‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››

ክፍል ስምንት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሰኔ ፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ተወዳጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ በሰላም አደረሳችሁ! በክፍል ስድስት ክብረ ምንኩስና ትናንት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ክብርና ሞገስ ያስገኘውን የቅድስና ፍሬና ያሳረፈውን አሻራ፣ በክፍል ሰባት ደግሞ ምንኩስና ዛሬ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እያጋጠመው ያለውን ተግዳሮት አንሥተን የተወሰኑ ችግሮችን ለማቅረብ ሞክረን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ክፍል ስምንትን አቅርበንላችኋልና ተከታተሉን!

፬. በዋዛ ፈዛዛ መጠመድ፡- ለመነኩሴ ቀርቶ ለአንድ ምእመንም ጊዜን ባልተገባ ሁኔታ ማባከን፣ በዋዛ በፈዛዛ በቧልት መጠመድ የተከለከለ ስለመሆኑ መምህራንም መጻሕፍትም ያስረዳሉ፡፡ ፍትሐ ነገሥት ‹‹መነኩሴ ሕይወቱን ሁሉ ለጾም ለጸሎት ለድካም፣ ለሥራ የሚያደርግ ዘወትርም እግዚአብሔርን ለማሰብ፣ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ ትርጓሜውን ለማወቅ፣ ወዳጆቹን ለመምሰል፣የቅዱሳኖቹን ገድል ለማንበብ የሚያደርግ ………..ለሚናገረውም ለሚሰማውም ጥቅም ከሌለው ነገር ሁሉ አንደበታቸውን እየጠበቁ ከበጎ ሥራ በቀር ለማሰብና ለመናገር የማይገባውን ወደ ሰውነታቸው እንዳያደርሱ አፋዊ ሰውነታቸውን ይይዙ ዘንድ ውስጣዊ ሰውነታቸውንም ይጠብቁ ዘንድ ይገባል….›› ይላል፡፡ (ፍት.መን. አን.፲፣ ገጽ ፫፻፷፩)

አሁን አሁን ግን ተናጋሪውንም ሰሚውንም የማያንጽ ረብ ጥቅም የሌለው አንዳች በዓለም ያለ ሰው ከሚያደርገው እንኳን ባነሰ ሁኔታ ፌዝ ዋዛ ፈዛዛ መናገር፣ ያልተገራና ያልታረመ ንግግር፣ ሳቅ ስላቅ በየቦታው ይሰማል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አንቀጽ ቁጥር ፫፻፸፮ ላይ ደግሞ ‹‹እርስ በርሳቸው፣ከሰውም ሁሉ ጋር ወደ ገበያና ወደ መንገድ ያለጸጥታ ኃፍረት በሌለው አካሄድ አይሂዱ፡፡ እርስ በርሳቸው እየሳቁ እየተጫወቱ፣በሚያሳፍርና በሰሐቅ ነገር አይነጋገሩ..›› ይላል፡፡

በመጽሐፈ ምዕዳን ላይ ደግሞ ‹‹መነኩሴ አይሳቅ፤ ፌዝ ነገር አይናገር፤ አይጫወት፤ ሀገር ለሀገር መንደር ለመንደር አይዙር፤ ሴት ካለችበት ቤት አይደር፤ ዘመድም ብትሆን ከሴት ጋር የሚኖር መነኩሴ መነኩሴ አይባልምና›› ይላል፡፡ ዛሬ ከሴት ጋር የሚኖሩ መነኮሳት ብዙ ናቸው፡፡ በቀላቢ ስም፣ በሠራተኛ ስም፣ በዘመድ አዝማድ ስም ብዙ መነኮሳት ከሴት ጋር ይኖራሉ፡፡ ዋዛ ፈዛዛ፣ ሳቅ ስላቅ፣ ፌሽታ ደስታ ደርቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ፣ ክብረ ምንኩስናን የሚያቃልል፣ ምእመናንን የሚያሸማቅቅ ተግባር ይፈጸማል፡፡ ይህ በየሚድያው አጀንዳ እስከሚሆን ድረስ ማለት ነው፡፡ በሕንጻ መነኮሳት መነኮሳትን የሚያረክሱ ነገሮች ተብለው ከተዘረዘሩ አምስት ነገሮች መካከል ከንቱ ነገሮችን መውደድ፣ ሴትን አተኩሮ መመልከት የሚል ነው፡፡

