‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ››

ክፍል አራት

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሚያዚያ ፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ክብረ ክህነት ዛሬ

ክህነት የቤተ ክርስቲያን መመሥረቻና የመንግሥተ እግዚአብሔር መግቢያ ቁልፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ዐለት በተባለ ቅዱስ ጴጥሮስ ክህነት ላይ ነው፡፡ (ማቴ.፲፮፥፲፰) አንድ ቤት በአሸዋ እና በድቡሽት ላይ ቢሠራ ነፋስ ይገለብጠዋል፤ ጎርፍ ይጠራርገዋልና በማይናወጥ ጽኑ ዐለት ላይ ማነጽ የብልህ እና አዋቂ ግንበኛ ግብሩ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ባለቤት ቤቱን በጴጥሮስ ዐለት ላይ መሥርቷት ዘመናትን ተሻግራ ለትውልድ ክብር ሆና ዘልቃለች፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጌጥ የውጭ ፈርጥ፣ የታች መሠረት የላይ ጉልላት ክህነት መሆኑን መረዳት አይከብድም፡፡ “ኢኀደጋ ለምድር እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፣ እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም፤ ቸሩ አምላካችን እግዚብአሔር ለዘለዓለም እስከ ለዓለም ምድርን ያለ ካህናትና ዲያቆናት አልተዋትም’’ እንዲል፤ (የኅዳር ጽዮን ዋዜማ) ቤተ ክርስቲያናችንን ያለ ክህነትና ካህናት ፈጽሞ ያልተዋት ቢሆንም አሁን ግን ክብረ ክህነት በዘመናችን በርካታ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበታል፡፡

ሀ. ያልተካኑ ሰዎች በክህነት ቦታ መሰየማቸው፡-

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንዶቹ ሳይጠሩ ተጠርተናል፣ ሳይመረጡ ተመርጠናል፣ ሳይካኑ ተክህነናል በማለት እንደ ደቂቀ ቆሬ፣ እንደ ደቂቀ ኤልያብ እንዲሁም የፋሌት ልጅ በድፍረት የተነሡ፣ መቅደሱን የሚያረክሱ፣ ከዕውቀትም ከሃይማኖትም ያነሱ ደፋሮች ቤተ ክርስቲያንን እግር ከወርች አስረው የያዙበት ዘመን በመሆኑ ክብረ ክህነት ችግር ላይ ወድቋል፡፡ (ዘኍ.፲፮፥፩-እስከ ፍጻሜ) በኦሪት ዘፍጥረት አንድ ታሪክ አለ፡፡ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ባሕር ከፍሎ ጠላት አስጥሞ በኵረ ግብጽን አጥፍቶ በኵረ እስራኤልን ሁሉ ለራሱ በኩር ማድረጉ የተመዘገበ ታሪክ ነው፡፡(ዘፀ. ፲፪፥፩-፲፪)

ይሁን እንጅ እስራኤል ሁሉ ለእግዚአብሔር በኵር ሆነው ሊዘልቁ ባለመቻላቸው፣ ለደብተራ ኦሪት ለክህነት አገልግሎት ተመራጭ ባለመሆናቸው እግዚአብሔር ከነገደ ሌዊ አሮንና ልጆቹን ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት በመለየቱና በመምረጡ ደቂቀ ቆሬና ሌሎቹ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ መግባት የክህነትን ሥራም መሥራት ፈልገው በሙሴ ላይ ማመጻቸውን፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገብተው ማጠን መፈለጋቸውና ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው ያለጸጋቸው በፈጸሙት ተግባር ደቂቀ ቆሬ ተቀሥፈዋል፤ ዳታንና አቤሮንን መሬት አፏን ከፍታ ውጣቸዋለች እሳትም ከሰማይ ወርዳ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች በልታቸዋለች፡፡ (ዘፍ.፲፮፥፩-፴፭) የዘመናችንን ደቂቀ ቆሬዎች፣ ዳታንና አቤሮንን ግን እግዚአብሔር ምድር ከፍቶ እንዳያሰምጣቸው እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳያቃጥላቸው ታግሧቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዓመቱም ዓመተ ምሕረት ዘመኑም ዘመነ ምሕረት ዘመነ ንስሓ ነውና፡፡ በዚህ ምክንያት ድፍረት ተሞልተው፣ ቤተ ጸሎት የተባለችውን የክርስቶስ ቤት ቤተ ምስያጥ ወፈያት ያደረጉ ደቂቀ ቆሬዎች ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ለክብረ ክህነት ዝቅ ማለት ምክንያት ናቸው፡፡

