‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› (ዘፀ. ፮፥፪)

ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ሰማይና ምድርን፣ መላእክትን፣ ሰውን እንዲሁም ፍጥረታትን በሙሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ ለፍጥረታቱም ህልውናውን እንደብቃታቸው ይገልጻል፤ በጥንተ ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን ለባውያን (አዋቂዎች) አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በሰጣቸው ዕውቀት ተመራምረው ፈጣሪያቸውን ያመልኩት ዘንድ እንዲሁም ከባሕርዩ ፍጹም ርቀት የተነሣ በመካከላቸው ሳለ ተሰወረባቸው፡፡ መላእክትም ተፈጥሮአቸውንና ፈጣሪያቸውን መመርመር ጀመሩ፤ አንዱም ለአንዱ ‹‹አንተ ምንድን ነህ? ከየትስ መጣህ?›› ይባባሉ፣ እርስ በርሳቸውም እየተያዩ በተፈጥሮአቸው ይደነቁ ነበር፡፡ በኋላም ‹‹ማን ፈጠረን? ከየትስ መጣን?›› የሚለው የማኅበረ መላእክት ጥያቄ መበርታቱን የተረዳው ሳጥናኤል ሹመቱ ከሁሉ በላይ ነበርና አሻቅቦ ቢያይ እኔ ነኝ ባይድምጽ አጣ፤ ዝቅ ብሎም ቢያዳምጥ ከእርሱ በክብር ያነሱ መላእክት ይመራመራሉ፤ ለምን እኔ ፈጠርኳችሁ ብዬ ፈጣሪነትን በእጄ አላስገባም ብሎ አሰበ፤ ከዚያም እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ በማለት ተናገረ፡፡ (ዘፍ. ፩፥፩-፴፩፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ ከገጽ ፳፬-፴፫)

በዚህ ጊዜ የመላእክት ማኅበር ታወከ፤ የተጠራጠሩትም ለሦስት ወገን ተከፈሉ፡፡ እኩሉ መላእክት ከዚህ በፊት ፈጠርኳችሁ ብሎ የተነሣ የለምና ‹‹ፈጥሮን ይሆን›› በማለት የተጠራጠሩት ናቸው፡፡ እኩሉ ‹‹አዎን፤ ፈጠረን›› ብለው እንደ ፈጣሪ የተቀበሉት ሲሆኑ እንዲሁም ‹‹ማን ከማን አንሶ? በበላይነትማ ከሆነ እኛም ከበታቻችን ያሉትን ፈጥረናል›› በማለት ተፈጣጠርን ሲሉ በትዕቢት የተናገሩ ናቸው፡፡ በሌላ መልኩ ሦስተኞቹ ደግሞ ‹‹ፈጠረንም፣ አልፈጠረንም›› ሳይሉ ከዚያም ከዚህም ሳይሆኑ ፈዘው የቀሩ ነበሩ፡፡ ከነዚህ የተለዩ በተሰጣቸው አእምሮ ማገናዘብ የቻሉ መላእክት ግን ‹‹በማዕረግስ ከሆነ እኛም መልካችን የሆነ እኛን መሳይ ነህ፡፡ ነገር ግን እኛን መስለሃል ብለን ፈጣሪ አይደለህም በማለት በምቀኝነት አንቃወምህም፤ ጸሓፊ በጸሐፊነቱ፤ ሐናጺም በቤቱ እንዲታወቅ በእውነት አንተም ፈጣሪ ከሆንክ ፈጥረህ አሳየን›› አሉት፡፡  እርሱም እፈጥራለሁ ብሎ ቢነሣ አልተቻለውም፡፡  (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ ገጽ ፴፬)

የዲያብሎስ ሐሰተኝነት በተገለጠ ጊዜ ውሸትና ዐመፃን ባልለመዱ ማኅበረ መላእክት ዘንድ ይህ ነው የማይባል ንጽውጽውታ እና ሁከት ሆነ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹አይዟችሁ! ፈጣሪያችንስ ፈጥሮ አይጥለንምና አምላካችንን እስክናውቀው ባለንበት ጸንተን እንቁም!›› ብሎ ማኅበረ መላእክትን አረጋጋ፡፡  (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ ገጽ ፴፮)

ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ለፍጡራኑ ያዝናልና ፈጽመው እንዳይስቱ በስተ ምስራቅ በኩል ‹‹ለይኩን ብርሃን ማዕከል ጽልመት፤ በጨለማ መካከል ብርሃን ይሁን›› በማለት ራሱን ገለጠላቸው፡፡ ይህም ብርሃን ጥበብና አእምሮ ሆኗቸው መላእክት አምላካቸውን አውቀው አመስግነውታል፡፡  (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ ገጽ ፴፰)

