‹‹እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› (ኢያ. ፳፬፥፲፭)

ሰማይና ምድር ተፈጥረው የሰው ልጅ በዚህ ዓለም መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አምላኩ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ የፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ ‹‹ሰማይና ምድር ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ተፈጸሙ›› እንዲል፤ በመጽሐፍም ‹‹እግዚአብሔር አምላክም በኤዶም በስተምሥራቅ ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያ አኖረው›› እንደተባለ የመጀመሪያው ሰው አዳም በገነት ውስጥ ይኖር የነበረው ከአምላኩ ጋር ነበር፤ በዚህም የፈጣሪውን ሕግ ጠብቆና ትእዛዙንም እያከበረ ኖሯል፡፡ (ዘፍ. ፪፥፩፤ ፰)

የእግዚአብሔርን አምላክነት የካደው ሰይጣን ለፈጣሪው መገዛት ባለመፍቀዱ ከሰማያዊት መንግሥት ከመባረሩ ጋር ተያይዞ እርሱ አምላክ መሆንን ተመኝቶ ለማሳት የጀመረው በመላእክት ዓለም እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ እንዲገዙለትም ሊያሳምናቸው ቢሞክር ቅዱስ ገብርኤል በእምነት ጸንተው እንዲጠብቁ በማሳወቅ ከቅዱስ ሚካኤል እና ከሌሎች መላእክት ጋር ሰይጣንን ተቃውመውታል፤ ተዋግተውም አሸንፈውታል፡፡ ሆኖም እርሱን የተከተሉት ብዙኃን አጋንንትና ርኩሳን መናፍስት ከራሳቸውም አልፎ ለሌሎች ወደ ገሃነም መውረድ ምክንያት መሆናቸው እስከ ዛሬ ድረስ ይታወቃል፡፡

የሰይጣን ሥራ ሁል ጊዜ ከትዕቢት፤ ከተንኮል እና ከመጥፎ ምግባር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አዳም ከገነት የተባረረው ሰይጣን ተንኮልን አሳስቦት የፈጣሪውን ትእዛዝ እንዲተላለፍ በማድረጉ ነበር፤ ይህም እንዲህ ነው፤ እባብ ከተፈጠሩት የምድር አውሬ መካከል ተንኮለኛ ነበር፡፡ አዳምም ከሚስቱ ሔዋን ጋር በገነት በነበረበት ጊዜ እባብ ወደ እርሷ መጥቶ  ‹‹በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ሴቲቱም ለእባቡ አለች፤ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፤ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። እባብም ለሴቲቱ አላት፤ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።  (ዘፍ. ፫፥ ፩-፯)

እግዚአብሔር አምላክም ይህን አውቆ ስለምን አትብሉ ከተባሉት ዛፍ እንደበሉ ሲጠይቃቸው እባብ አስቷቸው እንደሆነ ነገሩት፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ። ለሴቲቱም አለ፤ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል። አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና›› ብሎ ፈረደባቸው፡፡ (ዘፍ. ፫፥፲፬-፲፱)

አዳምም ወደ ምድር ወረደ፤ በብዙም ተሠቃየ፤ የሰው ጥንተ ጠላት ሰይጣን ተረግሞ ወደ ምድር ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዳይመለስ ለመጣል በብርቱ ይለፋ ነበርና አዳምን በከባድ ይፈትነው፣ ችግርንም ያበዛበት ነበር፡፡ አዳምም በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ሁኖ ወደ የፈጣሪው መሥዋዕት ሲያቀርብ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም አዘነለት፤ ቃል ኪዳንም ገባለት፡፡ በዚህም መሠረት ከልጅ ልጁ ተወልዶ፤ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ አዳነው፡፡

ቀደም ሲል ለአባታችን አዳምና ለእናታችን ሔዋን ‹‹ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት›› ተብሎ እንደታዘዘው በምንኖርባት በዚህች ምድር በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ሆኖም የሰው ዘር በሙሉ የተፈጠረው እንደ መላእክት ፈጣሪው እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሊኖር ቢሆንም ነገር ግን የተፈጠሩበትን ዓላማ ረስተው ለሰይጣን የተገዙ እና ባዕድ አምልኮን የሚከተሉ ሰዎች በዓለማችን ሞልተዋል፡፡  (ዘፍ. ፩፥፳፰)