ለ.ሳይማሩ የተሾሙ ካህናት መኖር፡-

ክህነት ባለፉት ክፍሎች እንዳየነው ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ማዕረገ ሹመት ነው፡፡ ምዕራፍ ቁጥር ጠቅሶ ምሥጢር አደላድሎ፣ የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ፣ የጎደለውን ሞልቶ፣ በምሳሌ አዋዝቶ ማስተማርን፣ አስተምሮ ማሳመንን፣ አሳምኖ ማጥመቅን፣ አጥምቆ ማቁረብን፣ ናዝዞ መፍታትን፣ በአፍኣም በጽሑፍም መናፍቃንን ተከራክሮ መርታትን ምእመናንን መጠበቅን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡

አንድ ካህን በውስጥ በአፍኣ ለሚያገለግለው አገልግሎት ጥበብ መንፈሳዊ ጥበብ ሥጋዊ ዕውቀትም ያለው መሆን አለበት፡፡ አሁን አሁን ዕውቀት አልባ የክህነት ሰዎች ትልቅ የዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት ሆነዋል፡፡ ‹‹ሕዝቤ ከዕውቀት ማጣት የተነሣ ጠፍቷል›› እንዳለ ነቢዩ ሆሴዕ ከዕውቀት ማጣት የተነሳ ለጠፋው በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ላለው፣ በምንደኞችና በሐሰተኛ ነቢያት ለተወሰደው ምእመን ሃይማኖታዊ የዕውቀት ብርሃንን ሊያበራ የሚገባው ካህን እየጠፋ በመምጣቱና የዕውቀት ጾመኞች በመብዛታቸው ክብረ ክህነት ተፈትኗል የሚል አረዳድ አለን፡፡ (ሆሴ.፬፥፮)

ካህን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካል ሆኖ የሚያስታርቅ፣ ለማስተማር የተሾመ ነውና ሕዝቡን የሃይማኖትን ትምህርት ገልጦ በማስተማር በሕገ እግዚአብሔር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ ማጽናት የሚችል የተማረ የተመራመረ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ‹‹ካህኑ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መልክተኛ ነውና ከንፈሮቹ ዕውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባዋል ፡፡ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል›› ተብሏልና፡፡ (ሚል.፪፥፯) በፍትሐ ነገሥትም ካህን ወንጌልን በማስተማር ምእመናንን የሚረዳ፣ እውነተኛ ትምህርት በማስተማር ሰውን ማጽናናት የሚቻለው፣ ክደው ሊያስክዱት የሚተናኮሉትን የሚከራከራቸው መሆን አለበት የሚል ሥርዓት ተሠርቷል፡፡ (ፍት. መን. አንቀጽ ስድስት ክፍል አንድ)

ምንም እንኳን መጻሕፍት ይህን ቢሉም በተጨባጭ አሁን ያለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተሾሙና እየተሾሙ ያሉ አንዳንድ የክህነት ሰዎች (ከዲያቆን እስከ ኤጲስ ቆጶስ) ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ለመወጣት የሚያስችል መንፈሳዊና ሥጋዊ ዕውቀት የጎደላቸው መሆን ግልጽ ተግዳሮት ከመሆኑም በላይ ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር እንዲሉ ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ለክብረ ክህነት የማይመጥን ተግባር ያለ ዕውቀት እየፈጸሙ ለክብረ ክህነት መቀነስ ወይም መጓደል ምክንያት ሲሆኑ ይታያል፡፡

