አምስተኛው ዐውደ ርእይ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡

ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል ከግንቦት ፲፯-፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለስድስት ቀናት በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል ያዘጋጀው አምስተኛው ዐውደ ርእይ ግንቦት ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 በሰላም ተጠናቀቀ፡፡

ዐውደ ርእዩ ከተጀመረበት ዕለት እስከ ተጠናቀቀበት ሰዓት ድረስ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በብዙ ሺሕ ምእመናን፣ በመንግሥት ባለ ሥልጣናትና በሌሎች ቤተ እምነት ተከታዮችም ተጎብኝቷል፡፡

በዐውደ ርእዩ ከተሳተፉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሰቲት ሑመራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህ ዛሬ ያየነው በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀ ትልቅና አስደናቂ ዐውደ ርእይ ነባሩን ኢትዮጵያዊ ሥርዓት፣ ቅርስ፣ ታሪክና ትውፊት የሚገልጽ ዐውደ ርእይ ነው፤ በመኾኑም በጣም የሚወደድ፣ የሚከበርና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ይህንን ነባር ሥርዓት ለማጥፋት የሚጥሩ ብዙ ሐሳውያንን ስላሉ ኹላችንም ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል፤ ዐውደ ርእዩም እስከ ወረዳ ድረስ መታየት ይገባዋል ካሉ በኋላ በርቱ፤ ጠንክሩ፡፡ ኹሉም ነገር ለሰላም፣ ድህነትን ለማጥፋት፣ አንድነትን ለማጽናት፣ በአጠቃላይ ድንቁርናን ለማስወገድ መኾን ይኖርበታል በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የጋሞ ጎፋና የደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሲኖዶስ አባል ደግሞ ይህንን የመሰለ ያማረ ጉባኤ ሳይ በጆሯችን የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን እንመሰክራለን ተብሎ እንደተጻፈ የሰማሁትንና ያየሁትን መመስከር ግድ ይለኛል፡፡ ልጆቻችንን በዚህ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ያበቋቸው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው እኔ ለኩሸዋለሁ፤ እናንተ አንድዱት የሚል ቃል ተናግረው ነበር፡፡ በእውነትም እርሳቸው የለኮሱት መንፈሳዊ ሕይወት፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ነዷል፡፡ ከኢትዮጵያም ተርፎ በመላው ዓለም ተዳርሷልና ይህንን በማየታችን እጅግ በጣም ደስ ብሎናል ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር የሚቋረጥ ሥራ አይወድምና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአባቶቻቸውን አደራ እንደ ጠበቁ ልጆች ማኅበረ ቅዱሳንም የአባታችሁን የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን አደራ በመጠበቅ አገልግሎታችሁን ልትቀጥሉ፤ ፈተናዎችንም በመወያየትና በመነጋገር ልታልፏቸው ይገባል የሚል አባታዊ ምክር ለግሰዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የኾኑት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልም የዚህ ታላቅ ማዕድ ተካፋይ በመኾኔ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በእናንተ በልጆቻችንም መንፈሳዊ ኩራት ይሰማናል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት በአባቶች ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ እንዳለው ኹሉ ተዋሕዶ እምነታችን እንደዚህ ለሃይማኖታችሁ የምትቆረቆሩ የምታስቡ ልጆች በማግኘቷና እኛም እንደዚህ ዓይነት ትውልድ ባለበት ሰዓት በመነሣታችን እጅግ ደስ ይለናል ሲሉ ስሜታቸውን ከገለጹ በኋላ ማኅበሩ የሠራው ሥራ የሚያስመሰግነው ቢኾንም በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው እኛ ለጌታ የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ማለት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህ ሥራ የመጨረሻችሁ ሳይኾን የመጀመሪያችሁ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከእናንተ ጋር ናቸው፡፡ ከአባቶቻችሁ መመሪያ እየተቀበላችሁ ከዚህ የበለጠ እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ የሚል አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፡፡

ሌሎች ብፁዓን አበውም ማኅበረ ቅዱሳንን አስነሥቶ ሕዝበ ክርስቲያኑን በዚህ መልኩ እንዲሰባሰብና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ፣ ስለ ሃይማኖቱ እንዲማር በማድረጉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፤ በማኅበሩ ሥራ መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለወደፊትም ከአባቶች ጋር በመመካከር ከዚህ የበለጠ መትጋት እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው ምእመናን እንደገለጹልን በዝግጅቱ ከመደሰታቸው የተነሣ ከቤተሰቦቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በመኾን ስድስቱን ቀን በሙሉ በዐውደ ርእዩ ተሳትፈዋል፡፡ በዐውደ ርእዩ መሳተፍ የሚኖረውን ጠቀሜታ አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ ያደርግንላቸው ምእመናንም ዐውደ ርእዩ ኹሉም ምእመን ስለ ሃይማኖቱ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያኑና ስለ አገሩ ታሪክ እውቀት እንዲኖረው ከማድረጉ በተጨማሪ ራሱን እንዲያይና ድርሻውን በማወቅ የሚጠበቅበትን ሓላፊነት እንዲወጣ የሚያስችል ግንዛቤ ያስጨብጠዋል ብለዋል፡፡

