‹‹አንተም÷ የሰው ልጅ ሆይ÷ ጡቡን ወስደህ በፊት አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሳልባት፤ ክበባት›› (ሕዝ.፬፥፩)

በብዙአየሁ ጀምበሬ

ቅዱሳት ሥዕላት አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምባቸው ንዋያተ ቅድሳት ናቸው፡፡ እስራኤላውያን ቀደም ሲል ሰዎች ድንጋይን በማዘጋጀት፣ እንጨትን በመጥረብ፣ ቆዳን በመፋቅ፣ ኅብር ባላቸው ቀለማት በመሳል ለትውልድ እንዲተላለፉ ያደርጉ ነበር፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት አጀማመር ዘመነ ኦሪትን መነሻ ያደረገ ነው፤ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ በታቦተ ሕጉ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል አዘዘው፡፡ ‹‹ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን÷ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሰራዋለህ፡፡ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፤ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፤ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ››፡፡ (ዘጸ. ፳፭፥፲፱-፳)

ስለ ቅዱሳትሥዕላት አጀማመር በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ‹‹በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው አሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤልን ሠራ፡፡ የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ÷ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ አሥር ክንድ ነበረ፡፡ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ፡፡ የአንዱ ኪሩብ ቁመት አሥር ክንድ ነበረ÷ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ፡፡ ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፡፡ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር÷ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር፡፡ ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው፡፡ በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ››፡፡(፩ኛ ነገሥት ፮፥፳፫-፳፱) በትንቢተ ሕዝቅኤልም ‹‹አንተም÷ የሰው ልጅ ሆይ÷ ጡቡን ወስደህ በፊት አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሣልባት፤ ክበባት›› ይላል ሕዝ.፬፥፩)፡፡

በጥንት ዘመን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በዋሻ ውስጥ በሥዕል እያስደገፉ ያስተምሩ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ለእምነታቸው ሲሉ ለተጋደሉ እና መሥዕዋትነትን ለከፈሉ ቅዱሳን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሥዕል በመሣል ታሪካቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ክርስቲያኖች ይህንን እያደረጉ ለዘመናት ከቆዩ በኋላ በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሮማውያን ክርስቲያኖች እና በቢዛንታይን ክርስቲያኖች ዘንድ አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላትን ምክንያት በማድረግ በሁለት ጽንፍ ተከፈሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ኢኮኖላትሪያ ሲባሉ እነዚህም ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላትን ከመጠን በላይ አብዝተው ከመውደዳቸው የተነሳ እንደ አማልክት የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ኢኮኖማኺያ ሲባሉ እነዚህም ክርስቲያኖች ቅዱሳት ሥዕላት ከነጭራሹ አያስፈልጉም በማለት ከአምልኮት ሥፍራ መወገድ አለባቸው የሚል አመለካከት የያዙ ነበሩ፡፡ ይህም አለመግባባት ለረጅም ዘመናት ከቀጠለ በኋላ በ፯፻፹፯ እ.ኤ.አ ሁለተኛው የኒቅያ ጉባኤ ተደርጎ ለቅዱሳት ሥዕላት አክብሮት እና ስግደት እንደሚገባ  ተወሰነ፡፡ በዚህም ጉባኤ መሠረት ቅዱሳት ሥዕላት በቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር ክብሩ መገለጫ ሁነው የሚያገለግሉ የቅድስት ሥላሴ፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ የቅዱሳን መላእክት፤ የነቢያትና ሐዋርያት የጻድቃንና ሰማዕታት ሥዕላት ናቸው፡፡ (ዐምደ ሃይማኖት ምዕራፍ ፲፫)

በቅድስት ቤተክርስቲያን የምንገለገልባቸው ቅዱሳት ሥዕላት የተሣሉት ባለቤቱ እግዚአብሔር በመረጣቸው ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለቱን ሥዕል ለንጉሥ ጢባርዮስ የሣለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነበር፡፡ ቅዱሳት ሥዕላት ቀኖና ቤተክርስቲያንን መሠረት ያደረገ የአሣሣል እና የአጠቃቀም ሥርዓት አላቸው፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ስለሚሰቀሉ ምእመናን በሥዕሉ ፊት በመቆም የሚጸልዩበትና ልመናቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡

