አርአያነት ያለው ተግባር በአዳማ ማእከል

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል በየጊዜው መልካም ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ማእከሉ በዚህ ዓመት ከፈጸማቸው አርአያነት ያላቸው ተግባራት መካከል ሦስቱን በዚህ ዝግጅት እናስታውሳችኋለን፤

ከወራት በፊት ማለት በመጋቢት ወር ፳፻፱ ዓ.ም ማእከሉ ከሞጆ ወረዳ ማእከል ጋር በመተባበር ኮምፒውተር ከነፕሪንተሩ ለሉሜ ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በስጦታ መልክ አበርክቷል፡፡ የንብረት ርክክቡ በተፈጸመበት መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የማእከሉ ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት ‹‹ማእከሉ ይህንን ድጋፍ ያደረገው የቤተ ክህነቱን አሠራር ወቅቱ በሚፈልገው መልኩ ማዘመን አስፈላጊ ስለኾነ፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያናችንን መዋቅር በሚቻለው አቅም ዅሉ የመደገፍና የማገዝ ሓላፊነት ስላለበት ነው›› በማለት ማእከሉ የኮምፒውተር ድጋፍ ያደረገበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ማእከሉ ኮምፒውተሩን ለወረዳ ቤተ ክህነቱ ሲያስረክብ

ቤተ ክርስቲያንን በዅለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ እና የቤተ ክህነቱ አሠራር ወቅቱን በሚዋጅ መልኩ እንዲቀላጠፍ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን እየሰጠ ያለው አገልግሎት የሚያስመሰግነው ትልቅ ተግባር መኾኑን በዕለቱ የተገኙት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ቀሲስ ሙሉጌታ ቸርነት ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገለት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ዋስይኹን ገብረ ኢየሱስም ማእከሉ ይህን ድጋፍ ማድረጉ ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተግባር እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተበረከተልን ኮምፒውተር የጽ/ቤታችንን አሠራር ዘመናዊ ከማድረጉ ባሻገር የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትም ያስችለናል›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ ስለ ተደረገላቸው ድጋፍም ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡

ገዳማውያኑ የሕክምና መድኀኒት እና ሳሙና ሲቀበሉ

በሌላ የአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ በማእከሉ አስተባባሪነት የአዳማ ከተማ ሆስፒታል ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ለሚገኙ ገዳማውያንና የአብነት ተማሪዎች ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የሕክምና አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ተግባር ለሰባ ተማሪዎች የእከክ በሽታ፤ ለዐሥራ አራት ተማሪዎች ቀላል የመተንፈሻ አካል ሕመም፤ ለዐርባ ስምንት ተማሪዎች የሆድ ትላትል፤ ለአራት አባቶች የቀላል ሕክምና ርዳታ ተደርጎላቸዋል፡፡

ገዳማውያኑ የአካባቢ ጤና አጠባበቅን የሚመለከት ትምህርት ሲማሩ

በተጨማሪም አንድ መቶ የንጽሕና መጠበቂያ ሳሙና ለገዳማውያኑ ተበርክቷል፡፡ እንደዚሁም ለአንድ መቶ አምሳ የአብነት ተማሪዎች የአካባቢ ጤና አጠባበቅን የሚመለከት ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ይህን አገልግሎት ለመፈጸም መድኃኒት እና ሌሎች ቁሳቁሶች የተገዙበት ወጪ የተሸፈነው በግቢ ጉባኤውና በበጎ አድራጊ ምእመናን እንደ ኾነ ማእከሉ ለዝግጅት ክፍላችን የላከው ዘገባ ያመላክታል፡፡

በቅርቡ ደግሞ ‹‹መልካም ሥራን አብረን እንሥራ›› በሚል መሪ ቃል ልዩ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ማእከሉ ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በአዳማ ከተማ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ምእመናንን በማስተባበር የደም እጥረት ላለባቸው ሕሙማን እና ወላድ እናቶች ደም መለገስ፣ የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ የመርሐ ግብሩ ክፍሎች ነበሩ፡፡ በርካታ ምእመናን ከፍተኛ የደም መጠን እንዲለግሱ በማድረጉ የአዳማ ከተማ የደም ባንክ ጽ/ቤት ማእከሉን አመስግኗል፡፡

