ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው” (ዘፍ.፲፩፥፯)

ጥር ፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ በኃጢያት የተገነባውን የሰናኦር ግንብ ያፈረሱበትና አንድነታቸውንና ሦስትነታቸውን በግልጽ ያሳዩበት ቀን ጥር ሰባት የከበረ በዓል ነው፤ “እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። “ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።” እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተው። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ” እንዲል። (ዘፍ.፲፩፥፯-፱)

ከዚህ ቅዱስ ቃል የምሥጢረ ሥላሴን እንረዳለን፡፡ በስም በአካል በግብር ሦስት ናቸውና፤ የስም ሦስትነታቸው እንደምን ነው ቢሉ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፤ የግብር ሦስትነታቸውስ እንደምን ነው ቢሉ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ የመሆኑ ምሥጢር ነው፤ የአካል ሦስትነታቸውስ እንዴት ነው ቢሉ ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመሆኑ የሥላሴ ገጽ አካል ፊት እንደ ሰው ነውን ቢሉ አዎን፤ የሥላሴ አንድነታቸው ደግሞ በባሕርይ በህልውና በስፋት በምልዓት በርቀት መለኮት በልብ በቃል በእስትንፋስ ይህን በመሰለው ነው።

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን፡፡