ቅዱሳት ሥዕላት በሚሣሉበት ወቅት አስቀድሞ የቅድስና ባለቤት ልዑል እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም የዕውቀት እና የጥበብ ባለቤት እርሱ ስለሆነ ሥዕላቱን ለመሣል የሚያስችል ጸጋ እንዲያድለን ነው፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት የቀለም አጠቃቀምም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን አንድምታ ያለው እንጂ በዘፈቀደ የሚሆን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀይ ቀለም ለቅዱሳን፣ ለጻድቃን እና ለሰማዕታት ወኪል የሆነ ሰማዕትነትን እና ተጋድሎን የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሰማዕታት ሥዕላት ላይ ቀይ ቀለም በብዛት ሊስተዋል ይችላል፡፡ ነጭ ቀለም ንጽሐ ባሕርይን ስለሚያመለክት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በቅድስት ድንግል ማርያም የትንሣኤ እና የዕርገት ሥዕላት ላይ ሊስተዋል ይችላል፡፡ ሰማያዊ ቀለም የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ አምላክነት እና ቀዳማዊነት ስለሚያመለክት በቅድስት ሥላሴ ሥዕለ አድኅኖ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ የቅዱሳት ሥዕላት የአሣሣል ልኬት መጠን እንደ አስፈላጊነቱ ሊተልቅ ወይም ሊያንስ ይችላል፡፡ በጸሎት መጻሕፍት ላይ የመጽሐፉን መጠን መሠረት ያደረገ ሲሆን በሕንጻ ቤተክርስቲያን ላይ ደግሞ የሕንጻውን መጠን መሠረት አድርጎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡

ቅዱሳት ሥዕላትን ለጸሎት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች በምንጠቀምበት ጊዜ ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ በዋነኛነትም እንዳይበላሹ እና እንዳይደበዝዙ በክብር ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሥዕላቱ የሚገልጹት የሥዕሉ ባለቤት የሆነውን አምላክ ወይም ቅዱስ፤  ጻድቅ ወይም  ሰማዕት ስለሆነ ተገቢውን ክብር እና ሥርዓተ አምልኮ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ምእመናን ትክክለኛዎቹን የሥዕሉን ባለቤቶች አውቀው እንዲያከብሩ እና እንዲማጸኑባቸው ሠዓሊዎች የሚሥሉትን ቅዱስ ሥዕል በትክክል መሣልም አለባቸው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የአምልኮት ስፍራዎች ይህ እየተተገበረ አይደለም፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥዕልን በማስመሰል ሁለት ወይም ሦስት አይነት ሥዕል ይሳላል፡፡ ለዚህም ምሳሌ በቅድስት አርሴማ ሥዕል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም  በምእመናን ዘንድ አነጋጋሪ ርዕስ ከመሆኑም ባሻገር የእርሷ ሥዕል አለመሆኑን ጭምር የሚሟገቱ ምንጮች ተነሱ፤ በስተመጨረሻ ሁላችንም የቅድስት አርሴማ ብለን የተቀበልነው ሥዕል የቅድስት ባርባራ ነው የሚል ድምዳሜ ላይም ደረሱ፡፡

ከዚያም በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ያልጠበቁ እና ከአኃት ምስራቃውያን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ውጪ የሆኑ ሥዕላት በስፋት ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ያህልም በምዕራብ አውሮፓ በካቶሊካውያን በስፋት የሚስተዋሉ ከኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጪ የሆኑ ሥዕላት አሉ፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ሆኖ የሚጠቀሰው የጌታችን እና አምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ሲሆን ባለ ሁለት ጣት ምስሎች ለሽያጭ እየቀረቡ ነው፡፡ በምስራቃውያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ባለአንድ ጣት ሥዕሎች ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሚለውን የተዋሕዶ ምሥጢር ስለሚያመለክት እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡ (ምሥጢረ ተዋሕዶ) ትክክለኛውን ሥዕል ለይቶ አለማወቅ አምልኮተ ሥርዐቱ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የማይወክሉ ሥዕላትን ከመጠቀም ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ በዚህም እንደ መፍትሔ ልንወስደው የምንችለው በታሪክ የወረስናቸውን የመጀመሪያዎቹን ሥዕሎች በማመሳከር፣ ካህናትንና ሊቃውንትን በመጠየቅ ልንጠቀም ይገባል፡፡

ምንጭ፡- (ዐምደ ሃይማኖት በብርሃኑ ጎበና ፳፻ ዓ.ም.)