ብሥራተ ገብርኤል

ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ብሥራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጦ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ መወለድ ያበሠራት ዕለት ታኅሣሥ ፳፪ ‹‹ብሥራተ ገብርኤል›› ታላቅ በዓል ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ በምትፈትልበት ሰዓት ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ ‹‹ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች መካከል አንቺ የተባረክሽ ነሽ›› አላት፤ ድንግል ማርያምም  ‹‹እንዲህ ያለ የምስጋና እጅ መንሻ እንዴት ይደረግልኛል?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም  ‹‹ማርያም ሆይ አትፍሪ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና፤ እነሆ ትፀንሺያለሽ፤ ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ ይህ የሚወለደው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው፤ እርሱም  የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› አላት፡፡  እርሷም ‹‹ይህ ነገር እንደምን ይሆንልኛል፤ ወንድ ሳለውቅ?›› አለችው፡፡ መልአኩ ገብርኤልም ‹‹መንፈስ ቅዱስ ይጠብቅሻል፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል›› አላት፡፡ እርሷም የመልአኩን ቃል ተቀብላ ‹‹እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ አካላዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ ቅድስት ማርያም እምነቷን በእግዚአብሔር ላይ አድርጋለችና በትንቢተ ነቢያት መሠረት በድንግልና ፀነሰችው፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱፣ ኢሳ. ፯÷፲፬ )

ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ስለ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትና ስለ አምላክ ሰው መሆን ሲመሰክር ‹‹እርሱ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ቅዱስ ገብርኤል የሚባል መልአክ ወደ አንቺ ላከ፤ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ያድራል፡፡ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል አለሽ፤ ከአባቱ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማሕፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መላኮት በማሕፀንሽ አደረ›› (ቅዳሴ ማርያም ቁ. ፵፭) ብሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የብሥራት ቀን በማሰብ ታከብረዋለች፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፤ ቅዳሴ ማርያም