፭. በዘረኝነት አስተሳሰብ መጠመድ፡- ይህ የዘመናችን ትልቁ ደዌ ነው፡፡ ሀገራችንም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችን መከራ ላይ የወደቁበት፣ ልንፈታው ያልቻልነው ቋጠሮ፣ ልናልፈው ያልቻልነው እንቅፋት ዘረኝነት ነው፡፡ ዘረኝነት የጎጠኝነት አስተሳሰብ አካል ገዝቶ እግር አውጥቶ እየታየ ነው ፡፡ ነገሩን ከባድ የሚያደርገው ‹‹ምውት ዘተፈልጠ እምዓለም፤ ከዚህ ዓለም የተለየ ሙት›› የተባለው ዘሩን (ጎጡን) ቀርቶ ማንነቱን ሁሉ የካደ፣ እግዚአብሔር አባቴ ቤተ ክርስቲያን እናቴ መንግሥተ ሰማያት ርስቴ ጉልቴ ብሎ ሁሉን ትቶ ከሁሉ ተለይቶ የመነነው መነኩሴ ዘረኛ ሁኖ በዘር ተቧድኖ ለምእመናን የመከራ ምንጭ፣ ለብዙዎች የመውደቅ ምክንያት ሲሆን ማየት የከፋ ነው፡፡ መነኩሴ በዓለማዊ ስሙ እንኳን አይጠራም፤ ሀገሩ ወገኑ አይጠየቅም ነበር፡፡

፮.ቁጡ መሆን፣ ጥላቻ ማብዛት፣ ቂመኛ መሆን፡-

በጣም ትልቁ የዘመናችን መነኮሳት ፈተና ቁጡነት፣ ጥላቻ፣ ቂም መያዝ ክርክር፣ ፉክክር ብዙ ነገሮችን በመነኮሳት ላይ እናያለን፡፡ ይቅር ባይነት፣ ትሕትና፣ ፍቅር አንድነት፣ መተሳሰብ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ፣ ወንድሜ አንተ ልክ ነህ፤ እኅቴ አንቺ ልክነሽ የሚል የትሕትና፣ የግብረ ገብነት ችግር ይታያል፡፡
ይህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ከላይ እንደዳሰስነው፣ ትዕግሥቱ ያልተፈተነ፣ ጾር ያልጠፋለት፣ሥጋዊ ደማዊ ፍላጎቱና ስሜቱን ሳይገራ፣ በገዳም በደጅ ጽናት፣ የአባቶችን ትሕትናና መንፈሳዊነት፣ ሳይመለከት፣ የመናንያንን ተጋድሎ፣ ገድለ መነኮሳትን ሳያጠና፣ እንደመጣ የሚመነኩስና ግብረ መነኮሳትን ያልተማረ፣ ለሹመት ለፍትፍት የተሾመ በጣም ብዙ ስለሆነ በዓለም ከሚኖሩ ከዓለማውያን ሰዎች ባልተናነሰ ሁኔታ ቁጡ ኃይለኛ አልፎም ጨቅጫቃና ቂመኛ ሆነው የሚታዩ ብዙዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ነገሮች በጣም ለመነኩሴ ቀርቶ ለማንኛውም ሰው ክፉ ፈተናዎች ልብን የሚያጨልሙ፣ከክርስቶስ ኅብረት የሚለዩ ናቸው፡፡ ሕንጻ መነኮሳት በአራት ነገሮች ልብ ይጨልማል ይላል፡፡ ‹‹ባልንጀራውን በመጥላት፣ ሰዎችን በማቃለል፣ በምቀኝነትና በቅናት፣ ሰዎችን በማክፋፋት ተገቢ ያልሆነ ቃል በመናገር›› ይላል፡፡ (ምዕ. ፳፣ቁጥ.፫) በማር ይስሐቅ መጽሐፍ መነኩሴ ‹‹ይስደቡት እንጅ አይሳደብ፤ ይምቱት እንጅ አይማታ፤ ይሙት እንጅ ማንንም አይማ›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ ነገር ግን ሐሜትም፣ ስድብም፣ ነቀፋም፣ ክርክርም ዘለፋም፣ ጥላቻውና ቁጣውም ደረጃውን ከፍ አድርጓል፡፡ ብዙዎቹን ተገዳድሯል፤ አንዳዶቹን አሸንፏል፡፡ በትልልቆቹ በሲኖዶስ አባላት ሳይቀር ፈተናው ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል፡፡

