እንዳልተባሉ እናስተውል፡፡ የማይታዘዙ ኃጥኣን ከነዚህ እንስሳት የከፉ ናቸው፡፡ እነርሱ ባለመበላታቸውም ሆነ ባለመገዛታቸው ዕዳ ፍዳ የለባቸውም፤ ኃጥኣን ግን ባለመታዘዛቸው ዕዳ ፍዳን በላያቸው ያከማቻሉ፡ ሐዋርያው “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ

የእግዚአብሔር ቁጣ በሰማይ ይገለጣልና” በማለት እንዳስተማረው፡፡ (ሮሜ ፩፥፲፰)
የማይበሉትና የማይገዙት እንስሳት ለሚበሉትና ለሚገዙት የስጋት ምንጭ እንደሆኑ ኃጥኣንም ለደጋግ ሰዎች የህልውና ስጋቶች ናቸው፡፡ ይህን በተመለከተ ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ የተባሉ ሊቅ ልጃቸውን “ልጄ ሆይ ጠላት በዛብኝ ምቀኛ አሴረብኝ ብለህ አትጨነቅ፡፡ በዓለም የሚኖር ፍጥረት ሁሉ ጠላትና ምቀኛ አለበት እንጂ ባንተ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም ጥቂቱን እጽፍልሃለሁ፡፡ በፍየል ነብር፤ በበግ ተኩላ፤ ባህያ ጅብ፤ በላም አንበሳ፤ በአይጥ ድመት፤ በዶሮ ጭልፊት አለባቸው፡፡ ይህንንም የመሰለ ብዙ አለ፡፡ ሰውም እርስ በርሱ እንደዚህ ነው፡፡” በማለት የመከሩትም ምክር ይህን ያጠነክርልናል፡፡ (ወዳጄ ልቤና ሌሎችም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ገጽ ፺፰)

በዓለም ያለው መገፋፋት፣ ሰብአዊ ቀውስና ትርምስ በዓለም ያለው መገፋፋት፣ ሰብአዊ ቀውስና ትርምስ እንዲሁም ቤተሰባዊ መሸካከር መነሻው እምቢተኝነት ነው፡፡ እነዚህ የማይበሉና የማይገዙ ሆነው የተፈጠሩ እንስሳት አልፎ አልፎም ቢሆን ርኅራኄ ይስተዋልባቸዋል፡፡

ነቢዩ ኤርምያስ በሰቆቃው “ቀበሮች እንኳን ጡቶቻቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎን ጨካኝ ሆነች፡፡” (ሰቆ.ኤር.፬፥፫) ወላጆች ለፈጣሪ ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው ባለመታዘዝ ችግር ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ልጆች “ትምህርታችሁን አጥኑ” ሲባሉ “እምቢ አሻፈረኝ” በማለት ፊደል ላይ ይሸፍታሉ፡፡ “አታምሹ በጊዜ ወደቤታችሁ ግቡ” ሲባሉ “እምቢ” ብለው በማምሸት ለዝሙትና ለሌሎች የችግር መነሻዎች ይዳረጋሉ፡፡ “ክፉ ባልንጀራ ይቅርብሽ ፍጻሜሽ የከፋ ይሆናል” ተብለው ሲመከሩ አይወዱም፡፡ ወደው የሰሙ የተቀበሉ ቢመስሉም ከወላጆቻቸውና ከታላላቆቻቸው ተሰውረው የሚውሉት ግን ከክፉ ሰዎች ጋር ነው፡፡
በዚህም አያሌ ጠባዮችን ከክፉ ሰዎች ወርሰው ለከፋ ነገር ይዳረጋሉ፡፡ ለእግዚአብሔር እንገዛ፤ የወጣትነት ጊዜያችን ፍሬ ያማረ ይሆናልና፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛት ሕጉን ትእዛዙን መጠበቅ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛት እግዚአብሔር ለጥቅማችን “አድርጉ፤ ጠብቁትም” ያለንን ፈቃዱን ጠብቆ መገኘት ነው፡፡ ስለምንጎዳበትም “አታድርጉ” ያለንን ነገር ባለማድረግ ታማኝነታችንን መግለጥ ነው፡፡ አማሌቃውያን በፈጸሙት ግፍ ንስሓ ባለመግባታቸውና በእልህ ጸንተው በመገኘታቸው ምክንያት ሊቀጣቸው ሽቶ ንጉሥ ሳኦልን “ሂደህ ቅጣቸው” ብሎ አዘዘው፡፡ ንጉሥ ሳኦል ግን ወደ አማሌቅ ከወረደ በኋላ የታዘዘውን ቸል ብሎ በገዛ ራሱ መንገድ ተጓዘ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር አዘነበት፡፡ መንግሥቱ ከእርሱ እንደምትወሰድበት ከሹመት እንደሚሻር ከመዓረጉም ዝቅ እንደሚል ነገረው፡፡ “የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ” ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ” እንዲል፤ (፩ኛሳሙ.፲፭፥፲፩) ለእግዚአብሔርና ለሰዎች አለመታዘዝ እንደሚጠፉ እንስሳት መምሰል እንደሆነ ይህ ታሪክ በእውነት ያስተምረናልና ወደ ልቡናችን ተመልሰን መታዘዝን ገንዘብ እናድርግ፡፡

ይቆየን!

ምንጭ፡- ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ ገጽ ፷ ፲፱፻፺፯ ዓም፤ ሥነ ፍጥረት ክፍል ሦስት ለከፍተኛ የመንፈሳዊ ትምህርት ተማሪዎች የተዘጋጀ ገጽ ፵፡- ዲያቆን ከፍያለው ታደሰ ኅዳር ፲፱፻፺፫ ዓ.ም)