‹‹አናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ፤ የገሃነም ደጆች አይችሏትም›› (ማቴ.፲፮፥፲፱)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
ሰኔ ፲፱፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በፊልጶስ ቂሳርያ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል›› ብሎ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠየቀ ሰዓት የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገረው ቃል ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ሆነ ነው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፫) ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› በማለት በሰጠው ምስክርነት ጌታችን ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ …..አንተ ዓለት ነህ፥ በዚያችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም›› በማለት ለሐዋርያቱ ቃል ኪዳን ገባላቸው። (ማቴ.፲፮፥፲፰) ቤተ ክርስቲያን የሚለው የተለያየ ዐውዳዊ ፍች ቢኖረውም የሰውን ድካም የሚያውቅ እግዚአብሔር በዚህች ቀን በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በፊልጵስዩስ ከሦስት ደንጊያዎች ቤተ ክርስቲያንን ሠራልን። ዓለት ያለውን ቅዱስ ጴጥሮስንም ‹‹አርሳይሮስ›› ብሎ ሾመው፤ ትርጓሜውም ሊቀ ጳጳሳት ማለት ነው። (መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ወር፣ ፳ እና ፳፩ ቀን)

ለሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን መነሻው ምንድን ነው የሚለውን እንመልከት፦ ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ በአሕዛብ ውስጥ በሰበኩ ጊዜ ብዙ ሰዎች ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፤ ከሰዎች ቤቶች በቀር ቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያን አልነበራቸውም። የሐዲስ ኪዳን ሊቃውንትም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የላከላቸውን መልእክት ምክንያቱን ሲገልጹ የቆንሮቶስ ምእመናን ከጣዖት ማምለክ የተመለሱ ስለነበረ ወደ ቤተ ጣዖት እንዳይሔዱ ሲከለክላቸው ሌላ የሚያመልኩበት ቦታ እንዱሰጣቸው ጠየቁት። የሐዋርያት አለቃ ወደሆነው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስና ወደ ሐዋርያትም ሁሉ ስለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ጉዳይ መልእክትን ላኩ፤ ሐዋርያትም ክብር ይግባውና ያለ ጌታችን ፈቃድ ምንም ምን እንደማይሠሩ ተናገሩ። ነገር ግን የሚሠሩትን እግዚአብሔር እስኪያስረዳቸው ድረስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለዩና እየማለዱ አንድ ሱባኤ ይጾሙ ዘንድ ወደ ሃይማኖት የተመለሱ አሕዛብን አዘዙአቸው።

በሱባዔውም ፍጻሜ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸላቸውና ሐዋርያቱን ሁሉ ከየሀገረ ስብከታቸው በደመና ሰበሰባቸው። ከከተማ በስተምሥራቅ በኩልም አውጥቶ የቤተ ክርስቲያንቱን ቦታና መሠረት ወሰነላቸው። በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስምም ያለ እንጨት ያለ ጭቃና ያለ ውኃ ከሦስት ደንጊያዎች አነጻት። የተሠራችዋ ቤተ ክርስቲያንም ሃያ አራት ክንድ ቁመት፣ ዐሥራ ሁለት ክንድ ወርድ የነበራትና ሦስት ክፍል ማለትም መቅደስ፣ ቅድስትና ቅኔ ማኅሌት ነበራት። (መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፩ ቀን)

ማኅደረ ጻድቃን፣ ጉባኤ መላእክት ቅዱሳን፣ ምስካየ ምእመናን ንጹሓን፣ ወሀቢተ ንጽሕ ለኃጥኣን፣ መርዓተ ክርስቶስ፣ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹አደባባይዋን ስለ ክርስቶስ በተጋደሉ በሰማዕታት ደም የቀጠረች፣ በሥቃይ የማያዘነብሉ፣ በምሳርና በመጥረቢያ የማይፈቱ፣ ስለክብራቸውም የሚያበሩ የጳዝዮን ደንጊያዎች፣ ስለ ደማቸው መቅላት ደስ የሚያሰኙ የሰንፔር ዓለቶች፣ ስለ ምስክርነታቸው የጠሩ የወርቅ ፈርጦች፣ ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ምሰሶዎቿ ያደረገች፣ በሮቿ ነቢያት የሆኑላት ቤተ ክርስቲያን ማን ናት›› በማለት የገለጻት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ነው። (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ ፬፻፵፯)

ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ ‹‹ሃሌ ሉያ ተቀደሲ፤ ወንሥኢ ኃይለ፤ ኦ ቤተ እግዚአብሔር እስመ ናሁ ንጉሥኪ በጽሐ ዘያበርህ ለኪ በኃይሉ፤ ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ፤ ለዛቲ ቤት ሐነጻን ወልድ ለዛቲ ቤት፤ ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ፤ ቤተ እግዚአብሔር ሆይ ተቀደሺ፤ ኃይልንም ልበሺ፤ ንጉሥሽ እያበራ ወደ አንቺ ደርሷልና፡፡ ይህቺን ቤት አስቀድሞ አብ ሠራት፤ ወልድ አነጻት፤ መንፈስ ቅዱስ ፈጸማት›› በማለት አብ የሠራት፣ ወልድ በቀራንዮ ያነፃት፣ መንፈስ ቅዱስ ፍጽምት ያደረጋትና በሥላሴ መሠረትነት የተሠራች እንደሆነች ያስተምረናል። (ድጓ)

ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቤተ ክርስቲያን በመስቀል ላይ ስለመታነጽዋ እንዲህ ይላል፦ ‹‹ሰማያዊው ሙሽራ ክርስቶስ በመስቀሉ አንቀላፍቶ ሳለ ጎኑ በጦር ሲወጋ ልክ ከአዳም ጎን ሔዋን እንደተገኘች እንዲሁ የእርሱ ሙሽራ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች። የአዳም ፈጣሪ በሞት እንቅልፉ አዲሲቱን ሔዋንን ፈጠረልን፤ ለአዳም ልጆች ልክ እንደ እናት ሆና ታገለግላቸው ዘንድ፣ በቀዳማዊቱ ሔዋን ምትክ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃና ደም መንፈሳውያን ልጆችን የምታፈራ እናት ተሰጠችን። የንጉሥ ልጅ በጎልጎታ በደሙ ሠርግን አሳረገ፤ በዚያም ቀን የተባለችውን ድንግል የእርሱ ትሆን ዘንድ ታጨችለት፤ የንግሥና ቀለበቱን እጆቹ በተቸነከሩበት ቀዳዳዎች አጠለቃቸው፤ በእጆቹም የሙሽሪትን እጆች አጥብቆ ያዛቸው፤ ምክንያቱም በእርሱ ሕማም ጊዜ ለእርሱ ያላትን ፍቅር ተመልክቶአልና የእርሱ ትሆን ዘንድ በቀኙ አስቀመጣት።›› (እነኋት ክርስትና በሽመልስ መርገያ)

የቤተ ክርስቲያን ልጆች አስተዋላችሁን? በጽርሐ አርያም የምትመሰል ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ያጫት የእርሱ ሙሽራ እንደሆነች? ሙሽራ በሙሽርነቷ አምራ፣ ተውባ፣ ንጽሕት ሆና እንድትገኝ ቤተ ክርስቲያንም የአማረች፣ የተዋበች፣ ንጽሕት፣ ክብርት ሆና የወርቅ ልብስ ለብሳና ተጎናጽፋ ሙሽራዋን የምትጠብቅ ስንዱ እመቤት ናት። ‹‹ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም።›› እንዳለ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን። (መኃ.፬፥፯) ቤተ ክርስቲያን የሙሽርነት ቀለበቷን ዘወትር ከፍ አድርጋ ለዓለም ሁሉ የምታሳይ ወረት የሌለባት ድንቅ ሙሽሪት ናት፤ ቀለበቷም ሙሽራዋ የነገሠበት ቅዱስ መስቀል ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር በመስቀሉ አጥር ተከልላም ትኖራለች። ‹‹መስቀል ለቤተ ክርስቲያን ዓምዳ ወድዳ፣ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን መሠረታ፣ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን ወልታሃ ወኲናታ፣ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን ሐፁራ ወጥቅማ፣ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን የማና ወፀጋማ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን ቅድሜሃ ወድኅሬሃ፣ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን ብርሃና፤ መስቀል ለቤተ ክርስቲያን መሠረትና ምሰሶዋ፣ ጋሻና ጦሯ፣ አጥሯና አዳራሿ፣ ቀኟና ግራዋ፣ ፊቷና ኋላዋ፣ ብርሃኗ ነው›› እንዳለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ውዳሴ መስቀል ዘሰኑይ) ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ከሁሉ ነገር በላይ የሆነውን መስቀልን ስለያዘች መስቀልን ከፍ አድርጋና ጉልላቷ ላይ ሰቅላ ጠላትን እያሸነፈች እንዲሁም የገሃነም ልጆች ሳይችሏትና ሳይበረታቱባት ጸንታ የምትኖረው ለዚህ ነው።

