‹‹ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች›› (ያዕ. ፭፥፲፮)

የማማለድን ጸጋ ያገኙ ቅዱሳን የምእመናንን ጸሎት ወደ አምላካችን እግዚአብሔር እንደሚያሳርጉ ገድላቸው ምስክር ነው፡፡ የቅዱሳን አማላጅነት እግዚአብሔርን የማክበር ምልክት በመሆኑ ራሱ ሰውን ወደ አማላጅነትም ይመራል፡፡ በምድራዊ ሕይወታችን በመከራና ችግር በምንሠቃይበት ጊዜ ለድኅነተ ሥጋ አምላካችንን እንማጸናለን፤ በተለያዩ ዘመናትም በሰዎች ኃጢአት የተነሳ መቅሠፍት ሲመጣብን ይቅርታና ምሕረትን በመሻት ጸሎታችን ወደ እርሱ ይደርስ ዘንድ ቅዱሳንን እንማልዳለን፡፡ እርሱም ቸር፣ መሓሪ፣ ይቅር ባይ እና ምሕረቱ የበዛ አምልክ ነውና በቸርነቱ ይጎበኘናል፤ ለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ታሪኮች ማስረጃዎች ናቸው፡፡

አማላካችን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ባወጣበት ዘመን ነቢዩ ሙሴ ይመራቸው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም ሕዝበ እግዚአብሔር መሆናቸውን ዘንግተው ትእዛዙን በመተላለፍ ወደ ግብፅ እንዲመልሷቸው ነብዩ ሙሴና አሮን ላይ አንጎራጎሩ፡፡ በአንድነትም ሆነው እየጮኹ ‹‹በዚህ ምድረ በዳ ከምንሞት በግብፅ ምድር ሳለን ብንሞት በተሻለን ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በጦርነት እንሞት ዘንድ ወደዚህች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ለንጥቂያ ይሆናሉ፤ አሁንም ወደ ግብፅ መመለስ አይሻልምን?›› አሉት፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ‹‹ይህ ሕዝብ እስከመቼ ይንቀኛል፤ በፊቱ ባያረግሁት ሁሉ እስከመቼስ አያምንብኝም፤ ከርስታቸው አጠፋቸው ዘንድ በቸነፈር እመታቸዋለሁ›› አለው፤ ሙሴም የእስራኤል ሕዝብ ምሕረትን ያገኝ ዘንድ ወደ አምላክ ጸለየ፤ ‹‹እነዚህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጊዜ ጀምሮ ይቅር እንዳልካቸው እባክህ እንደ ምሕረትህ ብዛት የዚህን ሕዝብ ኃጢአት ይቅር በል አለው››፤ እግዚአብሔርም እንደቃልህ ይቅር አልሁ›› ብሎ ሕዝቡን ማራቸው፡፡ (ዘኁ. ፲፬፥፩-፳)

ዳታንና አቤሮንም በምቀኝነታቸው ከነቤተሰቦቻቸው ምድር ስለዋጠቻቸው ሁለት መቶ ሃምሳ ሰዎች ደግሞ በትዕቢታቸው የተነሳ እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው፤ በዚህም ጊዜ  ‹‹የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አንጎራጎሩ››‹‹እግዚአብሔርም ተገልጾ ሙሴን ‹‹ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፤ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ አለ›› በዚያን ጊዜ ሙሴና አሮን በግንባራቸው ወድቀው ጸለዩ፤ ሙሴም አሮንን ‹‹ፍጠንና ውሰድ፤ ከመሰዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፤ ዕጣንም ጨምርበት፤ ወደ ማኅበሩ ፈጥነህ ውሰደው፤ አስተሰርይላቸው፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቁጣ ወጥቷልና መቅሠፍትም ጀምሯል›› ብሎ አዘዘው፡፡ አሮንም ሙሴ እንዳለው አደረገ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ፡፡››(ዘኁ.፲፮፥፵፩-፶)

የእግዚአብሔርን ሕግ እና ትእዛዛት እያስተማረ ወደ ምድረ ርስት ይወስዳቸው የነበረው ነቢዩ ሙሴ ከፈጣሪያቸው በተላከ መልእክት ቢያጽናናቸውም በእምነታቸው ጉድለት እርሱን መቃወማቸው ለቅጣት ይዳርጋቸው ነበር፡፡ ሆኖም ከአምላኩ ቃል ኪዳን ተገብቶለታልና ሕዝቡን ከጥፋት በመመለስ አድኗቸዋል፡፡

ቅዱሳን በዘመናቸው ባደረጉት ተጋድሎና ትጋት ለሌሎች መዳን ምክንያት ሆነዋል፤ በተለያየ ጊዜም ሰዎችን ከመቅሠፍት፤ ከደዌና ቸነፈር ይታደጋሉ፤ ለሰዎች ፈውስና ድኅነትም ይሆናሉ፡፡ ይህን ተአምር ያዩ እና ያመኑም በጸሎት ይተጋሉ፤ በችግር ጊዜም ከእራሳቸው አልፎ ለሌሎች ድኅነትን ይማጸናሉ፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረውም ‹‹ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ሰው ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች››፡፡ ቅዱሳን ስለኃጥአን የሚለምኑት ልመና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለውና በአማላጅነታቸው አምኖ መለመን ድኅነትን ያስገኛል፡፡ (ያዕ. ፭፥፲፮)

