አበው ነቢያት!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ኅዳር፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  እንዴት አላችሁ! መንፈሳዊ ሕይወት እንዴት ነው? በትምህርት ቤት፣ በሠፈር ውስጥ እንዲሁም በተለያየ ቦታ ስትገኙ በሥርዓት እና በአግባብ እንደምትኖሩ ተስፋችን እሙን ነው፤ ታዛዥና ትሑት ለሰዎችም አሳቢ ልጆች መሆን አለባችሁ፤ ሁል ጊዜ አበክረን የምንነግራችሁ ‹‹እውቀት ማለት ተግባር ነው…›› እንዲሉ አበው የተማርነውን በተግባር እንድትፈጽሙ ነው፡፡

ልጆች! በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊውም ትምህርት ተምራችሁ ማደግ አለባችሁ፤ ያኔ ለራሳችሁ ከዚያም ለቤተ ሰብ እንዲሁም ለአገራችሁ መልካም ነገርን መሥራት ይቻላችኋል፡፡ መልካም!!! ለዛሬ የምንነግራችሁ ስለ ቅዱሳን ነቢያት ነው፡፡

ነቢይ ማለት ኃላፍያትን (ያለፈን) የተሠራውን ምሥጢር እንዲሁም መጻእያትን (ወደ ፊት የሚሆነውን) የሚሠራውን ምሥጢር የሚያውቅ፣ ሰባኪ፣ መምህር ማለት ነው፣ መንፈሰ ትንቢት ያደረበት ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፳)

ነቢይ አንድ ሲሆን ነቢያት ደግሞ የብዙዎች መጠሪያ ነው፤ ሀብተ ትንቢት (ትንቢት የመናገር ሀብት) እግዚአብሔር ለመረጣቸው አባቶች በጸጋ ይሰጣቸዋል፤ ነቢያትም ይሆኑና የቀደመው ታውሷቸው የሚመጣው ተገልጦላቸው ይተነብያሉ፡፡

ትንቢት ማለት ራእይ፣ ንግግርና ገና ወደ ፊት የሚመጣን ነገር፣ አስቀድሞ የሚታይ፣ የሚገለጥና ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፮፻፳)

ነቢያት በተለያየ ዘመን ነበሩ፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት ሊሠራ ያለውን ይገልጥላቸውና ለሕዝቡ ይናገሩ ነበር፤ (ይተነብዩ ነበር) ለምሳሌ ከተናገሩት ትንቢት ብንመለከት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን እንደምትወልድ፣ ጌታችንን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህም ምድር ላይ የሚያደርጋቸውን ሥራዎችና ገቢረ ተአምራትን ነቢያት አባቶቻችን አስቀድመው ተንብየው ነበር፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ እመቤታችን ጌታችንን በድንግላና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልደው እንዲህ ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ ‹‹….እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች…፡፡›› (ኢሳ.፯፥፲፬)

ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን አስቀድሞ እንተነበየው ጊዜው ሲደርስ ትንቢቱ ተፈጸመና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በብሥራተ ገብርኤል ጌታችንን በድንግልና ወለደችልን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹.. ብዙ ነቢያት ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ፈለጉ…፡፡›› (ማቴ.፲፫፥፲፮) አያችሁ ልጆች! የጌታችንን መወለድ ነቢያት አስቀድመው መናገርም ብቻም ሳይሆን ማየትም ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ዕረፍተ ሞት ገትቷቸው አላዩም።

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት፣ በተናገሩት ትንቢት ዐበይት ነቢያትና ደቂቀ ነቢያት ተብለው ይጠራሉ፡፡

ዐበይት ነቢያት

ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ ኤርምያስ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ ነቢዩ ዳንኤል ይባላሉ፤ (ትምህርተ ነቢያት ክፍል አንድ ገጽ ፲፰)