ቁጣ መጥፎ ነው፤ ወደ ጥላቻ ወደ ቂም ያድጋል፤ ብዙዎች ቁጡ ሆነዋል፤ ቁጣቸውም አድጎ ወደ ቂምና ጥላቻ ተሸጋግሮ፤ ከልባቸው ተርፎ በአንደበታቸው ተለፍፎ፣ አየሩንም ሲሞላው ብዙዎችንም ሲበክል ይታያል፡፡ ለቁጣቸው፣ ለጥላቻቻው ምክንያት የሚያደርጉት ብዙ በሰም የተቀባ አጀንዳ ያላቸው አባቶች ይታያሉ፡፡

አንዳንዶቹ የብሔር፣ አንዳዶቹ የቋንቋ፣ አንዳንዶች የሥራና የሹመት እኩልነት፣ አንዳንዶች ሌላ ምክንያት አድርገው ይነታረካሉ፤ ጥላቻ ይሰብካሉ፤ እኛና እነርሱ የሚል ከቤተ ክርስቲያን ያልተማሩትን የክርስትና መሠረት የሌለው፣ ለመነኮሳት ቀርቶ በክርስትና ማዕቀፍ ላለ ሀብተ ወልድ ስመ ክርስትና ላለው ለማንኛውም ሰው እንኳን የማይፈቀደውን ግን ደግሞ በጎ ነገር የሚመስል ኮርኳሪና ቀስቃሽ አጀንዳ ይዘው ይነሣሉ፤ በዚህ ስም መርዙን ይተፉታል፡፡‹‹ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው›› እንዳለ ጠቢቡ ፍጻሜው ሞት የሆነ የልዩነት፣ የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የቂም፣ የትምክህት አጀንዳ በሰም ቀብተው አምጥተው ለምእመናን ሞት ስደት፣ መከራ፣ ለቤተ ክርስቲያን ውድመት ለአንዲቱ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን መከራ ያመጡ፣ የምእመናንን አንገት ያስደፉ፣ ለጠላት ጥቃት በር የከፈቱ በጣም ብዙ መነኮሳትን ማየት ችለናል፡፡ (ምሳ.፲፮፥፳፭)

መልከ ብዙ የሥጋ ጾር ያልጠፋላቸው ሳይገባቸው የገቡ፣ ሳይበቁ የመነኮሱ፣ የምንኩስና ክብሩን ልዕልናውን ለክፉ መሻታቸው የለወጡ፣ ብኩርናቸውን በምስር ወጥ የለወጡ ብዙዎች ክብረ ምንኩስናን ከመፈተን አልፈው ሲኖዶሳዊ ልዕልናችንን የሚፈትኑበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና አደጋ የሆኑበት ዘመን ላይ ነን፡፡