ሐ. የሥነ ምግባር ጉድለት መኖር፡-

ቤተ ክርስቲያን አቻ የማይገኝላት ትልቋ የሥነ ምግባር ትምህርት ቤት ናት፡፡ የተጣመመ የሚቃናባት፣ የታመመ የሚፈወስባት፣ ቀማኛው መጽዋች፣ ንፉጉ ለጋስ፣ ርኩሱ ቅዱስ፣ ዘማዊው ድንግል ኃጥኡ ጻድቅ የሚሆንባት የሥርዓት፣ የምግባር ማዕከል ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ምግባር ትምህርት ቤት ስትባል መምህራኖቿ ደግሞ ባለክህነቶቹ ዲያቆናቱ፣ ካህናቱና ጳጳሳቱ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የሰብእና መገንቢያ፣ የምግባር የትሩፋት ማዕከል፣ የሞራል ከፍታ ማሳያ፣ የሕግና ሥርዓት ምንጭ የነበረች ቤተ ክርስቲያን አሁን ስለምን የሥርዓት አልበኞች፣ የጨካኞችና የመዝባሪዎች መነኻሪያ ተደርጋ እስክትታይ ወረደች? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡

አሁንም መልሱ ከክብረ ክህነት መጓደል ያደርሰናል፡፡ ድፍረት፣ ትዕቢት፣ ፍቅረ ዝሙት፣ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሥልጣን፣ ዘረኝነት፣ ጎሰኝነት ፖለቲካ የተሸከሙ፣ ለእግዚአብሔርም ለክፉ ሥጋዊ ፍላጎታቸውም ባሪያ ለመሆን የሚሞክሩ፣ በጥቅሉ የመንፈስ ፍሬዎች የማይታይባቸው ክፉ ሠራተኞች በክህነትና በካህናት ስም መዋቅሯ ውስጥ ስለተሰገሰጉ ነው፡፡ (ገላ.፭፥፳፪) ንጹሓን የሚሸማቀቁባት፣ ፍትህ ርትዕ የጠፋባት፣ መገፋፋትና መነቃቀር መገለጫዋ እስኪመስል፣ በፖለቲካ የሤራ አስተሳሰብ የሚመሩ ብዙ ሥርዓት አልበኞች መዋቅሯን ተብትበው በመያዛቸው ነው ብለን እናምናለን፡፡

በዚህ ምክንያት ክብረ ክህነት እየተናቀ፣ አላፊ አግዳሚው ባልሰላ ምላሱ፣ ባልተሞረደ ጥርሱ የሚያላምጣት ቤተ ክርስቲያን፣ የጸኑት ልጆቿ አንገት የሚደፉበት፣ ያልጸኑት ተስፋ ቆርጠው ወደ ሌላ እምነት ቤት የሚሄዱበት፣ ቤተ ክርስቲያን በዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንድትወድቅ ያደረገ የሥነ ምግባር ችግር አለ፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ‹‹ያለ ሥርዓት የሚሔዱትን ገሥጿቸው›› ቢልም ታላላቆቹ፣ አዋቂዎቹ በአርአያ ክህነት በግርማ ሽበት፣ በምግባር በትሩፋት የሚታወቁት ዝምታን በመምረጣቸው ቤተ ክርስቲያን በፈተና እንድትሞላ ክብረ ክህነት እንዲቃለል፣ ሥርዓት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል ብለን እናምናለን፡፡

በጥቅሉ ክህነት በዘመናችን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ያለ፣ ልዩ ትኩረትን የሚሻ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ያልተማሩ ከድንቁርናቸው፣ ሥርዓት አልበኞቹም ከክፉ መንገዳቸው እንዲላቀቁ፣ በቆሬ መንገድ የቆሙ ከመንገዳቸው እንዲመለሱ የሚያደርግም ኃይል ነው፡፡ ሆኖም ግን ለቤተ ክርስቲያን ክህነት ጸጋቸው፣ አገልግሎት መለያቸው፣ ሥርዓት መገለጫቸው ሆነው በአርአያ ክህነት የሚመላለሱ፣ በክብረ ክህነት የሚገለጹ የክህነት ሰዎችን ለማፍራት የሠራነው ሥራ የለም፡፡

በምድር ያለች ሰማያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን የምትከፈትበት ቁልፍ ክህነት እንዲከበር ምን እናድርግ? ክብረ ክህነት ነገ ምን መልክ ይኑረው? ክብረ ክህነት እንዲመለስ፣ የቤተ ክርስቲያን የስሟ መጠሪያ የመልኳ መታያ ሆኖ እስከ ምጽአት እንዲዘልቅ ከማን ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጉዳዮችን ‹‹ክብረ ክህነት ነገ›› በሚል ክፍል አምስትን እናቀርብላችኋለን፤ ቸር እንሰንብት!