በመርሐ ግብሩ በቍጥር ከአምስት መቶ በላይ የሚኾኑ በጎዳና የሚኖሩ ወጣቶችን እና ሕፃናትን ንጽሕና የመጠበቅ፤ ልብስ አሰባስቦ የማልበስና ምግብ የመመገብ ተግባር ተከናውኗል፡፡ ወደ ሥራ መሠማራት የሚፈልጉ ወጣቶች ሥራ እንዲጀምሩ ለማገዝም የሊስትሮ ዕቃ ከነቁሳቁሱ ማእከሉ አስረክቧቸዋል፡፡ በዕለቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል የግንዛቤ ማዳበርያ ትምህርትም በከተማው ትራፊክ ፖሊስ ባለሙዎች ቀርቧል፡፡

ምእመናን ደማቸውን ሲለግሱ

ማእከሉ ከላከልን መረጃ እንደ ተረዳነው የማእከሉ አባላት፣ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች፤ የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤት መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች፤ እንደዚሁም የአዳማ ከተማ ምእመናን በበጎ አድራጎት መርሐ ግብሩ ተሳትፈዋል፡፡ የአዳማ ከተማ ከንቲባ፣ የከተማው ባህልና ቱሪዝም፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች እና የደም ባንክ ጽ/ቤቶች ሓላፊዎች፤ የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ባለሙያዎች እና የኦሮምያ ቴሌቪዥን ድርጅት ጋዜጠኞች በሥፍራው ተገኝተዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ተግባሩ በተከናወነበት ዕለት ከሰባት መቶ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት መርሐ ግብር በአዳማ ከተማ ምክር ቤት አዳራሽ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዕለቱ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ለማ ኃይሌ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ ‹‹በርቱልን! እግዚአብሔር ይስጣችሁ! ባደረጋችሁት በጎ ተግባር በከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ስም የተሰማን ደስታ ከፍ ያለ ነው፤›› በማለት የማኅበሩን አገልግሎት አድንቀዋል፡፡ አቶ ለማ አያይዘውም አዳማ ከተማ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትኾን እና የተቸገሩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ‹‹ማኅበሩ ከጽ/ቤታችን ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተስፋ እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡

በጎዳና ለሚኖሩ ወገኖች የተዘጋጁ አልባሳት

የአዳማ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሓላፊ ወ/ሮ ዘይነባ አማን በበኩላቸው ‹‹ማኅበሩ ያደረገው አስተዋጽዖ ለሌሎች ቤተ እምነት ተከታዮችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ አርአያነት ያለውና ፈር ቀዳጅ ተግባር በመኾኑ በጽ/ቤቴ ስም ምስጋናዬን እያቀረብሁ፣ ወደ ፊትም ከማኅበሩ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን›› በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጎ አድራጎት የቤተ ክርስቲያን አንዱ ተልእኮዋ እንደ ኾነ፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የሚደግፍ ማኅበር በመኾኑ ይህን የበጎ አድራጎት አገልግሎት ለመስጠት እንደ ተነሣሣ የማእከሉ ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት አስገንዝበዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያንም ኾነ ለአገር እያበረከተ ያለውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎትም ሰብሳቢው በሰፊው አስረድተዋል፡፡

ወጣቶቹ አካባቢን በማጽዳት ሥራ ላይ

በመጨረሻም አገልግሎቱን በአግባቡ ለመስጠት እንዲቻል ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉ የመንግሥት ተቋማትና የሥራ ሓላፊዎች፤ ለበጎ አድራጊ ምእመናንና በአገልግሎቱ ለተሳተፉ ወገኖች ዅሉ ሰብሳቢው በማኅበሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

እኛም እንደ ዝግጅት ክፍል የቤተ ክርስቲያናችንን መንፈሳዊ ተልእኮ ይበልጥ ለማጉላት፤ የአገራችንን ስም በመልካም ጎን ለማስጠራት ይቻል ዘንድ አዳማ ማእከል ከላይ የተጠቀሱትንና እነዚህን የመሰሉ አርአያነት ያላቸው ተግባራቱን አጠናክሮ ቢቀጥል፤ የሌሎች ማእከላት፣ የሰንበት ት/ቤቶች እና የማኅበራት አባላትም ይህን የማእከሉን ፈለግ ቢከተሉ መልካም ነው እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