‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› (ራእ. ፲፬፥፲፪)

ዲያቆን ተስፋዬ ዓለማየሁ

መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በዮሐንስ ራእይ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› በማለት የተናገረው ኃይለ ቃል የመጨረሻውን ዘመን አስጨናቂ እና ፈታኝ መሆን እንዲሁም ክርስቲያኖች ይህን ተረድተው በትዕግሥት መጽናት እንደሚገባቸው ለማስረዳት ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር ፲፩ ላይ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፣ የስሙንም ምልክት የሚጽፉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት እንደሌላቸው፣ ሕዝብንና አሕዛብን ስለሚፈትነው፣ በመጨረሻ ዘመን ስለሚነሣው አውሬ እና በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት እንደሚጣሉም ይገልጻል፡፡ (ራእ. ፲፬፥፲፪)

በዚያን ጊዜ ሰዎች ለሥጋዊ ድሎት በመገዛት፣ በጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች በመታለል እንዲሁም ለአውሬው ምስል በመስገድ ለእርሱ በመገዛታቸው የሞት ሞትን ይሞታሉ፡፡ ክርስቲያኖች ግን ለአውሬው ምስል ባለ መስገድ፣ ባለ መገዛት እና በሕይወታቸው ውስጥ የሚመጣባቸውን መከራ በመታገሥም ለእውነተኛው አምላክ ለእግዚአብሔር በመገዛት ጸንተው ይኖራሉ፤ በመጨረሻም መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ የአውሬው የሆነውን ሁሉ የማይቀበሉትን፣ ለእምነታቸው ሲሉ መከራን የሚታገሡትን እና ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምኑትን ሁሉ ‹‹ቅዱሳን›› ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኢየሱስን በማመን›› ሲል ምን ማለቱ ነው?

ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኢየሱስን በማመን›› ብሎ የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ እግዚአብሔር አብ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነበሩበት ጊዜ አብሮ ያለ፣ ከአብና መንፈስ ቅዱስ የማያንስና የማይበልጥ፣ በዘመነ ሥጋዌም ከንጽሕተ ንጹሓን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶና በሥጋ ተገልጦ ዓለምን ያዳነ መሆኑን ማመን ማለት ነው፡፡ ጌታችን ለራሱ መጾም ሳያስፈልገው ስለ እኛ ጾሞ፣ በምድር ላይ ተራበ ተጠማ፤ እርሱ መከበር ሲገባው ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር አጠበ፤ ለእኛ ድኅነትም በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንደገለጸው እውነተኛ ክርስቲያኖች ጌታችን ኢየሱስ በቀራንዮ አደባባይ የተቀበለውን መከራና ሥቃይ በማሰብ እንዲሁም መስቀሉን በመሸከም በክርስቶስ ክርስቲያን መባላቸውን ያረጋግጡ ዘንድ በምድር ላይ በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት የሚተጉ ናቸው፤  ፈተናቸውንም በትዕግሥት ይወጣሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ለዚህ ለከበረና እውነተኛ ሃይማኖት ሲሉ ሥቃይ መከናን በመታገሥ እንደ ሽንኩርት ተከትፈዋል፤ በመጋዝ ተሰንጥቀዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል፤ ለአንበሳ ተሰጥተዋል፤ አንገታቸውን ተቆርጠዋል፡፡

ዛሬም ቅዱሳን አባቶቻቸን እና እናቶቻችን በደማቸው ያቆዩልን ሃይማትና ሥርዓትን በኃላፊነት ተቀብለን እና ጠብቀን መኖር እንዲሁም ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡ በቅድስት ሥላሴ አንድነት ሦስትነት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት፣ በቅዱሳን አማላጅነት እና ተራዳኢነት በማመን እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን በመጠበቅ የአውሬው ማጒረምረም እና የአሕዛብ ሰይፍ ሳያስፈራን፣ የመናፍቃን ማስመሰል ሳያስተን በሃይማኖት ጸንተን የዘለዓለም ሕይወትን መውረስ ይጠበቅብናል፤ ይህንን ሁሉም በትዕግሥት ልናደርገው እንደሚገባ ቅዱስ ዮሐንስ አስተምሮናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ስለ ትዕግሥት እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹እነሆ በትዕግሥት የሚጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ የኢዮብን ትዕግሥት ሰምታችኋል፡፡ እግዚአብሔርም የፈጸመለትን አይታችኋል›› እንዲል፡፡ (ያዕ. ፭፥፲፩)

ጻድቁ አባታችን ኢዮብ በሕይወት ዘመኑ እንደርሱ እውነተኛ እና ደግ ሰው እንዳልነበረ በእግዚአብሔር የተሰመከረለት ሰው ነበር፡፡ ጠላት ዲያብሎስ ግን በእርሱ ላይ ቀንቶ በገንዘቡና በልጆቹ ላይ ያሠለጥነው ዘንድ እግዚአብሔርን በመጠየቁ እግዚአብሔርም የኢዮብን ትዕግሥት ያውቅ ነበርና ሰይጣንን እንዲፈትነው ፈቀደለት፡፡

ከዚህ በኋላም በአንዲት ቀን የኢዮብ ገንዘብ ሁሉ ጠፋ፤ ሰውነቱ ሥጋው በደዌ ሥጋ ከራሱ ጠጉሩ እስከ እግሩ ጥፍሩ ድረስ ተመታ:: ልጆቹም አንድ በአንድ ሞቱበት፡፡ በዚህ ውስጥ ሆኖም ግን እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን›› አለ:: (ኢዮብ ፩፥፳፩)

ኢዮብ በዚህ ባገኘው መከራ ሀብቱን ንብረቱን ልጆቹን መላ አካሉንም በበሽታ ሲመታ፤ ጤናው ሁሉ ሲታወክ አምላኩን አመሰገነ እንጂ አንድም የስንፍና ቃል በአምላኩ ላይ አልተናገረም:: ሆኖም ‹‹ረገማ ለዕለት ዘተወልደ ባቲ፤ ……የተወለደበትን ቀን ረገመ::›› (ኢዮብ ፫፥፩)

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም በአስጨናቂ ደዌ ተይዞና በሐዘን ውስጥ በነበረበት ጊዜ የወዳጆቹና የሚስቱ ዘለፋ በዝቶበት ነበር:: ሚስቱም ልታበረታው፣ ልትረዳው፣ ልታጽናናው ሲገባ ከወዳጆቹ ብሳ እንዲህ ብላ ተናገረችው:-

‹‹እስከ መቼ ድረስ በሞኝነት ትኖራለህ፤ እንግዲህስ ስደበውና ሙት፤ ዳግመኛ እግዚአብሔርን ደጅ እጠናዋለሁ፤ መከራውንም እታገሣለሁ፤ የቀድሞ ኑሮዬን ተስፋ አድርጋለሁ ትላለህ›› አለችው::

ዳግመኛም አለችው:: ‹‹እንዲህስ እንዳትል ከዚህ ዓለም እንሆ ስም አጠራርህ ጠፋ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼ ሞቱ:: እኔም ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ላይረቡኝ ላይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምኩ:: አንተም በመግል ተውጠህ፣ በትል ተከበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ፤ እኔም እየዞርኩ፣ እቀላውጣለሁ፤ ከአንዱ ሀገር ወደአንዱ ሀገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ:: ከድካሜ በእኔ ላይ ከመጣው ከችግሬም ዐርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኽው ሙት›› አለችው::

ኢዮብም ሚስቱን እየተመለከተ በትዕግሥት ሰማት:: እንዲህም አላት፦

‹‹ይህን ሁሉ እግዚአብሔር ለመልካም አደረገ፤ ሥርዓት እንዳልተሠራባቸው አሕዛብ ሴቶች እንዳንዲቱ ተናገርሽ፤ ከዚህ ቀድሞ በጎውን ነገር ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበልን፤ ከዚህ በኋላ መከራውን እንታገሥም ዘንድ›› አላት::‹‹ወተፈትነ ወተነጥፈ ከመ ወርቅ በእሳት፤ ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ፈጽሞ ተፈተነ›› ብሎም መሰከረ፤ ያለ መከራ ዋጋ ያለፈተና ጸጋ አይገኝምና፡፡

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔርም ኢዮብን ከደዌ ሁሉ ፈወሰው፤ ሀብቱንም ሁሉ ባርኮ ከቀድሞ እጥፍ አደረገለት፤ የተባረኩ ልጆችም ሌሎች ወንዶችና ሴቶችም ሰጠው:: ኢዮብም ሁለት መቶ አርባ ስምንት ዓመት እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም ዐረፈ፤ መንግሥተ ሰማያትንም ወረሰ፡፡ (ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት ፪)

ከጻድቁ አባታችን ኢዮብ ታሪክ እንደምንረዳው በሕይወታችን የሚመጣብንን ችግርም ሆነ መከራ እንዲሁም በሽታ በትዕግሥት ተመቋቁመን ማለፍ እንደሚገባ ነው፡፡ ይህንንም መፈጸም ከቻልን መጨረሻችን እንደ ኢዮብ አስደሳች ይሆናል፤ ትዕግሥት ፍሬዋ ጣፋጭ ነውና፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትዕግሥት መጽናት እንደሚገባ ሲያስተምር ‹‹…መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፤…›› ብሏል፡፡ (ሮሜ. ፭፥፫)

ምንም እንኳን የጠላታችን ዲያብሎስና የዓለም ፈተና ቢበዛብን፣ መከራ ቢፈራረቅብን፣ በበሽታ እና በተለያዩ ችግሮች ብንሠቃይም ችግሮቻችንን ተቋቁመን ለማለፍ መታገሥ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ትዕግሥት ማለት በመልካም ጊዜ የምንተገብረው ሳይሆን በችግር ጊዜ ለመጽናትና ፈተናችንን ለማለፍ የሚረዳን ምርኩዛችን ነው፡፡ በትዕግሥት የሚጓዝ ሰው ጠንካራም ያሆናልና፤ በዚያም እስከ መጨረሻው በሃይማኖት ጸንቶ ለመኖር ይቻለዋል፡፡

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ማመናችንን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ አጽንተን እንድንጓዝ እንዲሁም ፈተናዎቻችንን የምናሸንፍበት ጽኑ ትዕግሥት እግዚአብሔር አምላካችን እንዲሰጠን ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር