‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››

ክፍል አምስት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

ሚያዚያ ፲፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ክብረ ክህነት ነገ

ተወዳጆች እንደምን ሰነበታችሁ? በዚህ ርእስ ባለፉት ተከታታይ አራት ክፍሎች ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ክብረ ክህነት ጽሑፎችን አቅርበንላችኋል፡፡ በዚህም “ክብረ ክህነት ትናንት እንዴት ነበር? ዛሬስ ምን ሁኔታ ላይ ነው?” የሚሉ ጉዳዮችን አንስተን ለመዳሰስና የክብረ ክህነትን ተግዳሮቶች በጥቂቱ ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ በክፍል አምስት ደግሞ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የተሻለች ለማድረግ “ክብረ ክህነት ነገ ምን መሆን አለበት” የሚለውን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ምንም እንኳን የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ቢኖራቸውም ዲያቆንም፣ ቄስም ኤጲስ ቆጶስም በክህነት ያሉ ባለክህነት ስለሆኑና በወል ስማቸው የሚገናኙ በትርጉም አገልጋይ የሚባሉ ናቸውና ካህናት እያልን ስንነጋገር ቄሱን ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ካህናት ሁሉ በጥንቃቄ ተመርጠው እንዲሾሙ የተባለበት ምክንያት ሥራቸውና ኃላፊነታቸው ከፍተኛ በመሆኑና የክርስቶስም አደራና ትእዛዝ ያለበት ስለሆነ ነው፡፡

የየራሳቸው የአገልግሎት መደብ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉም ግን ለሦስት መሠረታዊ ዓላማ የተሾሙ ናቸውና እነዚህን ሦስት ዓላማዎች የተረዱና ተገዥ የሚሆኑ ካህናትን ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

፩ኛ. ማስተማር የሚችሉ፡- ማስተማር  የካህናት ዐቢይ ግብር መሆኑንን ጌታችን ሐዋርያትን ሲያዛቸው ‹‹ሒዱና አስተምሩ›› ማለቱ ትምህርተ ወንጌል ለሰው ልጆች ከሁሉ በፊት የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር መሆኑን ያስረዳናል፡፡ (ማቴ.፳፰፥፲፱-፳) ስለዚህ የካህን የመጀመሪያ ተግባሩ ጸሎትና ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር መትጋት ነው፡፡ ካህናት ብሉያትን ሐዲሳትን፣ ሊቃውንትን መነኮሳትን አምልተው አስፍተው እንዲያስተምሩ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ባይሆን እንኳን ቢያንስ አራቱን ወንጌሎች የማያውቁ ከሆነ አይሾሙ ተብሎ ሕግ ተሠርቷል፡፡ ‹‹ወኢይኩን አሐዱሃ ቀሲስ ዘኢየአምር ነገረ መጻሕፍት አምላካውያት ሠናያት፤ መልካም የሆኑትን የአምላክን መጻሕፍት ያላወቀ አንዱ እንኳ ቄስ አይሁን›› እንዲል ፍትሐ ነገሥት፡፡ (ፍት.መን አን.፮)

ሁሉን ባይባልም አብዛኞቹን ካህናት አይተን አሁን ባለው ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ነገ በተሟላ ሁኔታ ማሻገር ከባድ ነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አብዛኛው አማኝ በገጠር የሚኖር የነበረ መሆኑ፣ የተማረውና ጠያቂው አካል ብዙ ባለመሆኑ፣ የሌሎች እምነት ግፊትና ተጽእኖ ብዙም ባለመሆኑ፣ የባህልም፣ የእምነትም ወረራውና ጫናው ስላልነበረ ወዘተ የውስጥ አገልግሎቱን ታድሞ ተአምረ ማርያም ሰምቶ ወደ ቤቱ የሚሄድና ከአባቶቹ ያገኘውን እምነት ያለበቂ ዕውቀትም ቢሆን አጽንቶ ጠብቆ የሚኖር ምእመን ስለ ነበረ የካህናት አለማስተማር ችግር ጎልቶ አልታየም ነበር፡፡

አሁን ግን የከተማ ኑሮ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ትምህርት ቀመስ የሆነው ማኅበረሰብ እየባዛ መሄዱ፣ ሉላዊነት ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ በመምጣቱ፣ ጠያቂና ተመራማሪ ብሎም በሌሎች እምነት አስተምህሮዎች ተጽእኖ የሚደረግበት ትውልድ እየበዛ በመምጣቱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከውስጥ ወደ አፍኣ እያጋደለ እንዲሄድ አስገድዷል፡፡ ይሁን እንጅ ካህናት ያለፉበት የትምህርት ሥርዓታችን ደግሞ በተቃራኒው በመሆኑ ሁለገብ እውቀት ያላቸው ተጠያቂ የሆኑ ራሳቸውንም ምእመናንንም ከክህደት ከምንፍቅና ሊጠብቁ የሚችሉ፣ በአፍም በመጽሐፍም ተከራክረው መልስ የሚሰጡ ለዐውደ ምሕረቱ ብቁ የሆኑ ካህናት በበቂ ሁኔታ አሉን ማለት አይቻልም፡፡

