አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – የመጨረሻ ክፍል

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፫. ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን

የኒቅያ ጉባኤ ከተፈጸመ ከሦስት ዓመት በኋላ ማለት በ፫፻፳፰ ዓ.ም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ ከመሞታቸው አስቀድሞ በተናዘዙት ቃል መሠረት፣ በኒቅያው ጉባኤ የተዋሕዶ ጠበቃ የነበሩትና በኒቅያው ጉባኤ ትምህርተ ሃይማኖትን (ጸሎተ ሃይማኖትን) ያረቀቁት ታላቁ አትናቴዎስ በምትካቸው በጳጳሳት፣ በካህናትና በሕዝብ ሙሉ ድምፅ ተመርጠው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡ ፓትርያርክ አትናቴዎስ በኒቅያ ጉባኤ ጊዜ የአርዮስና የተከታዮቹን የክሕደት ትምህርት በመቃወም ባቀረቡት ክርክርና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መጠበቅ ባበረከቱት ተጋድሎ በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ‹‹ታላቁ አትናቴዎስ›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን በኒቅያ ጉባኤ ከተወገዙ በኋላም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘመቻቸውን ከበፊቱ አብልጠው ስለ ቀጠሉ፣ ታላቁ አትናቴዎስ በጽሑፍና በቃል ትምህርት ለእነዚህ መናፍቃን ምላሽ መስጠታቸውን እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አላቋረጡም ነበር፡፡

የኒቅያ ጉባኤ እንደ ተፈጸመ አርዮስ እና የአርዮስ ተከታዮች ሁሉ በንጉሡ በቈስጠንጢኖስ ትእዛዝ ወደ ግዞት ተልከው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮሳውያን የንጉሡንና የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖችን ለመወዳጀትና የእነርሱን ድጋፍ ለማግኘት ይሯሯጡ ጀመር፡፡ ስለዚህም ከሁለት ዓመት በኋላ ቆስጣንዲያ በተባለችው በንጉሡ እኅት እና የንጉሡ ወዳጅ በነበረው በኒቆምዲያው ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ አማካይነት ብዙዎቹ አርዮሳውያን ከግዞት እንዲመለሱ ታላቅ ሙከራ ተደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት አርዮስና አያሌ አርዮሳውያን ከግዞት ተመለሱ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ያወካት የነገሥታቱ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነበር፡፡ በጉባኤ ሲኖዶስ የተወገዘው አርዮስ ከውግዘት እንዲፈታና ወደ እስክንድርያ ተመልሶ በቤተ ክርስቲያን በየነበረው ሥልጣን አገልግሎቱን እንዲቀጥል ንጉሡ ለሊቀ ጳጳሱ ለአትናቴዎስ ትእዛዝ አስተላለፈላቸው፡፡ ንጉሡ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፈው ‹‹አርዮስ ከክሕደቱ ተመልሷል›› ብለው ወዳጆቹ ያስወሩትን ወሬ በመስማትና ‹‹የአርዮስ የእምነት መግለጫ ነው›› ተብሎ የቀረበለትን ግልጽ ያልሆነ መረጃ በመመልከት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን መግለጫ አርዮስን ያወገዘው ሲኖዶስ መርምሮ ሲያጸድቀው ነበር – ከክሕደቱ መመለሱ የሚታወቀው፡፡

በ፫፻፳፱ ዓ.ም የአርዮስ ደጋፊ በነበረው በኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ የተመራውና አርዮሳውያን በብዛት የነበሩበት ጉባኤ ተሰብስቦ ‹‹አርዮስ ከውግዘቱ ተፈቷል›› በማለት ወሰኑ፡፡ የውሳኔአቸውን ግልባጭ በማያያዝም አትናቴዎስ አርዮስን እንዲቀበለው ንጉሠ ነገሥቱ መልእክት አስተላለፈ፡፡ አትናቴዎስ ግን የንጉሡን ትእዛዝና የአርዮሳውያንን ጉባኤ ውሳኔ አልቀበልም አሉ፡፡ ያልተቀበሉበትንም ምክንያት በዝርዝር ለንጉሡ ጻፉ፡፡ አርዮሳውያንና መንፈቀ አርዮሳውያንም የአትናቴዎስን እምቢታ (የንጉሡን ትእዛዝ አለመቀበል) መነሻ በማድረግ አትናቴዎስን እና ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን መሪዎችን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ለማጣላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አደረጉ፡፡ አርዮስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ወደ ቀድሞው የክህነት ሥልጣኑ እንዲመለስ ንጉሠ ነገሥቱ ቈስጠንጢኖስ ያዘዘውን ትእዛዝ አትናቴዎስ ባለመቀበላቸውና መንግሥት በአርዮስ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በመቃወማቸው የተነሣም ንጉሠ ነገሥቱ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፡፡

