ነቢዩ ሶምሶን

የካቲት፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የጾርዓ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፥ ልጅም አልወለደችም። የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፥ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ። እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።”

ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፥ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም።እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አሁን የወይን ጠጅ የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፥ ርኩስም ነገር አትብዪ አለኝ ብላ ተናገረች። ማኑሄም “ጌታ ሆይ፥ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ፥ እንደ ገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንድናደርግ ያስገንዝበን” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። እግዚአብሔርም የማኑሄን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና ለሴቲቱ በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም። ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች፤ ለባልዋም “እነሆ፥ በቀደም ዕለት ወደ እኔ የመጣው ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ” ብላ ነገረችው።

ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፤ ወደ ሰውዮውም መጥቶ “ከዚህች ሴት ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን?” አለው። እርሱም፦ “እኔ ነኝ” አለ። ማኑሄም “ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ሥርዓት ምንድን ነው? የምናደርግለትስ ምንድን ነው?” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን “ሴቲቱ ከነገርኋት ሁሉ ትጠንቀቅ፥ ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፤ የወይን ጠጅንም የሚያሰክርንም ነገር አትጠጣ፤ ርኩስም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ትጠብቅ” አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ “የፍየል ጠቦት እስክናዘጋጅልህ ድረስ፤ እባክህ ቆይ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን “አንተ የግድ ብትለኝ መብልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትወድድ ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ “ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ “ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?” አለው። ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር።

ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ። የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ላማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አወቀ። ማኑሄም ሚስቱን “እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን” አላት። ሚስቱም “እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላስታወቀን ነበር” አለችው። ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፥ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ፤ እግዚአብሔርም ባረከው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ሊያነቃቃው ጀመረ።

ሶምሶንም ወደ ተምና ወረደ፥ በተምናም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ። ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ “በተምና ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ” አላቸው፡፡ አባቱና እናቱም “ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለምን?” አሉት። ሶምሶንም አባቱን “ለዓይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ” አለው። እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን ላይ ምክንያት ይፈልግ ነበርና ነገሩ ከእርሱ ሆነ፤ አባቱና እናቱ ግን አላወቁም።

በዚያን ጊዜም ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ላይ ገዦች ነበሩ። ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፤ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም። ወርዶም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ደስ አሰኘችው። ከጥቂትም ቀን በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፤ ማርም ነበረበት። በእጁም ወስዶ መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ መጣ፤ ማሩንም ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው ሬሳ ውስጥ እንደ ወሰደ አልነገራቸውም። አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጎበዞችም እንዲህ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ በዓል አደረገ። ባዩትም ጊዜ ከእርሱ ጋር ይሆኑ ዘንድ ሌሎች ሠላሳ ሰዎች ሰጡት። ሶምሶንም “እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀናት ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፡፡ መፍታትም ባትችሉ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም “እንድንሰማው እንቆቅልሽህን ንገረ” አሉት። እርሱም “ከበላተኛው ውስጥ መብል ወጣ፤ ከብርቱም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ” አላቸው። ሦስት ቀንም እንቈቅልሹን መተርጎም አልቻሉም።

በአራተኛውም ቀን የሶምሶንን ሚስት “እንቈቅልሹን እንዲነግረን ባልሽን ሸንግዪው፥ አለዚያም እንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወደዚህ የጠራችሁን ልትገፉን ነውን?” አሉአት። የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰች “በእውነት ጠልተኸኛል፥ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች እንቈቅልሽ ሰጥተሃቸዋልና፡፡ ትርጓሜውንም አልነገርኸኝም” አለችው። እርሱም “እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ለአንቺ እነግርሻለሁን?” አላት። ሰባቱንም የበዓል ቀን በፊቱ አለቀሰች፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ትርጓሜውንም ለሕዝብዋ ልጆች ነገረች።

በሰባተኛውም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማይቱ ሰዎች “ከማር የሚጣፍጥ ምንድን ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው?” አሉት። እርሱም “በጥጃዬ ባላረሳችሁ የእንቈቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁ ነበር” አላቸው። የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ በኃይል ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፥ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፥ ልብሳቸውንም ወስዶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጠ። ቍጣውም ነደደ፥ ወደ አባቱም ቤት ወጣ። የሶምሶን ሚስት ግን ከተባበሩት ከሚዜዎቹ ለአንደኛው ሆነች።

ከዚህም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና ወደ ጫጉላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ አለ፤ አባትዋ ግን እንዳይገባ ከለከለው። አባትዋም “ፈጽመህ የጠላሃት መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋት፤ ታናሽ እኅትዋ ከእርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ፥ በእርስዋ ፋንታ አግባት” አለው። ሶምሶንም “ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ” አላቸው።

ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱንም ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፤ በሁለቱም ጅራቶች ማካከል አንድ ችቦ አደረገ። ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም የቆመውንም እህል ወይኑንም ወይራውንም አቃጠለ። ፍልስጥኤማውያንም “ይህን ያደረገው ማን ነው?” አሉ። እርሱም “ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የተምናዊው አማች ሶምሶን ነው” አሉ። ፍልስጥኤማያንም ወጥተው ሴቲቱንና አባትዋን በእሳት አቃጠሉ። ሶምሶንም “እናንተ እንዲሁ ብታደርጉ እኔ እበቀላችኋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ዐርፋለሁ” አላቸው። እርሱም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም በኤጣም ዓለት ባለው ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።

ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፤ በይሁዳም ሰፈሩ፤ በሌሒ ላይም ተበታትነው ተቀመጡ። የይሁዳም ሰዎች “በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድን ነው? አሉ። እርሱም “ሶምሶንን ልናስር፤ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል” አሉ። ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኤጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን “ገዦቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድን ነው?” አሉት። እርሱም “እንዳደረጉብኝ እንዲሁ አደረግሁባቸው” አላቸው። እነርሱም “አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል” አሉት። ሶምሶንም “እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው። እነርሱም “አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም” ብለው ተናገሩት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት።

ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፤ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ። አዲስም የአህያ መንጋጋ አገኘ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፤ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። ሶምሶንም “በአህያ መንጋጋ ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁ” አለ። መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም “ራማትሌሒ” ብሎ ጠራው። እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና። “አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፤ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም በሌሒ ያለውን አዘቅት ሰነጠቀ፤ ከእርሱም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፤ ነፍሱም ተመለሰች፤ ተጠናከረም። ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም “ዓይንሀቆሬ” ብሎ ጠራው፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ በሌሒ አለ። በፍልስጥኤማውያንም ዘመን በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈረደ።

ሶምሶንም ወደ ጋዛ ሄደ፤ በዚያም ጋለሞታ ሴት አይቶ ወደ እርስዋ ገባ፡፡ የጋዛ ሰዎችም ሶምሶን ወደ ከተማ ውስጥ እንደ ገባ ሰሙ፤ ከበቡትም፤ ሌሊቱንም ሁሉ በከተማይቱ በር ሸመቁበት። “ማለዳ እንገድለዋለን” ብለውም ሌሊቱን ሁሉ በዝምታ ተቀመጡ። ሶምሶንም እስከ እኩለ ሌሊት ተኛ፤ እኩለ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ተነሥቶ የከተማይቱን በር መዝጊያ ያዘ፤ ከሁለቱ መቃኖችና ከመወርወሪያውም ጋር ነቀለው፤ በትከሻውም ላይ አደረገ፤ በኬብሮንም ፊት ወዳለው ተራራ ራስ ላይ ተሸክሞት ወጣ፤ በዚያም ጣለው።

ከዚህም በኋላ በሶሬቅ ሸለቆ የነበረች ደሊላ የተባለች አንዲት ሴትን ወደደ። የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው “እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን” አሉአት። ደሊላም ሶምሶንን “ታላቅ ኃይልህ በምን እንደ ሆነ፥ እንድትዋረድስ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። ሶምሶንም “በሰባት ባልደረቀ በእርጥብ ጠፍር ቢያስሩኝ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ” አላት። የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ሰባት ያልደረቀ እርጥብ ጠፍር አመጡላት፤ በእርሱም አሰረችው። በጓዳዋም ውስጥ ሰዎች ተደብቀው ነበር። እርስዋም “ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። እርሱም የተልባ እግር ፈትል እሳት በሸተተው ጊዜ እንዲበጠስ ጠፍሩን በጣጠሰው፤ ኃይሉም በምን እንደ ሆነ አልታወቀም።