‹‹ካህኑ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ ዕውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል›› እንዳለ ነቢዩ ሚልክያስ  ለማስተማር የሚበቁ ከላይ በማቴዎስ ወንጌል የተሰጠውን ትእዛዘ ሐዋርያት መፈጸም የሚችሉ ሁለገብ ዕውቀት ያላቸው፣ የትውልዱን ተግዳሮት የሚረዱ፣ ዘመኑን የዋጁ አስተማሪ፣ መካሪ የክህነት ሰዎችን ማፍራት ስንችል አንደኛውን የክህነት ዓላማ ማሳካት እንችላለን፡፡ (ሚል.፪፥፯)

፪ኛ.ምሥጢራትን መፈጸም፡- ከማስተማር ቀጥሎ ትልቁ የካህናት ተልእኮ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ፍቅሩን የገለጸባቸውን፣ ያለንፍገት ጸጋውን የሚሰጥባቸውን ምሥጢራት መፈጸም ከካህናት በቀር ለማንም አልተሰጠም፡፡ እነዚህን ልዩ ልዩ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጅ የሚሰጡ መንፈሳዊ አገልግሎች እንዲፈጽሙ የተጠሩ ብሎም የተመረጡ ካህናት ዛሬ ላይ ይህን አገልግሎት እንደሸክም ያዩታል፤ በቅዳሴው በሰዓታቱ አገልግሎት መመደብ እንደ ምርጫ ማጣት ይመለከቱታል፤ ቢችሉ ሁሉም የቢሮ ሥራ ቢመደቡ ይመርጣሉ፤ የሚያገለግሉትም ሰማያዊ ዋጋውን አስበው፣ በምእመናን እና በራሳቸው ሕይወት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን መንፈሳዊ ለውጥና በረከት ተገንዝበው ሳይሆን ሥራ ስለሆነ ብቻ የሚከውኑት ብዙዎች ናቸው፡፡

ካህናት ይህን የተዛነፈ የአስተሳሰብ ችግር መቅረፍ፣ ተልኳቸው ቅዳሴ ውዳሴ መሆኑን በእኒህ ግሩማን ረቂቃን ምሥጢራት አማካኝነት የእግዚአብሔር በረከት ለሰው ልጆች የሚሰጥ መሆኑን የተረዱ፣ የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ሥራ አለመሆኑን የሚረዱ፣ ይልቁንም ከሰማያውያን መላእክት ከካህናተ ሰማይ ጋር የሚያስተባበር መሆኑን የሚገነዘቡ ካህናት ሲኖሩን ሁለተኛውን የክህነት ዓላማ እናሳካለን፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፫)

ቅዱስ ያሬድ በካህናተ ሰማይ ድጓ ላይ ካህን ንቃተ ሕሊና ኖሮት ሲያገለግል ለዓለም፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ብርሃን እንደሚሆን አብራርቶ ይገልጻል፤ እንዲህ ሲል፡‹‹ሶበ ይነቅህ ካህን ተከሥተ ብርሃን ለኵሉ ዓለም ወተቀደሰት ቤተ ክርስቲያን በትፍሥሕት ወሐሤት ለጻድቃን፤ ካህን በነቃ ጊዜ ንጹሕ አገልግሎት በሰጠ ጊዜ ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን ተገለጠ፤ ቤተ ክርስቲያንም ከበረች፤ ተድላ ደስታም ለጻድቃን ሆነ›› በማለት የአገልግሎታቸውን ውጤት ተናግሯል፡፡

፫ኛ.ጥበቃ/ጠባቂነት ፡- ሌላኛውና ዋነኛው የካህናት ተልእኮ ጠባቂነት ነው፡፡

  • ጳጳሳቱ ጠባቂዎች ናቸው ፡፡ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚያብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው እና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› እንዲል፤ (የሐዋ. ሥራ ፳፥፳፰)
  • ካህናቱ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ‹‹ግልገሎቼን አሠማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ›› የሚለው አምላካዊ አደራ ለጳጳሳት ብቻ አለመሆኑን ይልቁንም እያንዳዱ ካህን በየአጥቢያው የሚገኙትን ምእመናን ከነጣቂ ተኩላዎች ከመናፍቃንና ከከሓዲዎች እንዲሁም ዲያብሎስ ካጠመደው የኃጢአት ወጥመድ ሁሉ እንዲድኑ በየጊዜው ሳይሰለች ማስተማር፣ መምከር፣ መገሠፅና መጠበቅ ግብሩ መሆኑን እንረዳለን፡፡ (ዮሐ.፳፩፥፲፭)
  • ዲያቆናቱም ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን እንዲጠብቁ፣ እንዲያስተባብሩ፣ እንዲያሰማሩ፣ እንዲመግቡ እስጢፋኖስን ጨምሮ ሰባቱ ዲያቆናት ለሕዝቡ መሾማቸውን ልብ ይሏል፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፮፥፫)