ፓትርያርክ አትናቴዎስ የአርዮስ መወገዝም ሆነ መፈታት የሚመለከተው ቤተ ክርስቲያንን እንጂ ቤተ መንግሥትን አለመሆኑን ገልጠው ከመጻፋቸውም በላይ፣ ‹‹በሲኖዶስ የተወገዘ በመንግሥት ሳይሆን በሲኖዶስ ነው መፈታት ያለበት›› እያሉ ይናገሩ ስለ ነበር ንጉሡ በዚህ እጅግ አልተደሰተም ነበር፡፡ ንጉሡ በአትናቴዎስ ላይ መቆጣቱን የሚያውቁ አርዮሳውያንም አትናቴዎስን በልዩ ልዩ የሐሰት ክሶች ይከሷቸው ጀመር፡፡ ከሐሰት ክሶቹም አንዱ ‹‹ከግብጽ ወደ ቊስጥንጥንያ ስንዴ እንዳይላክ አትናቴዎስ ከልክለዋል›› የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‹‹በንጉሡ ላይ ለሸፈቱ ሽፍቶች አትናቴዎስ ስንቅና መሣሪያ ያቀብሉ ነበር›› የሚል ነበር፡፡ ሌሎችም ሞራልንና ወንጀልን የሚመለከቱ የሐሰት ክሶችም ቀርበውባቸዋል፡፡

ሆኖም ግን ንጉሠ ነገሥቱ ቈስጠንጢኖስ አትናቴዎስን ለመበቀል ጥሩ አጋጣሚ ስላገኘ በአትናቴዎስ ላይ የቀረቡት ክሶች በጉባኤ እንዲታዩ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤውም በ፫፻፴፭ ዓ.ም በጢሮስ ከተማ ተካሔደ፡፡ አትናቴዎስም ማንንም ሳይፈሩ ወደ ጉባኤው ሔዱ፡፡ ጉባኤው እንደ ተጀመረም በአትናቴዎስ ላይ የቀረቡትን ክሶች መስማት ጀመረ፡፡ በዚህ ጉባኤ አብዛኞቹ አርዮሳውያን ስለነበሩ፣ አትናቴዎስ በተከሰሱባቸው ክሶች ሁሉ ነጻ ቢሆኑም በግፍ ወደ ግዞት ቦታ እንዲሔዱ ተፈርዶባቸው ትሬቭ (ፈረንሳይ ውስጥ የምትገኝ) ወደምትባል ቦታ ተጋዙ፡፡

፬. የአርዮስ ድንገተኛ ሞት

ፓትርያርክ አትናቴዎስን በግፍ ወደ ግዞት ቦታ እንዲሔዱ የፈረደባቸው የቂሣርያው ጉባኤ፣ ‹‹አርዮስ ተጸጽቶ ከክሕደቱ መመለሱን የሚያመለክት መጣጥፍ አቅርቧል›› በሚል ሰበብ አርዮስን ከግዝቱ ፈቶ ነጻ አወጣው፡፡ አትናቴዎስ ወደ ግዞት በመላካቸው አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን ምቹ ጊዜ አግኝተው ስለ ነበር አርዮስን ወደ ሀገሩ ወደ እስክንድርያ ለመመለስ ይሯሯጡ ጀመር፡፡ የአርዮስ ነጻ መውጣትም ንጉሡ በሚኖርበት በቊስጥንጥንያ በይፋ እንዲከበር በማሰብ አርዮስ በወዳጆቹና በደጋፊዎቹ ታጅቦ ወደ ቊስጥንጥንያ እንዲሔድ አደረጉ፡፡ በዚያም በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ከቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጋር እንዲቀድስና ወደ ክርስቲያን አንድነት መግባቱ በይፋ እንዲታወጅ ዝግጅት ተደርጎ ሳለ ሆዱን ሕመም ተሰምቶት ወደ መጸዳጃ ቤት ሔዶ በዚያው ቀረ፡፡ አርዮስ ስለ ዘገየባቸው ደጋፊዎቹ ሔደው ቢያዩት ሆድ ዕቃው ተዘርግፎ ሞቶ አገኙት፡፡ በዚህም ‹‹የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት በአርዮስ ላይ ተገለጠ›› ተብሎ በብዙ ሰዎች ዘንድ ታመነ፡፡ ሆኖም በአርዮስ ሞት የተበሳጩ አንዳንድ የአርዮስ ደጋፊዎች የእግዚአብሔርን ፍርድ አይተው ከክሕደታቸው በመመለስ ፈንታ ‹‹አርዮስ የሞተው በመድኃኒት ተመርዞ ነው›› ብለው ማውራትና ማስወራት ጀመሩ፡፡