እግዚአብሔር በትንቢተ ኢሳይያስ ‹‹ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች፦ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ›› በማለት እንደ ተናገረ ንጽሕት እምንጹሐን፣ ቅድስት እምቅዱሳን፣ ልዕልት እምልዑላን በሆነችው በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የመጀመርያዋን ቤተ ክርስቲያን ሠራት። (ኢሳ.፶፮፥፬-፮) ቅዱስ ሥጋው የሚፈተትባት ነውር ነቀፋ የሌለባት በገነት እንበላው የነበረውን ዕፀ ሕይወት እንበላባት ዘንድ ገነት ቤተ ክርስቲያንን በምትናገረዋ ገነት የሐዋርያት የስብከታቸው ሞገስ በሆነች በእመቤታችን ስም ሠራት። ዕፀ ሕይወትም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፤ ‹‹በእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ ከፈለነ ንብላ እምዕፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ፤ ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን፤ ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን፤ ይኸውም እኛን ስለመውደድ መጥቶ ያዳነን የክርስቶስ ክቡር ሥጋው ክቡር ደሙ ነው›› እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)

በቤተ ክርስቲያን ወንጌል እንዲነበብ፣ እንዲተረጎም፣ መንፈሳዊ ነገር እንዲሠራ በእናቱ በድንግል ማርያም እም አነጻት፤ እርሷ ወንጌሉን ያስገኘች ንጽሕት ፊደል ናትና። ‹‹ትመስሊ ፊደለ ወትወልዲ ወንጌለ፤ ፊደልን ትመስያለሽ፤ ወንጌልን ትወልጂያለሽ›› እንዲል። (መጽሐፈ ሰዓታት) ደሙ የሚቀዳባት ሥጋው የሚቆረስባትን ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ እንዲህ እያለ ይማፀናታል፤ ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊት ዓውድ መዝገበ ሥርናይ እንበለ ክርዳድ ምስአል ወምስጋድ ምጥባሐ ሥጋሁ ለወልድ፤ የወልድ ሥጋ መፈታቻ መንፈሳዊት አደባባይ እንክርዳድ የሌለብሽ የሥንዴ መዝገብ መለመኛና መስገጃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያ ሆይ ለምኝልን›› በማለት ዘወትር ራሷ ከሆነ ከክርስቶስ ታምልደን ዘንድ መማፀኛ አድርጎ የሰጠንን ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሰአሊ ለነ፤ ለምኝልን›› ማለት እንዳለበን ይነግረናል። (መጽሐፈ ሰዓታት)

በመጨረሻም ቅዱስ ያሬድ ‹‹ወደ ሮሜ አገር ወረድኩኝ፤ ቤተ ክርስቲያንን አየኋት፤ አወኳት፤ አፈቀርኳት›› እንዳለ ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን ደስ እያለን እንሒድ! (ጾመ ድጓ) በዚያም ቤተ ክርስቲያንን የሙሽርነት ልብስ ለብሳ እንያት! ማን እንደሆነችም እንወቃት! ያኔ እናፈቅራታለን፤ እንወዳታለን። ስለ እርሷ እንደ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የቤትህ ቅናት በላኝ›› በማለት መንፈሳዊ ቅናት እንቀናለን፤ (መዝ.፷፰፥፱) ሙሽራ ብቻዋን ትሆን ዘንድ መልካም አይደለምና ሚዜዎቿ ሁነን እንኑር!

አምላካችን እግዚአብሔር እግራችንን ወደ ሰላም መንገድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያቀና ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሆይ ለምኝልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!