በጥቅሉ የካህናት ሦስተኛው ዐቢይ ግብራቸው መንጋውን መጠበቅ፣ ማሰማራት፣ በለመለመ መስክ በንጹሕ ምንጭ ውኃ መመገብ እንጅ ክህነትን መገልገያ፣ የሥጋዊ ደማዊ ፍላጎት መሙያ፣ የዝናና ክብር ማስፈጸሚያ፣ የሥልጣንና ገንዘብ መንጠላጠያ እንዳልሆነ የሚረዱ፣ ባለ ራእይና ሩቅ አሳቢ ካህናትን መሥራት ስንችል ነጋችንን ማስተካከል ቤተ ክርስቲያንን ባለቤቱ መጥቶ ወደ ዘለዓለም መንግሥቱ እስኪወስዳት እስከ ምጽአት እንድትቀጥል ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ይህን ዓለም ሲፈጥረው በተለይ የሰውን ልጅ መለኮታዊ ጥበቃ፣ መልአካዊ ጥበቃ፣ ሰዋዊ ጥበቃ እንዳይለየው አድርጎታል፡፡ ሰዋዊውን የጥበቃ ኃለፊነት ለካህናቱ ለነገሥታቱ ነውና የሰጣቸው፡፡

ማጠቃለያ፡- የክህነት ተልእኮ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህን ተልእኮዎች ለመወጣት የክህነት ሰዎች የአገልጋይነት ሥነ ልቡናን የተላበሱ፣ ፍጹም እምነት፣ መንፈሳዊነት ያላቸው፣ ራሳቸውን የካዱ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ በዕውቀት የማበስሉ፣ ራእይና ጉጉት ያላቸው፣ አገልግሎታቸው በቦታና በሁኔታ የማይወሰን፣ ግብረ ገብነት ያላቸው፣ ስለ መዳራትም ወይም ስላለመታዘዝ የማይከሰሱ፣ የማይነቀፍ ማንነት ያላቸው፣ የማይኮሩና የማይቆጡ፣ የማይሰክሩና የማይጨቃጨቁ፣ ነውረኛና ረብ የማይወዱ፣ እንግዳ ተቀባይ የሆኑ፣ በጎ የሆነውን ነገር ሁሉ የሚወዱ፣ ጠንቃቃ፣ ጻድቅ፣ ቅዱስ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርትን ሊመክሩ ተቃዋሚዎቹን ሊወቅሱ የሚችሉ የተማሩ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል፡፡ (ቲቶ.፩፥፬-፱)

‹‹ሤመክሙ እግዚአብሔር ጳጳሳተ፣ ቀሳውስተ፣ ወዲያቆናተ ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ እንተ አጥረያ በደሙ ወአተባ በዕፀ መስቀሉ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን በዕፀ መስቀሉ የባረካትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት አድርጎ ሾማችሁ›› እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ (ጾመ ድጓ)

የነገዋ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቀድሞው ዘመን የቅድስና፣ የንጽሕና፣ የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የማስተዋል ምንጭ የሆኑ፣ ለመንጋው የሚሳሱ፣ የምእመናን መጥፋት፣ የቤተ ክርስቲያን ጉዳት የሚገዳቸው፣ ምንደኛ ያልሆኑ እውነተኛ እረኞች፣ ጠባቂዎች፣ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የሆኑ እንደ ሙሴ አብነት የሚሆኑ፤ ‹‹ይህ ዝብ ከሚጠፋ እኔ ከሕይወት መዝገብ ልፋቅ›› እንዳለው ከምንም በላይ ለሕዝቡ የሚራሩ የክህነት ሰዎችን ማፍራት ለነገ የማይባል ትልቁ የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡ (ዘፀ.፴፪፥፴፪)

ለዚህም ከታች ከመሠረቱ ስንጀምር፣ የአመለካከት ለውጥ ስናመጣ፣ ሥልጠናዎች ላይ ስናተኩር፣ የምእመናንን ንቁ ተሳትፎ ስናገኝ፣ የአብነት ትምህርታችንን ሁለገብና ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ስንሠራ፣ ክህነትን ለሥጋዊ ደማዊ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ የሚያደርጉና መጥፎ አርአያ የሚሆኑ አገልጋዮችን መገሠፅ ብሎም ቦታ እንዳያገኙ ማድረግ የሚያስችል የሕግ እርምጃ ሲኖር፣ ዘመኑን የሚዋጁ፣ ለትውልዱ ቤዛ የሚሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሻግሩ እውነተኛ አገልጋዮችን እውነተኛ ጠባቂዎችን እናፈራለን፤ ነገም የተሻለ ይሆናል፡፡

ይቆየን!