፭. አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን የኒቅያን ውሳኔ ለመቀልበስ ያደረጉት ዘመቻ

የእስክንድርያው ፓትርያርክ ታላቁ አትናቴዎስ የክርስቶስን አምላክነት የካደውን የአርዮስን ሞት የሰሙት ያለ ፍትሕ በግፍ በተጋዙበት ሀገር ሳሉ ነው፡፡ ታላቁ ቈስጠንጢኖስም ብዙ ጊዜ በሕይወት አልቆየም፡፡ ንጉሡ ታሞ ግንቦት ፳፩ ቀን ፫፻፴፯ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ሦስቱ ልጆቹ ማለት ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ፣ ቆንስጣንዲያስ እና ቁንስጣ መንግሥቱን ለሦስት ተከፋፈሉት፡፡ ከሦስቱ ልጆቹ መካከል የምዕራቡን ክፍል ይገዙ የነበሩት ሁለቱ ማለት ኦርቶዶክሳውያኑ ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ እና ቁንስጣ ሲሆኑ፣ መናገሻ ከተማውን ቊስጥንጥንያ ላይ አድርጎ የምሥራቁን ክፍል ይገዛ የነበረው ደግሞ አርዮሳዊው ቆንስጣንዲያስ ነበር፡፡ ትልቁ ቈስጠንጢኖስ ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ ኅዳር ፳፫ ቀን ፫፻፴፰ ዓ.ም አትናቴዎስ ተግዘውበት የነበረበትን ሀገር ይገዛ የነበረው ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ አትናቴዎስን ከተጋዙበት እንዲመለሱ አደረገ፡፡ አትናቴዎስ ከግዞት ወደ እስክንድርያ ሲመለሱም ሕዝቡ እጅግ ተደስቶ በዕልልታና በሆታ ተቀበላቸው፡፡ አቀባበሉም ለአንድ ተወዳጅ ንጉሠ ነገሥት የሚደረግ አቀባበል ዓይነት ነበር፡፡

ፓትርያርክ አቡነ አትናቴዎስ በአርዮሳውያንና በመንፈቀ አርዮሳውያን ነገሥታት ያለ ፍትሕ በግፍ ለአምስት ጊዜያት ያህል ሕይወታቸውን በግዞት ነው ያሳለፉት፡፡ በእስክንድርያ መንበረ ጵጵስና በፓትርያርክነት የቆዩት ለ፵፮ ዓመታት ቢሆንም፣ ፲፭ቱን ዓመታት ያሳለፉት በግዞትና በስደት ነበር፡፡ ፓትርያርክ አትናቴዎስ ከዕድሜያቸው አብዛኛውን ዘመን ያሳለፉት ከአርዮሳውያን ጋር በመታገልና በመዋጋት ነበር፡፡ አንድ ታሪክ ጸሓፊም ‹‹ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ምድረ ርስትን ለማውረስ የጀመረውን ተግባር ከግቡ ሳያደርስ እንደ ተጠራ፣ አትናቴዎስም ከአርዮሳውያን ጋር ያደርጉ የነበረውን ትግል ሳይጨርሱ ነው ለሞት የተጠሩት፤›› በማለት የፓትርያርክ አትናቴዎስን ተጋድሎና የአገልግሎት ፍጻሜ ያስረዳሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ‹‹አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በጥንት ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር›› በሚል ርእስ በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል የተዘጋጀው ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በግንቦት ወር ፳፻፰ ዓ.ም ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል መቅረቡን፤ እንደዚሁም በኅዳር ወር ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፯ ሐመር መጽሔት፣ ከገጽ ፰ – ፲፬ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