የነዌ ልጅ ኢያሱ  የእስራኤልን ሕዝብ ወደ ተስፋዋ ምድር እየመራቸው በነበረበት ዘመን አምላካቸውን ክደው ጣዖታትን ማምለክ በጀመሩ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ፡፡ እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፡፡ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን እርሱ ቅዱስ ነውና፡፡›› የእስራኤልም ሕዝብ የሚያመልኩአቸውን አማልክት ትተውና አርቀው ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዳግምም አመለኩት፡፡ (ኢያ.፳፬፥ ፲፬-፲፯)

ይህ ትውልድም እግዚአብሔር አምላኩን ክዶ ለባዕድ አምልኮ መገዛት ከጀመረ እና ለሰይጣን ተገዢ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ብዙ ሰዎች ለባዕድ አምልኮት ተገዢ መሆናቸው በተለያየ ጊዜ ማስረጃዎች በቤተ ክርስቲያናቱም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች በሰይጣን ኃይል ተመርተው ለጠንቋዮች የተለያዩ መሥዋዕትን በማድረግ በምድር ላይ የፈለጉትን ነገር ለማግኘት እንደሚጠቀሙበት በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ስለ ባዕድ አምልኮ እና አምላኪዎቹ ዝርዝር መረጃ የያዘ መጽሐፍም ተጽፏል፡፡

የእኛ ኃጢአት መብዛት ለተለያዩ መከራ፤ ሥቃይና በሽታ ተጠቂ እንድንሆን አድርጓል፡፡ በአሁን ጊዜም የተስፋፋው መድኃኒት የለሹ ወረርሽኝ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ ስለሆነም አምላካችን ሁሉን መርምሮ የሚያይና የሚያውቅ በመሆኑ በእርሱ ግዛት ውስጥ ሆነን ለሌላ ባዕድ አምልኮ እንድንገዛ ስለማይፈቅድ ቁጣውን በምድር አመጣ፤ መቅሠፍትም ላከ፤ ብዙዎችም በዚህ በሽታ ተጠቁ፡፡

የሰው ልጅ በመላ ዘመኑ በሚያጋጥመው መከራ እና ሥቃይ ሊፈተን፤ ከባድ ችግርም ሊደርስበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ፈተናው ከእግዚአብሔር ሲሆን ለድኅነት እና ለበረከት ከጠላት ዲያብሎስ ሲሆን ደግሞ ለጥፋት የሚመጣ በመሆኑ ፍርሃት ሳይሆን ጥንቃቄና ጽናት ያስፈልጋል፤ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› እንደተባለው በእምነት ሁሉንም ፈተና ማለፍ ይቻላል፡፡ ይህን እውነት አውቀውና ተረድተው ወደ እግዚአብሔር መመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ነቢዩ ኢያሱ ‹‹እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› ብሎ እንደተናገረው ባዕድ አምልኮን ትተው  እግዚአብሔርን ማምለክ ይኖርቸዋል፤ ካልሆነ ግን የዘለዓለም ቅጣት እንደሚጠበቃባቸው እሙን ነው፡፡ (ማር. ፭፥፴፮፤ ኢያ. ፳፬፥፲፭)

‹‹ከታላላቅ ኃጢአት እንዳትወድቁ ከትንንሽ ኃጢአት ተጠበቁ›› ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው ማንኛውም ሰው ከኃጢአት የራቀ እና የጸዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ሳናውቅ በስሕተት በማወቅ በድፍረት የሠራነውን ኃጢአትም ይቅር ይለን ዘንድም ዘወትር መማጸን አለብን፡፡ (መጽሐፈ መነኮሳት)

እንዲሁም ይቅርታና ምሕረትን ለማግኘት የምንሻ ከሆነና ይህንንም መቅሠፍት አምላካችን እንዲመልስልን ከፈለግን ከልብ በመጸጸት በንስሓ ወደ አምላካችን መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ ከተቻለም በአጽዋማት ጊዜ ሱባኤ ይዞ በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል እንጂ እንዲሁ ለጥቂት ጊዜ ስለጸለይን ብቻ ምላሽ ማግኘት ይገባናል ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር የውስጣችንን ስለሚያውቅ ለሁላችንም የድካማችንን ዋጋ ይከፍለናልና በትዕግሥት እና በእምነት ጸንተን በአምልኮተ እግዚአብሔር እንኑር፤ አምላካችንም በምሕረቱና በይቅርታው ይጎበኘን ዘንድ በእርሱ ሕግ ለመኖር ያብቃን፤ አሜን፡፡