የእግዚአብሔርን አምላክነት በሕገ ልቡና (ባልተጻፈ ሕግ) ዐውቀውና ተረድተው ለአምላካቸውም ተገዝተው የኖሩ እንደ አብርሃም ያሉ ጻድቃን አባቶችም አምላካቸው ተገልጾላቸዋል፡፡ ‹‹ከዚህም በኋላ አብራም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለት፤ አንዲህም አለው፤ “በፊትህ የሄድሁ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ አለው…. ንጹሕም ሁን፤…” አብራምም በግንባሩ ወደቀ›› እንዲል፤ (ዘፍ. ፲፯፥፩)

በኦሪት ዘመን እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነፃ ያወጣቸው ዘንድ የታዘዘው ነቢዩ ሙሴ እግዚአብሔር አምላክ ተገልጦለት እንዲህ ብሎታል፤ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሙሴን ተናገረው፤ አለውም፥  “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡ ለአብርሃምም፥ ለይስሐቅም፥ ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር፡፡”›› (ዘፀ.፮፥፪-፫)

ለእግዚአብሔር አምነውና ታምነው የኖሩ ጻድቃን አባቶችም ለቃሉ ተገዝተው በመኖራቸው ፈጣሪያቸውን እስከማየትና እስከማነጋገር ደርሰዋል፤ ለዚህም ገድላቸው ምስክር ነው፤ እኛም የዚህ ትውልድ ሰዎች ነቢዩ ሙሴ ባስተማረንና እግዚአብሔር አምላክ በራሱ ጣት ጽላቱ ላይ ቀርፆ ባስቀመጠልን የተጻፈ ሕግ (ዐሥርቱ ትእዛዛትን) በማክበርና በመተግበር ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁነን መኖር አለብን፡፡

የእግዚአብሔርን አምላክነት ያልተረዱ ሰዎች ነገር ግን ከልባቸው እርሱን ለማወቅ የሚሹ ደግሞ ፈጣሪያቸውን ያውቁ ዘንድ ተገቢ በመሆኑ ዘወትር በመጸለይ፣ በጾም በስግደት በመትጋት በሕገ እግዚአብሔር መኖር አለባቸው፡፡ ታዋቂና ዝነኛ ከነበሩት ፈላስፎች መካከል እንኳን በምርምራቸው ከፍጥረት ሁሉ በላይ ያለ አንድ ኃይል መኖሩን አረጋግጠዋል፤ ይህንም በታሪክ ያወቅነው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አምላክነት ካወቅንም በኋላ ባሕርያቱን ተረድቶ ለእርሱ መገዛትም ከእኛ ስለሚጠበቅ ይህን ማወቅና መረዳት ያሻል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የሚባል አምላክ የለም፤ ቢኖር የንጹሓንን ወይንም የሕፃናትን ሕይወት እንዲህ ባለ ጊዜ ይታደግ ነበር›› እያሉ ተስፋ ሊያስቆርጡ ከሚዳክሩ ተንኮለኞችና ሴረኞችም በመጠንቀቅ በሃይማኖት ጸንቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡

የእግዚአብሔር ቁጣ በበረታበት በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ደግሞ የእርሱን ቸርነት መማጸን እንጂ አምላክ የሚባል የለም ብሎ ሰበብ በማድረግ፣ እጅጉን ተስፋፍቶ ብዙዎችን የገደለውን በሽታም ሰዎች እንደፈጠሩት በማመን ያለ እግዚአብሔር አጋዥነት በራሳችን መከላከል እንዲሁም ማጥፋት እንደምንችል ማሰብ ለባሰ ጥፋት እየዳረገን በመሆኑ ልናስተውል ይገባል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የምናየው መቅሠፍት ቸነፈር ብቻ ሳይሆን ዕልቂት ነውና፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር ቸር ይቅር ባይ አምላክ ስለሆነ የቀደመ ኃጢአቴን ይቅር አይለኝም ብለን ከመፍራት ይልቅ ከልብ ተጸጽተን ይቅርታ ብንጠይቀው ይሰማናል፤ እርሱ የሚፈልገው ድኅነታችንና በግዛቱ እንድንኖር በመሆኑ ንስሓችንን እንደሚቀበለን በማመን ለኃጢአታችን ሥርየት እንዲሰጠን መማጸን ተገቢ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹የመዳን ቀን አሁን ነው›› ብሎ እንዳስተማረው በንስሓ መመለስ የሚሹትን ኃጥኣን እግዚአብሔር አምላክ ሁሌም እጁን ዘርግቶ ይቀበላል፡፡ በንስሓም ወደ እርሱ ከተመለስን በኋላም ዳግም እንዳንበድል በፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲሁም በሃይማኖት ጸንቶ በመኖርና ዘወትር እርሱን በማመስገን መኖር ያስፈልጋል፡፡ (፪ ቆሮ. ፮፥፪)

እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱን ያብዛልን፤ ከጥፋት ይታደገን፤ በሰላም ከእርሱ ጋር ያኑረን፤ አሜን፡፡