‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል›› (መዝ.፴፫፥፲፫)

ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ሰዎች አንደበታችንን እግዚአብሔርን ለማመስገንና በጎ ነገርን ለመናገር ልንጠቀመው ይገባል። በእያንዳንዱ ንግግራችን የምናወጣቸው ቃላትም ሆነ የምንመሠርታቸው ዓረፍተ ነገሮች ከክፋት የጸዱ መሆን አለባቸው። ለዚህም ነው ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ›› በማለት የተናገረው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓው ሲናገር ‹‹ይጹም ዐይን ይጹም ልሳን እዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ሕሡም፥ ዐይን ይጹም፣ አንደበትም ይጹም፣ ዦሮም ክፉን ከመስማት ይጹም›› ብሎ እንደተናገረ አንደበት በቃለ እግዚአብሔር እና በበጎ መንፈሳዊ ምግባራት ካልተገታችና ካልታረመች የሰውን ልጅ ወደ ጥልቅ የበደልና የጥፋት መንገድ ሊጥሉት ከሚችሉ ሕዋሳት አንዲቱ ናት። (መዝ.፴፫ (፴፬)፥፲፫)

በመጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያው ያዕቆብ መልእክት እንደተገለጸው ከቁጥጥር ውጭ የሆነ አንደበት ወደ ለኃጢአት ይመራል፡፡ አንድ ሰው ምላሱን ሳይገታ፣ በክፉ ልቡና ተነሣስቶ ቃላትን ቢያወጣ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ እክል ይሆንበታል። አምልኮው፣ አገልግሎቱ እና ጥረቱ ሁሉ ከንቱ ይሆናል። እምነት በጎደለውና በሐሰተኛ አንደበት የእውነትን ቃላት ብናወጣ የእግዚአብሔርን ሕግ አለማክበር በመሆኑ የጽድቅ ሳይሆን የኵነኔ ፍርድ ይከተለናል፡፡ ሁሉን የሚያይ ከእርሱ ምንም ምን የማይሠወረውን እግዚአብሔር አምላክን እናታልላለን ወደሚል እሳቤም ከደረስን ለጥፋት እንዳረጋለን፡፡ (ያዕ.፩፥፳፮)

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በምዕራፍ ሦስት ላይ እንዲሁ የአንደበትን ዋጋ ያብራራል፤ ከሰውነታችን አካላት ውስጥ ትንሽ ቢሆንም ሰውን ወደ ሕይወት ወይም ወደ ጥፋት ሊመራ የሚችል ሕዋስ ነው። እንደ መርከብ መሪ፣ ምንም እንኳን ከመርከቧ መጠን ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም፣ መንገዱን ይቆጣጠራል፤ እናም በደኅና ወደ ባሕር ዳርቻ ሊወስደው ወይም ወደ ጥፋቱ ሊልከው ይችላል።

ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ፥ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር፥ እርሱ አምልኮቱ ከንቱ ነው›› በማለት የተናገራቸው ቃላት ባልተገደበ አንደበት ምክንያት የአንድ ሰው ሃይማኖት እንዴት ከንቱ ሊሆን እንደሚችል ያሳያሉ። ሃይማኖት ያለ ምግባር ባዶ በመሆኑ የማንተገብራቸውን ተግባራት በተዋቡ ቃላት አጅቦ በሽንግላ አንደበት በስመ ክርስቲያን ብቻ መኖር የተገባ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን፣ ጾማችን እና ጸሎታችን የይስሙላ ከሆነ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡   (ያዕ.፩፥፳፮)

አንደበታችንን መጠቀም ያለብን መጥፎ ቃላትን ከመናገር መከልከል ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የሚጠቅመውን ለመናገርም ነው። በመጽሐፍም ‹‹የሚሰሙአችሁ ሞገስን ያገኙ ዘንድ፥ ግዳጃችሁ እንዲፈጸም መልካም ነገር እንጂ ክፉ ነገር ሁሉ ከአፋችሁ አይውጣ፡፡››፣ (ኤፌ.፬፥፳፱) ‹‹የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ፡፡›› (ሮማ.፲፪፥፲፬) ‹‹የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ማመስገን ይሁን እንጂ›› ተብሎ ተጽፏልና፡፡ (ኤፌ.፭፥፬)

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ አንደበታችንን ለሚጎዳና ለሚያጠፋ ነገር ከመጠቀም እንድንጠነቀቅ ያሳስበናል፤ ምናልባት ሁል ጊዜ ማስታወስ ያለብን የአባቶቻችን ምክር ነው፤ ይህም አንደበታችንና ልባችንም ከክፋትና ከሐሰት መከልከል የተሻለ መሆኑን ነው። በዚህ ጊዜ ዓለማችን የሐሰተኞችና አስመሳዮች መናኻሪያ በመሆኗ አንደበቱ ሁለት ከሆነ ሰው መጠንቀቅ እንዳለብን በዚሁ መረዳት ያሻል፡፡ በምድራዊ ሕይወት ጥቅም ዓይናቸው ታውሮና ልባቸው በክፋት ደንድኖ እውነትን የካዱ ሰዎች እንደ አሸዋ በበዙበት በአሁኑ ዘመን ራሳቸው ጠፍተው ለሌሎች ጥፋት መንሥኤ የመሆናቸውን ምክንያት እንኳን እንደ ጀግንነት ይቆጥሩታልና በጎነትን፣ መንፈሳዊነትን እንዲሁም ክርስቲያናዊነትን ለማጥፋት ከሚዳክሩ ሰዎች እንጠንቀቅ፡፡ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ እንደነዚህ ዓይነቱን ሰዎች እየመረጠ በእነርሱ ላይ በማደር በጎ ሰዎች ክፋትና ኃጢአት ለማሠራት የዘወትር ጥረቱ በመሆኑ በንግግራቸው ሊያሳምኑን ከሚቀርቡን ሰዎችን ውስጣቸውን አናውቅምና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡

ሰው በምላሱ ከሚወድቅ ከፍ ካለ ቦታ ቢወድቅ ይሻላል። ሃይማኖታችን በከንቱ እንዳይሆን በአንደበታችን ከልብ ከመነጨ ሐሳብ እውነትን ልንናገር ያስፈልጋል፡፡ አምልኮትን ለመፈጸም የምናደርጋቸው ነገሮች እውነትና የእውነት መሆን አለባቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄዳችን የልማድና የታይታ ሳይሆን እግዚአብሔር አምላካችንንና ድኅነትን ፈልገን ሊሆን ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን እውነት በመሆኑ እኛም ለእርሱ ተገዝትን ለመኖር እውነትን ወደን በእውነተኛ መንገድ ልንጓዝ አለብን፡፡ እውነትን የሚሻ ልብ፣ እውነትን የሚናገር አንደበት፣ ስለ እውነት የሚሠዋ ሰውነት ሊኖረንም ያስፈልጋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ፴፫ ዓመት ሲኖር ወንጌልን ሰብኮ፣ በገቢረ ተአምራቱ ብዙዎችን ፈውሶ፣ በመስቀሉ መከራና ሥቃይ ተቀብሎ፣ ሞቶ ተቀብሮ፣ በትንሣኤው ተነሥቶ እና ዐርጎ የድኅነትን መንገድ ‹‹የእውነትና የሕይወትም መንገድ እኔ ነኝ›› ብሎ እንዳስተማረን መስቀሉን ተሸክመን መጓዝ ይገባል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፮)

እግዚአብሔር አምላክ በጎ ኅሊናን፣ ርቱዕ አንደበትንና ጽናትን ያድለን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!