አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ

ጥር ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በኃጢአት የተገነባውን የሰናዖር ግንብ ያፈረሱበት አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን በግልጽ ያሳዩበት ጥር ሰባት ቀን የከበረ በዓል እንደመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ታሪኩ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደተጻፈ እንዲህ ይነበባል፡፡

የኖኅ የትውልድ ነገዶች ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ።እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።እግዚአብሔርም አለ።‹‹ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።››እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ከተማይቱንም መሥራት ተው።ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ።እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል። (ዘፍ.፲፩፥፩-፱)

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ አንድነታቸውን ሲያጠይቅ ‹‹ኑ እንውረድ›› ባሉት መሠረት ሥላሴ በስም በአካል በግብር ሦስት መሆናቸው እንረዳለን፤ የስም ሦስትነታቸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ የግብር ሦስትነታቸውስ ደግሞ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ የመሆኑ ምሥጢር ነው፤ የአካል ሦስትነታቸው ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ስላላቸው ነው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመሆኑ የሥላሴ ገጽ አካል ፊት እንደ ሰው ነውን? የሚል ጥይቄ የተነሣ እንደሆነ መልሱ‹‹አዎ፤ እንደ ሰው ነው›› ይሆናል፤ ነገር ግን የሰው ውሱን ጠባብ ፈራሽና በስባሽ ነው፤ የሥላሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ በሰማይና በምድር፣ በአየርና በእመቅ የመላ ረቂቅ ሕያው ባሕርይ ነው፡፡‹‹ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድን ነው? ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፤ ይህም ሁሉ የእኔ ነው››እንዲል፤ (ኢሳ.፹፮፥፩-፪) የሥላሴ አንድነታቸው በመለኮት፣ በፈቃድ፣ በሥልጣን፣ ወዘተ በመሳሰሉት ነው።

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን!