‹‹እባክህ አሁን አድነን!››

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሚያዚያ ፲፯፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹…ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና…›› በማለት ትሕትናን በአንደበቱ ትምህርት ከማስተማሩ በተጓዳኝ በተግባር ሕይወቱም ተግብሮ ካሳየባቸው ዕለታት አንዱ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ነው፤ (ማቴ.፲፩፥፳፱) ይህ ግሩም አምላክ በትሕትና ከተገለጠባቸው ዕለታት አንዱ የሆነው ድንቅ ቀን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሆሣዕና›› በመባል ይታወቃል፡፡ ሆሣዕና መተርጉማነ አበው በአንድምታቸው ‹‹ሆሣዕና በአርያም በሰማይ ያለ መድኃኒት›› ብለው ተርጒመውልናል፤ (ማቴ.፳፩፥፱ ወንጌል አንድምታ) አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ደግሞ በመዝገበ ቃላታቸው ሆሣዕና ማለት ‹‹…እባክህ አሁን አድነን፤…መድኃኒት፣ መድኃኒት መሆን …›› በማለት ገልጸውታል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፫፻፸፫)

‹‹እባክህ አሁን አድነን››፡- ይህን የተማጽኖ ቃል የተናገሩት ጌታችን በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበሩ ሕዝብ ናቸው፡፡ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው፣ አንድም የወይራ ቅጠል እንዲሁም ልብሳቸውን ከምድር አንጥፈው ከልብ በመነጨ፣ ምስጋናቸው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉ ሆሣዕና በአርያም ‹‹…እባክህ አድነን…›› በማለት አመሰገኑት፡፡ የነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት ትንቢት ተፈጽሞ በእናታቸው ጀርባ ያሉ የሚጠቡ ሕፃናት አመሰገኑ፤ ‹‹…ከሕፃናት ከሚጠቡ ልጆች አፍም ምስጋናን አዘጋጀህ…›› እንዲል፡፡ (መዝ.፰፥፪)

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም፣ ቤተ ፋጌ በቀረበ ጊዜ ከቅዱሳን አባቶቻችን ሁለቱን ሐዋርያት ወደ ቤተ ፋጌ ልኮ የታሰረች አህያ እንደሚያገኙና ፈትተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፤ ነገር ግን ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው ከመጣ ‹‹…ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ…›› አላቸው፤ (ማቴ.፳፩፥፫) ፈትታችሁ አምጡ ማለቱ ሕዝቡን ከማዕሰረ ኃጢአት የሚፈቱበት ጊዜ እንደ ደረሰ ሲያጠይቅ ነው፡፡ ዛሬ ዓለም በሥጋዊ ጥቅም በኃላፊ ደስታ ዓይነ ልቡናችንን ጋርዳ፣ ሥጋዊ ፈቃዳችን ከፈቃደ ነፍሳችን አይሎ በኃጢአት ማዕሰር ታስረናል፡፡ ጌታችን በትምህርቱ ‹‹…ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው፤ ባርያም ለዘለዓለም በቤት አይኖርም…›› በማለት እንደገለጸው በበደላችን በኃጢአት ባርነት ቀንበር ሥር ወድቀን በዲያብሎስ ባርነት ታስረናል ፤ (ዮሐ.፰፥፴፬) ‹‹ሆሣዕና በአርያም፤ እባክህ አሁን አድነን››፤ ከታሰርነበት የጥላቻ፣ የቂም፣ የዘረኝነት፣ የጎጠኝነት የኃጢአት ማሰሪያ ይፈታን ዘንድ ‹‹እባክህ አሁን አድነን!›› እንበለው፡፡

‹‹እባክህ አሁን አድነን››፡- አይሁድ፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያን የምስጋና ባለቤት ከሆነው ዘንድ በተሰጣቸው ኃላፊነት ምስጋና የባሕርይው የሆነን ፈጣሬ ዓለማት መድኅን ዓለም ክርስቶስን ማመስገን፣ አመስግነው መመስገን፣ ቅዱስ ስሙን ጠርተው መቀደስ ሲገባቸው በተቃራኒው ልባቸው በጥላቻና በቅናት ተመልቶ የሚያመሰግኑት ዝም ይሉ ዘንድ ጠየቁ፤ አንደበትን ለምስጋና የፈጠረ ጌታ ግን ‹‹እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ›› አላቸው፤ ምንም የሚሳነው የሌለ ጌታም ድንጋዮች ያመሰግኑት ዘንድ አደረገ፡፡ (ሉቃ.፲፱፥፵)

ጌታችን በትምህርቱ ‹‹ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም›› በማለት እንደገለጸው የክፋት ሥራቸውን የሚገልጥ፣ ጨለማ አስተሳሰባቸውን የሚያበራ የብርሃን ጌታ ሲመጣ የእርሱ መገለጥና መመስገን እነርሱን የሚያሳንስ ስለመሰላቸው ተቃወሙ፡፡ ክህነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነና የሰጣቸውም እርሱ እንደሆነ ማስተዋል ቢሳናቸው የራሱን ገንዘብ ምስጋናውን ለማስቀረት ፈለጉ፤ (ዮሐ.፫፥፳) ማድረግ የማይቻላቸውን ሊያስቀሩ ደፈሩ፤ ክፉዎች የቅኖች ደግነት፣ የመልካሞች በጎ ሥራ፣ የትሑታን የተሰበረ መንፈስና የአመስጋኞች ምስጋናቸው ይረብሻቸዋል፡፡

ልቡናቸውን ለጠላት ዲያብሎስ ማኅደር ስላደረጉ የቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ስሙ ሲጠራና ምስጋናው ሲደመጥ ሰላም ይነሳቸዋል። ዲያብሎስ እግዚአብሔር ሲመሰገን፣ ሰው ንስሐ ሲገባ፣ የምሥራቹ ወንጌል ሲነገር፣ ምእመናን በቤተ እግዚአብሔር ሲበዙ፣ ሰላም ሲሰፍን፣ ሰዎች ሲፋቀሩ አንድነት ሲጸና፣ ሕገ እግዚአብሔር ሲከበር፣ ክርስትና ሲሰፋ፣ በዓላት ሲከበሩ ማየትና መስማት አይሻም፤ የግብር ልጆቹን እያሰማራ መንፈሳዊውን ዓለም ያውካል፤ ሁሉም እንደ እርሱ ከፈጣሪው ተጣልቶ በክህደት እንዲኖር ይፈልጋሉ። ዓለም ሳይፈጠር ባሕርይው ባሕርይውን እያመሰገነ ምስጋናው ሳይቋረጥ የኖረውን ጌታችንን በእናታቸው እቅፍ ያሉ ሕፃናት፣ አዕባን (ድንጋዮች) “ለምን አመሰገኑት” ብለው የቅናት ጥያቄ እንደጠየቁት ማለት ነው።

ዛሬም በሥጋ ለባሹ የሰው ልጅ አድሮ “ለምን አመሰገናችሁ? ለምን አምልኮተ እግዚአብሔር ፈጸማችሁ” በማለት ምስጋናውን ሊያስቀር ይጥራል፤ ግን አይቻለውም! እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት በስሙ እንዳያስተምሩ፣ ባስፈራሯቸውም ጊዜ ‹‹… ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል…›› አሉ፡፡ (የሐ. ሥራ ፭፥፳፱) እኛም ልጆቻቸው የአሠረ ፍኖታቸው ተከታይ ነንና! ዛቻና ማስፈራራቱን ሳንፈራ ‹‹ሆሣዕና በአርያም፤ እባክህ አሁን አድነን›› እንላለን፡፡ አመስግነን እንመሰገን፣ ቀድሰን እንቀደስ ዘንድ ከባለጋራችን ዲያብሎስ የተቃውሞ ዛቻና በትር እንዲታደገን ዘንድ ‹‹ሆሣዕና በአርያም፤ እባክህ አሁን አድነን…መድኃኒት ሁነን›› ብለን እንዘምራለን፡፡

