‹‹አቤቱ በፊትህስ ባለሟልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈው›› (ዘፍ.፲፰፥፫)

ዲያቆን ዮሐንስ ተመስገን

ሐምሌ ፮፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ለሰይጣን የዘወትር ሥራው ክፋት ነው፤ በጎ ነገርን ሁሉ መጥላት ልማዱ መሆኑን የተረዱት አባቶች ‘ጸላኤ ሠናያት’ ብለውታል፤ የደግነት ጠላቷ ነውና አባታችን አብርሃምን ፈተነው። አብርሃም ደግ ሰው ነው፤ ለብዙዎችም ምሳሌ ሁኗል። ለጋስም ነበር፤ ድንኳኑን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ተክሎ ብዙዎችን አብልቷልና። ቸርም ስለሆነ ለሚያውቀውም ለማያውቀውም ዘወትር በድንኳኑ ያሳርፋ ነበር፤ ምስካየ ኅዙናን ነው፤ ያዘኑ የተከዙ በቤቱ ተጠልለዋልና።

አስቀድመን የበጎ ነገር ጠላት ያልነው ሰይጣን ይህን የአብርሃምን መልካምነት አልወደደውም። ይፈትነው ዘንድም አሰበ። በመንገድ ላይ ተቀምጦ ራሱ የተፈነከተ መስሎ ደም ለበሰ። ጥንቱን የአብርሃምን ግብር የሚያውቁ ሰዎች መጡ። አብርሃምን ይፈትነው ዘንድ የሚተጋው ሰይጣንም ‹‹እንደ በፊቱ የሚመግበው፣ እንግዳ የሚቀበለው አብርሃም ዛሬ ተለውጧል፤ ወደ ድንኳኑ የሚገሰግሱትን ይደበድባል፤ እኔንም በደም ያጨቀየኝ እርሱ ነውና አትሔዱ›› ማለቱን ያዘ። አብርሃም ያለ እንግዳ አይበላምና በረኃብ ልቅጣው ብሎ ይህን አደረገ።

በዚህ ክፉ የሐሰት ወሬም ለተከታታይ ቀናት ከቤቱ እንግዳ ጠፋ። አብርሃምም ከእህል ራሱን ከለከለ፤ በቤቱ ታዛ ሥር ብቻውን በልቶ አያውቅምና። ይህን የአብርሃም ለእግዚአብሔር እንግዳ ልዩ ፍቅር የሚያውቀው ሥላሴ ይጎበኘው፣ በቤቱም ታዛ ሥር ይስተናገድ ዘንድ ፈቃዱ ሆነ። ሐምሌ ፯ በአብርሃም ቤት ሥላሴ እንግዳ ሁነው መጡ:: (ዘፍ.፲፰፥፩) ይባርኩት እና የናፈቀውን ልጅ ይሰጡት ዘንድ ወደ እርሱ መጡ።

ሥላሴ ሊቃውንት ‘የወይራ ዛፍ’ ብለው በተረጎሙት በመምሬ ዛፍ ሥር ተገለጠ፤ አብርሃምም ጎልማሳ እንግዶች መስለውት ወደ ቤቱ ወስዶ ያስተናገዳቸው ዘንድ ወደ እነርሱ ሮጠ፤ ‹‹ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ሮጠ›› እንዲል (ዘፍ.፲፰፥፪)። ቀርቦም ከምድር ወድቆ እጅ ነሣ፤ እንዲህም አላቸው። ‹‹አቤቱ በፊትህስ ባለሟልነትን አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈው፤ ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁን እንጠባችሁ።›› (ዘፍ.፲፰፥፫)

አብርሃም በዚህ ቃል ምሥጢረ ሥላሴን ገልጧል፤ በፊትህ ብሎ አንድነቱን፣ እግራችሁን ብሎ ሦስትነቱን አስረድቷል፡፡ (ትርጓሜ ዘፍጥረት ምዕራፍ ፲፰) ‹‹ወደ ቤቴ ከገባችሁ በኋላ ወደ አሰባችሁት ትሔዳላችሁ›› ባለው መሠረት አጋእዝተ ዓለም ቅድስት ሥላሴ ቤቱን ባረኩለት፤ ይስሐቅንም ሰጡት። ‹‹ባለሟልነትን አግኝቼ ቢሆን›› ማለትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ነው። እግዚአብሔር ወልድ ከእርሱ ዘር እንዲወለድ ፈቃዱን ሲለምን ባለሟልነትን (እመቤታችንን) በዘሩ ያገኝ ዘንድ በቤቱ ጥላ እንዲያርፍ ጠይቋል። መጽሐፍ የእመቤታችንን የባለሟልነትን ባለቤትነት ሲገልጥ ‹‹እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፤ ባለሟልነትን በእግዚአብሔር ዘንድ አግኝተሻልና›› ይላል። (ሉቃ.፩፥፴፣ ውዳሴ ማርያም ዘሰሉስ) አብርሃምም እመቤታችን ከእርሱ ዘር ተወልዳ ትወልደው ዘንድ ፈቃዱ እንዲይሆን ለመነው። አምላካችንም የለመኑትን የማይነሳ ነውና ይስሐቅን ሰጥቶ ከዘሩ ተወልዶ ጸሎቱን ፈጽሞለታል፤ እግዚአብሔርን ጠይቆ ያልተቀበለ ማን አለ?

