ታማኝነት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
መጋቢት ፲፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ታላቁ ዐቢይ ጾም እንዴት ነው? እንደ አቅማችሁ እየጾማቸችሁ ነው? ጠዋት እና ማታስ በዚህ በጾም ወቅት በርትታችሁ ትጸልያላችሁን?! ትምህርትስ እንዴት ነው? ደጋግመን እንደምንነግራችሁ ትምህርት አለማወቅን በማወቅ፣ በማስተዋል፣ ታናሽትን በታላቅነት፣ ጭካኔን በርኅራኄ፣ መጥፍውን በመልካም የምንቀይርበት፣ የምንመኘውን እንዲሁም የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት የሚደግፈን ነው! በዚህ ምደር ስንኖር መመገብ ያስፈልገናል፤ ለመመገብ ደግሞ መሥራት አለብን፤ ምክንያም ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹ሊሠራ የማይወድ አይብላ›› ይላል (፪ኛተሰ.፫፥፲) ልጆች! ለመሥራት ደግሞ ትምህርት ያስፈልጋል፤ ነገ አድጋችሁ በተለያየ ኀላፊነት ላይ ሆናችሁ አገርን እንድታገለግሉና እንድትመሩ ዛሬ በርትታችሁ እንዲሁም ጠንክራችሁ ተማሩ! የወላጆቻችሁ ድካማቸውና ክፍያቸው እናንተ ጎበዝ፣ ብልህ፣ አስተዋይና፣ ታማኝ ስትሆኑ ማየት ነውና በርቱ! ልጆች! ለዛሬ የምንማማረው ባለፈው የጀመርነውን ትምህርት ክፍል ሁለት ነው፤ የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ቀጣዩን ክፍል “ታማኝነት” በሚል ርእስ ይሆናል፤ መልካም ቆይታ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታማኝ ማለት “የማይጠረጠር፣ እምነት የሚጣልበት” ማለት ነው፤ ታማኝነት ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አንዱ ነው፤ በሰዎች ዘንድ መታመን መታደል ነው፤ ልጆች! በማንኛውም ነገር ሁሉ ታማኞች ከሆንን ሰዎች ሲመርቁን እግዚአብሔር ይባርከናል፤ ሰዎች አምነውን “እነርሱ እኮ ታማኝ ናቸው” ሲሉ ልባችን ይደሰታል፤ ደስታ እናገኛለን፡፡

ልጆች! በእርግጥ ሰዎች እንዲያመሰግኑን ሳይሆን ክርስቲያናዊ ግዴታችን ስለሆነ መታመን (ታማኝ መሆን) አለብን፤ የራስ ያልሆነን ነገር አለመንካትና የሰዎችን ነገር አለመመኘት መታመን ነው፤ በቤት ውስጥ፣ በሠፈር፣ በትምህርት ቤት የእኛ ያልሆነ ማንኛውንም ነገር ባለቤቱ ሳያውቅና ሳይፈቅድ መንካት (መውሰድ) አለመታመን ነው፤ ስለዚህ የእኛ ያልሆነ ማንኛውንም ነገር ተቀምጦ አልያም ወድቆ ብናገኝ ለባለቤቱ መመለስ ያስፈልጋል፤ ይህ መታመን ነው፤ ሰዎች እንድንይዝላቸው የሚሰጡንን ነገር በአግባቡ በማስቀመጥ ሲፈልጉት መስጠት ይህ መታመን ነው፤ በዚህ መልካም ምግባራችን እግዚአብሔር ይመሰገናል፤ ሰዎችንም ወደ መልካም ምግባር እንዲመጡ ምክንያት መሆን እንችላለን፡፡

ልጆች! እኛ ታማኞች ከሆንን በቤት ውስጥ፣ በሠፈርም ሆነ በትምህርት ቤት ያሉ ጓደኞቻችንን ወደ መልካም ነገር ማምጣት እንችላለን፤ ስንናገር እንደመጣለን፤ መክረን እንመልሳለን፤ ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹…መልካሙ ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ…›› በማለት አስተምሮናል፡፡ (ማቴ.፭፥፲፮)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታማኝነትን በተመለከተ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ታሪክ እንንገራችሁ፤ ያዕቆብ የተባለው አባታችን ፲፪ (ዐሥራ ሁለት) ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱ መካከል አንደኛው ዮሴፍ ይባላል፤ ይህ ልጅ ከወንድሞቹ በተለየ መልኩ መልካም እና ታማኝ ነበር፤ በዚህም ምግባሩ (በታማኝነቱ) አባቱ በጣም ይወደው ነበር፤ ከሁሉም የተለየ ልብስም አለበሰው፡፡ (ዘፍ.፴፯፥፩-፲፯) ልጆች! አባቱ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርም ወደደው፤ ንጉሥም እንደሚሆን በሕልሙ ገለጸለት፤ (አሳየው) ይህ ሁሉ በታማኝነቱ ነው!