ዲያብሎስ በግብር ልጆቹ ልቡና አድሮ በግፍ በትር ሊሸነቁጠን በተስፋ መቁረጥ ገመድ አስሮናልና ቅዱሳን በቃል ኪዳናቸው ይፈቱን ዘንድ ይልክልን ዘንድ ‹‹ሆሣዕና በአርያም፤ እባክህ አሁን አድነን›› እንበለው፤ በነቢዩ ዘካርያስ አማካኝነት ‹‹…የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በይ፥ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል…›› በማለት በተናገረው ቃል መሠረት መምህረ ትሕትና የዓለም ጌታ መድኅን ክርስቶስ በአህያይቱና በውርንጭላይቱ ዘባን ( ጀርባ) ተቀምጦ ሲመጣ በኢየሩሳሌም የነበሩ ልብሳቸውን ከምድር አነጠፉ፤ (ዘካ.፱፥፱) “እንኳን ለአንተ ለተቀመጥክባት አህያም ክብር ይገባል” ሲሉ! ትሕትናን ከእርሱ በተግባር ተምረዋልና በትሕትና የለበሱትን ልብስ አውልቀው ከምድር አነጠፉ፤ በጥቂት የትሕትና ሥራቸው ዝቅ ካሉበት ከሰጠሙበት የበደል አዘቅት ከፍ ያደርጋቸውና ያከብራቸው ዘንድ ‹‹ሆሣዕና በአርያም፤ እባክህ አሁን አድነን…!›› በማለት ተማጸኑት፤ እኛም ከልቡናችን እልፍኝ በጎ ሥነ ምግባር ልብሳችንን አንጥፈን ይገባበት ዘንድ ‹‹በሰማይ ያለ መድኃኒት ናልን›› ብለን እንጋብዘው፡፡

በሆሣዕና በዓል ዕለት በምስጋናው ጊዜ ዘንባባን እንይዛለን፤ ጌታችን በአህያና በውርንጭላይቱ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ከልብሳቸው በተጨማሪ የዘንባባ ዝንጣፊም ይዘው ነበር፤ በብሉይ ኪዳን ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ደግሞ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ወጡ፤ ዮዲት ወገኖቿን ሲያስጨንቅ ንጹሐንን በግፍ ሲገድል የነበረውን ሆሎፎርኒስ የተባለን ሰው ገድላ በተመለሰች ጊዜ ዘንባባን ይዘው ደስታቸውን ገልጠዋል፡፡ አንድም ይላሉ መተርጉማነ አበው ‹‹ዘንባባ እሾኻማ ነው፤ ትእምርተ ኃይል (መዊእ) አለህ›› ሲሉት አንድም ዘንባባን እሳት አይበላውም፤ ለብልቦ ይተወዋል፤ ባሕርይ አይመረመርም›› ሲሉ ነው፡፡ የሰላም አለቃ፣ ኃያል፣ ልዑል፣ ባሕርይው የማይመረመር አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ይሆነን፣ ያድነን ዘንድ በሕጉ ተጉዘን፣ ትእዛዙን፣ አክብረን፣ በትሩፋት ሥራ አጊጠንና የምግባር ዘንባባን ይዘን ጠላት ዲያብሎስን ድል አድርገን ‹‹ሆሣዕና›› እንበለው፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል አድምታ ትርጓሜ ፳፩፥፰) ዝቅ ካልንበት ከፍ ያደርገን ዘንድ ከእግሩ በታች ራሳችንን እናዋርድ፤ ‹‹… በመጠን ኑሩ፤ ንቁም ባለጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና …›› እንደተባለው፤ (፩ኛጴጥ. ፭፥፰) በአህያ ውርንጭላ ጀርባ ተቀምጦ ስለ እኛ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከፍ አድርጎናል፤ ዳግመኛ በኃጢአት ቀንበር ወድቀን በባርነት እንዳንያዝም በጾምና በጸሎት ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡

‹‹አምላካችን ሆይ! እባክህ አሁን አድነን!››

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ! አሜን!