ከአስተያየት መስጫ መዛግብት ላይ ከሰፈሩ ዐሳቦች ውስጥም ዐውደ ርእዩ በጣም አስተማሪ መኾኑን ገልጸው፣ የአዘጋጆቹን፣ የአስተናጋጆቹንና የገላጮቹን ጥንካሬ በማድነቅ እንደዚህ ዓይነቱ ዐውደ ርእይ በዐዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይኾን፣ በየክፍለ ሀገሩና በየወረዳው መዘጋጀት እንደሚገባው፤ ትዕይንቶቹም ቀለል ባለ መልኩ በብሮሸርና በሲዲ መልክ ለምእመናን መዳረስ እንደሚኖርባቸው አስተያየት የሰጡ ሰዎችን ዐሳብ በአብዛኛው አንብበናል፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ በዐውደ ርእዩ ላይ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ሥራዎች እንዲተዋወቁ ማድረጉ ያስመሰግነዋል፤ ለወደፊቱ እንደዚህ ዓይነት ዐውደ ርእይ ሲያዘጋጅ ከቤተ ክህነትና ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ ቢሠራ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ይኾናል የሚሉና ሌሎችም አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

በአንጻሩ የዐውደ ርእዩ ጊዜ ጠባብ መኾኑ፣ ማኅበሩ ኤግዚብሽን ማዕከሉ ውስጥ ለታዳሚዎች የሚኾን ምግብ ቤት ስላልተዘጋጀ፣ እንደዚሁም በትዕይንቶቹ አዳራሾች ውስጥ ጎብኝዎቹ ስለሚደራረቡና የልዩ ልዩ ትዕይንቶች ገላጮች ድምፅ ስለሚቀላቀል ለወደፊቱ ሰፊ ዝግጅት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተለየ ደግሞ ማኅበሩ ራሱን የሚያስተዋውቅበት የትዕይንት ክፍል ማዘጋጀት ነበረበት የሚል አስተያየት በጽሑፍም በቃልም ተነሥቷል፡፡

ከውጪ አገር ከመጡ ጎብኝዎች መካከል ማርቆስ ሀይዲኛክና ባለቤቱ አገራቸው ቡልጋርያ በሃይማኖታቸውም የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል መኾናቸውን ጠቅሰው በዚህ ዐውደ ርእይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ሥነ ጽሑፋዊ ጥበብ፣ የክርስቲያኖቹን ትጋትና መንፈሳዊ ሕይወት እንደዚሁም የአገሪቱን ሕዝብ ባህል እንደተረዱበት ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡

ከሌላ ቤተ እምነት ከመጡ ግለሰቦች መካከልም ማርሺያ ሲንግልተን የምትባል አንዲት አሜሪካዊት የፕሮቴስታንቲዝም እምነት ተከታይ በዚህ ዐውደ ርእይ በመሳተፏ እድለኛ መኾኗን ጠቅሳ በጉብኝቱም የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪክ የበለጸገና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ መኾኑን ከገለጸች በኋላ ዐዲስ እውቀት እንዳገኝ ስላደረጋችኹኝ አመሰግናለሁ የሚል አስተያየቷን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍራለች፡፡

በተያያዘ ዜና አንድ ጣልያናዊ ጎልማሳ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በዐውደ ርእዩ የኢትየጵያን ታሪክና የክርስትናን አስተምህሮ እንደተረዳበትና በመታደሙም ደስተኛ እንደኾነ ገልጾ፣ ዐውደ ርእዩ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት መኾኑን ከትዕይንቶቹ ይዘት መረዳቱን ከተናገረ በኋላ ማኅበሩንና አዘጋጆቹን አመስግኗል፡፡

በመጨረሻም በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 4፡00 ዐውደ ርእዩ ሲጠናቀቅ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች፣ የትዕይንት ገላጮች፣ የአብነት ተማሪዎችና ሌሎችም ድጋፍ ሰጪ አካላት በኤግዚብሽን ማዕከሉ ግቢ ውስጥ ተሰባስበው ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ እያሉ በሰላም ያስፈጸማቸውን ልዑል አግዚአብሔርን በዝማሬና በዕልልታ አመስግነዋል፡፡