አባትነታቸውን የሚያምን ሁሉ ግራ የየተጋባበት ክፉ ዘመን ነው፡፡ ‹‹ቁጣ ሲመጣ ሲኦልን አስቦ ይታገሧል፤ በቁጡ ሰው መንፈስ ቅዱስ አያድርም›› ይላል መጽሐፈ ምዕዳን፡፡ (ገጽ ፻፶፬) ‹‹ቁጡ ሰው የሰይጣን ደቀ መዝሙር ነው እንዳለ አባ ጳኩሚስ ቁጣ ቂም በቀል፣ ጥላቻ፣ የጥላቻ ንግግር፣እብሪት፣ ወገንተኝነት ያልተገባ ንግግር እነዚህን የመሰሉትን ሁሉ ከመነኮሳት፣ ከመናንያን ሁሉን ትተው ከተከተሉት የማይጠበቅ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ እንደ መጽሐፈ መነኮሳት፣ እንደ ሕንጻ መነኮሳት ባሉት መጻሕፍት እንደተደነገገው መኖር ባይቻል እንኳን በመጠኑ ጫፍ ባልወጣና ለቤተ ክርስቲያን ውርደት ለምእመናን ኀፍረት ላለመሆን ለራሳቸው ክብር ያላቸው በወንድሞቻቸው ላይ በቁጣ በጥላቻ የማይነሳሱ ለዚህ ዓለም ሐሳብ የማይሸነፉ ለመሆን ተግተው የሚጸልዩ መነኮሳት ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱ አሳሳቢ ነው፡፡

ምክንያቱም ባልንጀራውን የሚያማ፣ በክፉ የሚከስሰው፣ በመነኮሳት ዘንድ ጠብን፣ ክርክርን የሚፈጥር ቢኖር ከኅብረቱ ይውጣ የሚል ሥርዓት አለና፡፡ (ፍት. መን.አን. ፲፥፬፻፪) በጥቅሉ ምንኩስና ፈተና ላይ ነው፡፡ የእነ እንጦንስና መቃርስ፣ የእነ ጳኩሚስ አስኬማ፣ ዘጠኙ ቅዱሳንን ያስመለከተን፣ ነገሥታትን ማርኮ ዘውድ አስጥሎ ሌጦ አስለብሶ፣ ገዳም ያስገባው፣ብዙዎች ምድራዊነታቸውን ረስተው በቅድስና በንጽሕና በዓለመ መላእክት ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን ጋር በደመና ተጭነው በክንፍ በርው እንዲያመሰግኑ በግብረ መላእክት እንዲተባበሩ ያደረገ ምንኩስና ተፈትኗል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ለአባ ጳኩሚስ በሰጠው ሕገ መነኮሳት/ሥርዓተ መነኮሳት ያለው ትንቢት እየተፈጸመብን ይመስላል፡፡
ተባይስ በምትባል አውራጃ ጠርቤንስስ በምትባል ሥፍራ በምናኔ ሳለ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ለአባ ጳኩሚስ ሕንጻ መነኮሳት የተባለውን ሕግ ሰጥቶታል፡፡ እናም በዚህ ጊዜ መልአኩ ለአባታችን በሰማይ የተጎሳቆሉ አምስት የመነኮሳት ኅብረትን አሳይቶት ነበር፡፡ እነዚህ አምስት የክፉዎች ማኅበር በሰማይ ተጎሳቁለው ያያቸውን መነኮሳት ሲዘረዝር ፩ኛ የጅቦች ማኅበር፣ ፪ኛ.የውሾች ማኅበር፣ ፫ኛ.የተኩላዎች ማኅበር፣ ፬ኛ.የቀበሮዎች ማኅበር፣ ፭ኛ.የፍየሎች ማኅበር ስብስቦችን ተመለክቷል ማለት በነዚህ የተመሰሉ መነኮሳትን ማለት ነው፡፡

አባታችን ሲናገር ‹‹ተርጉመህ አስረዳኝ አልኩት፤ እርሱም ልብህን ከፍተህ ስማኝ አለኝ፡፡ በጅቦች የተመስለው ያየሃቸው መነኮሳት በስማቸውና በአነጋገራቸው ከወንድሞች ጋር በጋራ የሚሠሩ ይመስላሉ፡ ነገር ግን ተግባራቸው እንደ ጅቦች ነው፡ ቀን ቀን ከቅዱሳን ወንድሞች ጋር ይጾማሉ፤በመሸ ጊዜ በምኝታ ሰዓት በጨለማ እንደ ጅብ ወጥተው ወደ ሴቶች መነኮሳት ሰፈር ይሄዳሉ፤ፈቃደ ሥጋቸውን ለመፈጸም፣ ከርሳቸውን ለመሙላት፣ በልተው ከጠገቡ በኋላ ራሷን መቆጣጠር የተሳናትን ሴት ነጥቀው ያረክሷታል፤ የምንኩስናቸው ክብርም ከላያቸው ይገፈፋል አለኝ›› ይላል፡፡ በዚህ አላበቃም ቀጥሎ የተዘረዘሩትንም እየተረጎመ ይነግረዋል፡፡

ሁለተኛዎቹ ማኅበረ መነኮሳት በውሾች የተመሰሉ ናቸው፡፡ ስለነሱም ሲተረጉም ‹‹ያየሃቸው የውሾች ስብስብ መነኮሳት ናቸው፡፡ በአንድነት እየኖሩ ለግላቸው ገንዘብ የሚሰበስቡ ናቸው፤ ሲኖሩ እንደ ውሾች ናቸው፤ ውሾች ያገኙትን ነገር ሁሉ ኩስም ቢሆን አይጥሉም፤ ንቀው የሚተውት አንዳች ነገር የላቸውም እነዚህም መነኮሳት በዚህ ሥራቸው በውሾች ተመሰሉ አለኝ›› ይላል፡፡ይህን ትንቢት ስናነብ በማቴዎስ ወንጌል ጌታ በገዳመ ቆሮንቶስ የተፈተነባቸውን አርእስተ ኃጣውእ ሊቃውንት ሲተረጉሙ ‹‹መነኮሳትን የስስት ካህናትን የትዕቢት ጾር ይጸናባቸዋል›› የሚለውን ያስገነዝበናል፡፡ (ትርጓሜ ማቴ. ፬፥፲፩)

ሦስተኞቹን ስብስቦች ደግሞ በተኩላ መስሎ አሳይቶታል፡፡ ‹‹እነዚህ መነኮሳት ነገር ሲያድኑ እንደ ሰይፍ በነገር በተሳለው አንደበታቸው የወንድሞቻቸውን ሥጋ እንደ ተኩላዎች የሚቦጫጭቁ ናቸው፡፡ መሰሎቻቸውን በማስተባበር በአንደበታቸው የሰውን ሕይወት የሚያጠፉ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፡፡ ስለዚህም በተኩላዎች ተመሰሉ›› ሲል መልአኩ ነግሮታል፡፡ እንደተኩላ ያሉ አንደበታቸው ሰይፍ ሆኖ የሚቆራርጥ፣ እሳት ሆኖ የሚያቃጥል፣ መርዝ ሆኖ አንጀት የሚበጣጥስ ለመሰሎቻቸው ለወንድሞቻቸው ተኩላ የሆኑ ነጣቂዎች ብዙዎችን እየተመለከትን በመሆኑ የአባ ጳኩሚስ ራእይ በኛ ላይ ደረሰን? ያስብላል፡

አራተኞቹ የመነኮሳት ስብስቦች ደግሞ በቆናጽል /በቀበሮዎች ተመስለው የታዩት ናቸው፡፡ እነዚህ መነኮሳት ሲታዩ ማኅበራውያን የሚመስሉ በውስጣቸው ግን ብቻቸውን ተደብቀው የሚበሉ መነኮሳት ናቸው፡፡ ለቀበሮዎች ያገኙትን ሁሉ ብቻቸውን የመብላት ልምድ አላቸው፡፡ በአንድነት አይበሉም፤ ሲበዛ ስግብግቦች ናቸው፡፡ እነዚህንም መነኮሳት በቀበሮ የመሰላቸው ስግብግቦች ራስ ወዳዶች ሁሉን ለኔ ብቻ የሚሉ ለማኅበሩ ለወንድሞቻቸው የማያስቡ ስለሆኑ ነው፡፡‹‹እያንዳዳቸው ከሚወዱት ሰይጣን ጋር በመሆን ይመገባሉ›› በማለት የጉዳዩን ክፋት ይገልጽና በዚህ ምክንያት በቀበሮዎች መመሰላቸውን ይገልጽለታል፡፡

የመጨረሻዎቹን አምስተኞቹን የመነኮሳት ስብስቦች በፍየል ነው መስሎ ያሳየው፡፡ በፍየሎች ማኅበር የተመሰሉት መነኮሳት ባልንጀሮቻቸው መነኮሳት ሲበድሉ የተመለከቱትን የሚከተሉ ማለትም የሌሎችን ኃጢአት የሚደግሙ ናቸው፡፡ ፍየል ነጣቂ ነምር አንዱን ሲበላው በመሸሽ ፋንታ ሌሎችም ወደ ነጣቂው ነምር ይሄዳሉ፤ እያንዳዳቸውንም ሰብሮ ይጨርሳቸዋል፡፡ እነዚህ መነኮሳትም ከጠላቶቻቸው ከሰይጣን ጦር የተነሣ ጓደኞቻቸው ሲወድቁ እያዩ አይጠነቀቁም፤ዝሙት የሚፈጽም መነኩሴ ሲያዩ እነርሱም ዝሙት ይፈጽማሉ፤ ሐሜተኛም ከሆነ በመጥፎ ተግባሩ ይሳተፋሉ፤ ጾምን የሚደፍር መነኩሴ ሲያዩ እነርሱም ጾምን ይደፍራሉ፤ እርሱ የሆነውን ሁሉ ይሆናሉ እንጅ ከዚያ ግብር አይታቀቡም፤ አይሸሹም፡፡ በዚህ የተነሣ በፍየሎች መስሎ ቅዱስ መልአክ ለቅዱሱ አባት አባ ጳኩሚስ አሳይቶታል፡፡ (ሕንፃ መነኮሳት ክፍል ሦስት ቁጥር ፲)

መቼም እናቶቻችን የትንቢት መፈጸሚያ አታድርገን የሚሉት ቀላል ጸሎት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን አባታችን የተመለከተው ራእይ ወይም በኋለኛው ዘመን የሚመጡ መነኮሳትን የሚገጥማቸውን ፈተና ለአባ ጳኩሚስ የነገረውን ሁሉ ስንመለከት በዘመናችን ያሉ መነኮሳት ከዚህም ከዚያም ሲፈተኑበት ብዙዎችም ፈተናውን ሲወድቁ፣ በመነኮሳት የሚታመኑ ምእመናንም ቅስማቸው ሲሰበር፣ ቤተ ክርስቲያንም ‹‹በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል›› እንደተባለ በአንዳዶች ምክንያት ክብሯ ገናንነቷ ችግር ላይ ሲወድቅ እየተመለከትን ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን ለእውነተኞቹ መናንያን መነኮሳት አባቶች ብሎም ለምነና ለምንኩስና ትውልዱ የነበረውን አመለካከትና ክብር የሚፈትን መሆኑ ነው፡፡

ነገን ዛሬ ለመሥራት፣ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የተሻለች ለማድረግ፣ ወደ ቀደመ ክብሯና መታፈሯ እንዲሁም መከበሯ ለመመለስ ይቻል ዘንድ ክብረ ምንኩስናን ማጠናከር፣ ገዳማዊ ሥርዓትን መጠበቅ፣ አሁን የሚታዩ ተግዳሮቶችን ማስወገድ የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው፡፡ ስለሆነም ክብረ ምንኩስና ነገ ምን መሆን አለበት? እንዴትስ የተሻለ እናድርገው? የሚለውን በሚቀጥለው በክፍል ዘጠኝ ይዘን እስክንቀርብ ቸርነቱ አይለየን፤ አሜን!!!