ሀገራችን ኢትዮጵያ በቸነፈር ከተመታች ሰነባብታለች፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብዙዎችን እያጠቃ መሆኑን መረጃዎች በየቀኑ እያስታወቁ ነው፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕሙማን ወደ ሆስፒታል እየተጋዙ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ባሳለፍነው ሳምንታት የቫይረሱ ስርጭት ፍጥነት መጨመር ተገቢው ጥንቃቄ እንኳን እየተደረገ የወረርሽኙን ስርጭት ለስማቆም አለመቻሉ ሌላ ችግር ሆኗል፡፡

ላለፉት ሦስት ወራት በተለይም በዐቢይ ጾም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ካህናትና ምእመኑ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤታቸው ጸሎት እና ምሕላ በማድረግ መድኃኒት የለሹን በሽታ አምላካችን እንዲያርቅልን ተማጽነዋል፡፡ ቢሆንም ግን እስከ አሁን ዘላቂ መፍትሔ ባለመገኘቱ አምላካችን ከቁጣ ወደ ምሕረት እንዲመለስልን እያንዳንዳችን የቅዱሳንን አማላጅነትና ተራዳኢነት ልንማጸን ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን አምላካችንን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሌት ከቀን ያለማቋረጥ በጸሎት፤ በጾም እና በስግደት ያገለገሉ ቅዱሳን አባቶቻችንን በማሰብ ለኃጢአተኞች ምሕረትን እንደሚያደርግ ነው፡፡ በተለይም ጻድቁ አባታችን አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ተጋድሏቸውን ሲፈጽሙ በተሰጣቸው ቃል ኪዳን መሠረት እኛን  ከቸነፈር እንደሚጠብቁን በማሰብ ልንጽናና  ይገባል፡፡ አምላካችን በዕለተ ዕረፍታቸው ከሰማይ ወርዶ በመገለጥ ‹‹መታሰቢያህን ያደረጉትን፣ ዝክርህን የዘከሩ፣ የገድልህን መጽሐፍ የጻፉ፣ ያጻፉ፣ ቤተ ክርስቲያንህን የሠሩ፣ ያሠሩ፣ የሠሩትን ኃጢአት ይቅር እላቸዋለሁ። ወዳጄ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ! ገድልህን የጻፈውን፣ ያጻፈውን፣ ያነበበውን፣ የተረጎመውን፣ ጽፎም በቤቱ ያስቀመጠውን ሰው የተለያዩ በሽታ የሚያመጡ ሰውን የሚፈትኑ ርኩሳን አጋንንት አይቀርቡትም፡፡ ተላላፊ በሽታ ወይም ተስቦ፣ ተቅማጥ፣ ርኃብ ቸነፈር፣ የውኃ መታጣት፣ የልብስ መራቆት፣ መዥገር አይደርሱበትም፡፡ ሌጌዎን የተባለ ክፉ ጋኔንም ፈጽሞ አይቀርብም። ፋኑኤልና ሩፋኤል እስከ ዘለዓለሙ ይጠብቁታል፤ ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ የሰማይ መላእክት በተድላ በደስታ ወደ ሰማይ ያሳርጉታል።›› (ገድለ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ)

እንዲሁም ሕፃኑ ቂርቆስ በሰማዕትነት ባረፈበት ዕለት ጌታችን ጽናቱንና ትጋቱን አይቶ ከመከራ ሊያሳርፈው ፈቀደና ተገልጾለት፤ ‹‹ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ቂርቆስ፤ ወዳጄ ቂርቆስ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎም ሰላምታ ሰጠው፡፡ ‹‹የመከራህን ጽናት የትዕግስትህን ብዛት አይቼ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍህ መጣሁ›› ብሎ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳንን አድርጓል፡፡ ይህም ‹‹…ስምህ በተጠራበት፣ ቤተ መቅደስህ በታነጸበት ሥዕልህ ባለበት ቦታ ሁሉ የሕፃናት እልቂት፣ የከብት በሽታ፣ የእህል እጦት፣ ረኃብ፣ ቸነፈር አይደርስም›› የሚል ነበር፡፡ (ስንክሳር ዘጥር ፲፭)

እኛም በእነዚህ ቅዱሳን አባቶች ከበሽታ፣ ከመከራ እና ከሥቃይ እንዲታደገን ገድላቸውን ገዝተን እንጸልይበት፤ በቤታችንም እናስቀምጥ፤ በቅዱሳን አማላጅነትና ተራዳኢነት እንድን ዘንድ እንማጸናቸው፡፡