ጌታችን በወንጌል ‹‹በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል›› እንዳለ፤ (ማቴ.፲፰፥፭) የሰው ልጅ ወንድሙን እንደቀበል የሥላሴ ፈቃድ ነው፤ ይኸውም ሥላሴን መቀበል ነው፤ ለዚህም ምስክሩ አብርሃም ነው።

አባታችን አብርሃም ሥላሴን ‹‹ባርያህን አትለፈው›› ብሎ መለመኑ ብዙ ነገር ያስተምረናል። አግዚአብሔርን “አትለፈኝ” ብለን ሕግና ትእዛዛቱን ልንጠብቅ ይገባናል። በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ሰው በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ ሰው ነው። ‹‹ሕግህ ለመንገዴ መብራት ለእግሬ ብርሃን ነው›› እንዳለ ነቢዩ ዳዊት ሕገ እግዚአብሔርን የሚጠብቃት ሰው ለእግሩ ብርሃን ትሆነዋለች።  (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭) እንዲህ ከሆነ ደግሞ የአገልጋይነትን ሞገስ ያገኛል።

እንግዳ መቀበልን ያስተማረን ራሱ ሥላሴ በአብርሃም ቤት እንግዳ ሁኖ ነው፤ በተመሳሳይ ታሪክም በአብርሃም ወንድም በሎጥ ቤት መላእክት እንግዳ ሁነው ነበር፡፡ (ዘፍ.፲፱፥፩) አልዓዛርም በባለጸጋው ነዌ ቤት እንግዳ ነበር፡፡ (ሉቃ.፲፮፥፳-፳፭) አብርሃምና ሎጥ አክብረው በመቀበላቸው በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝተዋል። ነዌ በመናቁ ምክንያት በአምላካችን ፊት የተናቀ ሁኗል፤ ዛሬም በእንግድነት ማን እንደሚመጣ አናውቅም፤ ሥላሴ፣ መላእክት፣ ቅዱሳን…. ሊሆኑ ይችላሉ፤ ብዙ ታሪክ የሚነግረን እርሱን ነው።

በእርግጥ በዘመናችን እንግዳ ለመቀበል ብዙ ፈታኝ ነገሮች አሉ፤ ሌቦች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ዝሙተኞች… እንግዳ ሁነው ሊመጡ ይችላሉ። መልሱ አጭር ነው፤ ይህን እንድንመዝንበት የሚያስተውል ለብዎ ተሰጥቶናል። አብርሃምን እንደፈተነው ያለ ሰይጣን ዛሬም ሊፈትነንና ተስፋ ሊያስቆርጠን ስለሚችል መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው።

ቢያንስ ቢያንስ ግን እንደ አብርሃም ደግ መሆን ባንችል ለቅን ሰዎች እንቅፋት አንሁን። ሰይጣን መንገድ ላይ ተቀምጦ ራሱን ገምሶ “አብርሃም ደበደበኝ” እንዳለው መንገድ ላይ ተቀምጠው “እገሌ እንዲህ ነው፤ እገሌ እንዲያ ነው” በማለት ዕድሜያቸውን ሙሉ ዕንቅፋት የሚሆኑ ሰዎችም ሊኖሩ ስለሚችሉ መጠንቀቅ ተገቢ ነው። “አባታችን አብርሃም ነው” በማለት ቢናገሩም መልካም ነገርን ግን የሚቃወሙትን በወንጌል አይተናል። ክርስቶስንም በዚህ ቃል ተቃውመውት ነበር፤  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ‹‹አብርሃምን አታውቁትም›› አላቸው፤›› (ዮሐ.፰፥፴፰-፵፩) አብርሃምን መቀበልስ በሰይጣን ክፉ ወሬ ሳይደናገጡ ሁል ጊዜ ለቅንነት መሰለፍ ነውና።

ከሥላሴ ቡራኬ ከአብርሃም በረከት ይክፈለን!!