ደሊላም ሶምሶንን እነሆ አታለልኸኝ፤ የነገርኸኝም ሀሰት ነው፤ አሁንም የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ” አለችው። እርሱም “ሥራ ባልተሠራበት በአዲስ ገመድ ቢያስሩኝ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ” አላት። ደሊላም አዲስ ገመድ ወስዳ በእርሱ አሰረችው፤ በጓዳዋም የተደበቁ ሰዎች ተቀምጠው ነበር። እርስዋም “ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ገመዱንም ከክንዱ እንደ ፈትል በጣጠሰው። ደሊላም ሶምሶንን “እስከ አሁን ድረስ አታለልኸኝ፤ የነገርኸኝም ሐሰት ነው፤ የምትታሰርበት ምን እንደ ሆነ ንገረኝ” አለችው። እርሱም “የራሴን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድር ጋር ብትጐነጕኚው፥ በችካልም ብትቸክዪው፥ እደክማለሁ፤ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ” አላት። ሶምሶንም በተኛ ጊዜ ደሊላ የራሱን ጠጕር ሰባቱን ጕንጕን ከድሩ ጋር ጐነጐነችው፤ በችካልም ቸከለችውና ሶምሶን ሆይ “ፍልስጥኤማውያን መጡብህ አለችው። ከእንቅልፉም ነቃ፤ ችካሉንም ከነቆንዳላው ድሩንም ነቀለ። እርስዋም “አንተ እወድድሻለሁ እንዴት ትለኛለህ? ልብህ ከእኔ ጋር አይደለም? ስታታልለኝ ይህ ሦስተኛ ጊዜህ ነው፤ ታላቅ ኃይልህም በምን እንደ ሆነ አልነገርኸኝም” አለችው። ዕለት ዕለትም በቃልዋ ነዘነዘችው፤ አስቸገረችውም፤ ነፍሱም እስከ ሞት ድረስ ተጨነቀች። እርሱም “ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ ለእግዚአብሔር የተለየሁ ነኝና በራሴ ላይ ምላጭ አልደረሰም፤ የራሴንም ጠጕር ብላጭ ኃይሌ ከእኔ ይሄዳል፤ እደክማለሁም፤ እንደ ሌላም ሰው እሆናለሁ” ብሎ የልቡን ሁሉ ገለጠላት። ደሊላም የልቡን ሁሉ እንደ ገለጠላት ባየች ጊዜ የልቡን ሁሉ ገልጦልኛልና ይህን ጊዜ ደግሞ ኑ ብላ ላከችና የፍልስጥኤማውያንን መኳንንት ጠራች።

የፍልስጥኤማውያን መኳንንትም ብሩን በእጃቸው ይዘው ወደ እርስዋ መጡ። እርስዋም በጕልበትዋ ላይ አስተኛችው፤ አንድ ሰውም ጠራች፤ እርሱም ሰባቱን የራሱን ጕንጕን ላጨው። ልታዋርደውም ጀመረች፤ ኃይሉም ከእርሱ ሄደ። እርስዋም “ሶምሶን ሆይ፥ ፍልስጥኤማውያን መጡብህ” አለችው። ከእንቅልፉም ነቅቶ እወጣለሁ እንደ ወትሮውም ጊዜ አደርጋለሁ አለ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ እንደ ተለየው አላወቀም። ፍልስጥኤማውያንም ይዘው ዓይኖቹን አወጡት፤ ወደ ጋዛም አምጥተው በናስ ሰንሰለት አሰሩት፤ በግዞትም ሆኖ እህል ይፈጭ ነበር። የራሱም ጠጕር ከላጩት በኋላ ያድግ ጀመር።

የፍልስጥኤምም መኳንንት “አምላካችን ጠላታችንን ሶምሶንን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን” እያሉ ለአምላካቸው ለዳጎን ታላቅ መሥዋዕት ይሠው ዘንድ ደስም ይላቸው ዘንድ ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ባዩት ጊዜ “ምድራችንን ያጠፋውን፥ ከእኛም ብዙ ሰው የገደለውን ጠላታችንን አምላካችን በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ። ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ “በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት” አሉ። ሶምሶንንም ከግዞት ቤት ጠሩት፤ በፊታቸውም ተጫወተ፤ ተዘባበቱበትም፤ በምሰሶና በምሰሶም መካከል አቆሙት። ሶምሶንም እጁን የያዘውን ብላቴና “ቤቱን የደገፉትን ምሰሶች እጠጋባቸው ዘንድ እባክህ አስይዘኝ” አለው። በቤትም ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ሞልተውበት ነበር፤ የፍልስጥኤምም መኳንንት ሁሉ በዚያ ነበሩ፤ በቤቱም ሰገነት ላይ ሶምሶን ሲጫወት የሚያዩ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ወንዶችና ሴቶች ነበሩ። ሶምሶንም “ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል እግዚአብሔር አምላክ ሆይ እባክህ አስበኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ እባክህ አበርታኝ” ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ።

ሶምሶንም ቤቱ ተደግፎባቸው የነበሩትን ሁለቱን መካከለኞች ምሰሶች ያዘ፤ አንዱን በቀኝ እጁ አንዱንም በግራ እጁ ይዞ ተጠጋባቸው፡፡ ሶምሶንም “ከፍልስጥኤማውያን ጋር ልሙት” አለ፤ ተጎንብሶም ምሰሶቹን በሙሉ ኅይሉ ገፋ፤ ቤቱም በውስጡ በነበሩት በመኳንንቱም። በሕዝቡም ሁሉ ላይ ወደቀ፤ በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ። ወንድሞቹም የአባቱ ቤተ ሰቦችም ሁሉ ወረዱ፤ ይዘውም አመጡት በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በአባቱ በማኑሄ መቃብር ቀበሩት፤ እርሱም በእስራኤል ላይ ሃያ ዓመት ፈረደ።

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተገለጸውም ነቢዩ ሶምሶን ጠላቶቹን ድል የነሣቸው በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት በየካቲት ፲፪ ቀን ነው፡፡

የነቢዩ ሶምሶን አማላጃነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

መጽሐፈ መሳፍንት ከምዕራፍ ፲፫ እስከ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፴፩