አያችሁ ልጆች! መታመን ምን ያህል ክብር እንደሚያሰጥ! ከዚያም አንድ ቀን ወንድሞቹ በጎችን ይዘው ለእረኝነት ወጡ፤ ዮሴፍም ለወንድሞቹ ምሳ እንዲያደርስላቸው ተላከ፤ እነርሱ የነበሩት በጣም ሩቅ ቦታ ነበርና ሲፈልጋቸው ውሎ ደከመው፤ ለእርሱ የተሰጠው ስንቅ አለቀበት፤ እንደገናም ራበው፤ የሚገርማችሁ ነገር ልጆች! የሚበላ ምግብ ይዟል፤ ግን ራበው፤ የያዘው ምግብ ለወንድሞቹ እንዲያደርስ የተሰጠው ነውና በታማኝነት ሳይነካው ደክሞትና ርቦት ሳለ በዚህም ታማኝነቱ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና “ድንጋዩን በተአምራት ዳቦ እንዲሆን አደረገለት፤ ከዚያም በላና ጠነከረ፤ የወንድሞቹንም ምግብ (ስንቅ) በታማኝነት ምንም ሳይነካ ይዞላቸው ሄደ፤ (የማቴዎስ ወንጌል ፬፥፫ ትርጓሜ አንድምታ)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እስኪ ራሳችንን በእርሱ ቦታ አድርገን እንመልከት! የሚበላ ነገር ይዘን ቢርበን ምን እናደርጋለን? መቼም ታምነን አንነካም እንል ይሆንን? ወይስ ከሚርበኝ ልብላውና ይቅርታ ልጠይቅ እንል ይሆን? ወይስ ሳይታወቅ ቀስ ብለን ቆረስ አድርገን እንበላ ይሆን! ይህንን ጥያቄ ራሳችንን እንጠይቅ? ምን ያህል እንታመን ይሆን? ወላጆች ሲልኩን በታማኝነት ሳንነካ የምናደርስ፣ ጓደኞቻችንን በአደራ የሰጡንን በአግባቡ በታማኝነት የምንይዝ ምን ያህሎቻችን እንሆን?

ልጆች! መታመን ከትንሽ ነገር ይጀምራል፤ አንድ ነገር እንድናደርግ ሲነገረን “እሺ” ብሎ መፈጸም፣ ለራሳችን ከመታመን መጀመር፣ በትምህርት ቤታችን በመምህራን ዘንድ መታመን፣ ያልደከምንበትን ውጤት ለማግኘት አለመሞከር፣ ራሳችን ደክመን፣ በርትተን ባጠናነው፣ በርትተን በተማርነው፣ በርትተን በተፈተነው የፈተና ውጤት ብቻ ለማለፍ መታመን አለብን፡፡ ይህ ተግባር እያደገ ሲመጣ ታማኞች እንሆናለን! አያችሁ ዮሴፍ በመታመኑ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት፤ የሚፈልገውን ዳቦ ሰጠው፤ በመታመኑ እግዚአብሔር አነገሠው፡፡ መታመን አለመጠርጠር ለታላቅ ክብር ያበቃናል፤ ስለዚህ ታማኞች እንሁን! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹…በጥቂቱ ታምነኻል በብዙ እሾምሃለሁ…›› በማለት እንደነገረን በብዙ እንድንሾም በጥቂቱ እንታመን! (ማቴ.፳፭፥፳፫) መታመን (ታማኝነት) ክብሩ ለራስ ነውና ታማኝ እንሁን!

አምላካችን እግዚአብሔር ታማኞች ሆነን ለክብር እንበቃ ዘንድ ማስተዋሉን ይስጠን፤ አሜን! ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!