ደቂቀ ነቢያት

ነቢዩ ሆሴዕ፣ ነቢዩ አሞጽ ፣ ነቢዩ ሚክያስ፣ ነቢዩ ዮናስ ፣ ነቢዩ ናሆም፣ ነቢዩ አብዩድ ፣ነቢዩ ሶፎንያስ፣ ነቢዩ ሐጌ፣ ነቢዩ ኢዩኤል፣ ነቢዩ ዕንባቆም ፣ ነቢዩ ሚልክያስ፣ ነቢዩ ዘካርያስ ናቸው፡፡ (ዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንድምታ መግቢያ)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ነቢያት እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ በዘመነ አበው የነበሩ ነቢያት፣ በዘመነ ነገሥታት የነበሩ ነቢያት ተብለውም የሚታወቁ ብዙ ነቢያት አሉ፤ ለምሳሌ ብንወስድ ንጉሥ ዳዊትን ቀብቶ ያነገሠው የሐና እና የህልቃና ልጅ ነቢዩ ሳሙኤል፣ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ለምን ጣዖት ይመለካል በማለት ሰማይ ዝናም እንዳይሰጥ ያደረገው (የለጎመው) ነቢዩ ኤልያስ እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ነቢዩ ኤልሳዕ ሌሎችም ነቢያት አሉ፤ የነቢያት ሁሉ አለቃ የሆነው ደግሞ ነቢዩ ሙሴ ነው፡፡  (ትምህርተ ነቢያት ክፍል አንድ ገጽ ፲፰)

ከላይ ዐበይትና ደቂቀ ነቢያት በማለት የገለጽናቸው በጻፉት መጻሕፍት መሠረት ነው፡፡ (የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስተማሪያ መጽሐፍ ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ገጽ ፹፰) ነቢያት  በየዘመናቸው በርካታ የሆኑ ትንቢቶችን ተናግረዋል፤ ከዚህም ጋር በተጓዳኝ ጾምን ይጾሙ ነበር፤ የተናሩት ትንቢት ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ስለ ነበር ‹‹ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን›› እያሉ ጾምን ይጾሙ ነበር።

አያችሁ ልጆች! ነቢያት ያስተምራሉ፤ ሕዝቡ ሲያጠፋ ይገሥጻሉ፤ የሕዝቡን ልመና በጸሎታቸው ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ አማካኝነት ለሕዝቡ ፈቃዱን ይገልጣል፤ በድለው ከሆነ ይቅር ይላል፤ የሚፈልጉትንም ይሰጣል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ነቢያትን ስናነሣ አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውን የነቢያት ጾም (የገና ጾም) ተብሎ የሚታወቀውና ከኅዳር ፲፭ (ዐሥራ አምስት) ቀን ጀምሮ እስከ ልደት በዓል (ታኅሣሥ ፳፱ /ሃያ ዘጠኝ/ዘመነ ዮሐንስ ከሆነ ደግሞ ታኀሣሥ ፳፰) ድረስ የሚጾመውን ጾም ነው፡፡

ልጆች! የጾም ወቅት በነቢያት ስም መሰየሙ ነቢያቱ ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን›› እያሉ የጾሙት ጾም ስለሆነ ነው፤ እኛ ደግሞ ጌታችን ነቢያት በተናገሩት ትንቢት፣ እርሱም በገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ‹‹ወርዷል፤ ተወልዷል፤ አድኖናል›› እያልን እንጾመዋን፡፡ (ጾም፣ ጸሎት ምጽዋት መጽሐፍ) 

እንግዲህ ውድ እግዚአብሔር ልጆች! ስለ አበው ነቢያት ለግንዛቤ ያህል ጥቂት ነገርናችሁ፤ ነቢያት የሚባሉት እነማን እንደሆኑ፣ ትንቢት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተመለከትን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ነቢያት በረከታቸውን ያድለን፤ አሜን!

ምንጭ፡-  ጾም፣ ጸሎት ምጽዋት መጽሐፍ ትምህርተ ነቢያት ክፍል አንድ መምህር ብዙነህ ሺበሺ ፳፻፲፩ ዓ.ም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!