ባሕረ ሀሳብ

የእስክንድርያ ዐሥራ ሁለተኛ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ ባሕረ ሀሳብን ሲደርሰው  የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያልነበረው በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ ሆኖም ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሥርዓት የተመራችበትን የዘመን አቆጣጣር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሊደርሰው ችሏል፤ ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡

ቅዱስ ድሜጥሮስ አባቱ ደማስቆ ወይም እንድራኒቆስ አጎቱ ደግሞ አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ ይባላሉ፡፡ ሁለቱም በዘመነ ሰማዕታት ከኢየሩሳሌም ርቀው በባዕድ ሀገር በፋርስ ባቢሎን በስደት ለረጅም ዘመናት ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህ የስደት ዘመናቸው ከሁለቱ (ደማስቆና አርማስቆስ) በስተቀር በሀገሩ የሚኖሩት አሕዛብ ነበሩ፡፡ ለድሜጥሮስ አጎት አርማስቆስ ልዕልተ ወይን የምትባል ሴት ልጅ ነበረችው፤ መሞቻው ጊዜ በደረሰም ጊዜ ለወንድሙ እንድራኒቆስ ‹‹ልጄን ለአሕዛብ እንዳትድራት›› ብሎ አምሎት ሞተ፡፡ ልዕልተ ወይን ለአቅመ ሔዋን በደረሰችበት ወቅት ድሜጥሮስም ለአቅመ አዳም ደርሶ ነበርና አባቱ ደማስቆ ‹‹ልጄን ከአሕዛብ ጋር አጋብቼው የሃይማኖት ዝምድና ከሚፈርስ የሥጋ ዝምድና ቢፈርስ ይሻላል›› ብሎ ከወንድሙ ልጅ ከልዕልተ ወይን ጋር አጋባቸው፡፡ እነዚህ ሁለት የታላቅና የታናሽ ልጆች ከተጋቡ በኋላ እንደወጉ ሥርዓተ መርዓት ወመርዓዊ እንዲፈጽሙ በሰርጋቸው ዕለት ማታ በጫጉላ ቤት ትተዋቸው ሳለ ሁለቱም ሀዘን ገብቷቸው ያለቅሱ ጀመር፡፡ የሀዘናቸው ምክንያት ደግሞ የወንድማማች ልጆች ሆነው ሩካቤ ሥጋ ለመፈጸም ባለመፈለጋቸው ነበር፡፡ ያን ጊዜም ልዕልተ ወይን እንዲህ ስትል ጠየቀች፤ ‹‹ለመሆኑ ይህንን ያደረከው አኔን ንቀህ ነው ወይስ ዝምድናችንን ንቀህ?›› ድሜጥሮስም መለሰ እንዲህ በማለት ‹‹አንቺንም ዝምድናችንንም ንቄ ሳይሆን የአባቴን ለቃድ ለመፈጸም ነው፡፡›› ከዚህ በኋላ ሁለቱም ከስምምነት ላይ ደረሱ፤ ይኸውም ያለሩካቤ ሥጋ በድንግልና ለመኖር ነበር፡፡ በሰዎች ዘንድ ግን እንደባልና ሚስት በመምሰል ለመኖር ተስማሙ፤ በዚህ ሁኔታ ዐርባ ስምንት ዓመታትን በድንግልና ኖረዋል፡፡

ከዕለታት በአንድ ቀን ድሜጥሮስ ገበሬ እንደመሆኑ ወደእርሻው በሚገባበት ወቀት ያለጊዜያቸው ያፈሩ ሦስት የስንዴ ዛላ እና አንድ የወይን ዘለላ አግኝቶ በመገረሙ ከልዕልተ ወይን ጋር ተመካክሮ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወሰደው፡፡ በዚህን ዕለት የመንበረ እስክንድርያ ዐሥራ አንደኛ  ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ዩልያኖስ /ዩልዮስ/ ከዕድሜ ብዛት የተነሣ በማርጀቱ ከእርሱ ቀጥሎ የሚሾመውን ጳጳስ በሱባዔ አየ፡፡ ሕዝቡን በቤተ እግዚአብሔር ቤት ሰብበስቦ ሊነግራቸው ባሰበበት ወቅት ቅዱስ ድሜጥሮስ ከእርሻው ያገኘውን አንድ የወይን ዘለላ እና ሦስት የስንዴ ዛላ ይዞ መጣ፡፡ ለጳጳሱ በሰጠው ጊዜ ከእርሱ ቀጥሎ እንደሚሾም በሱባዔ ስለተገለጠለት ቅብዓ ሜሮን ቀብቶ ሥርዓተ ጵጵስናን ፈጽሞለታል፡፡ ይህ ሲሆን ግን ድሜጥሮስ አላወቀም ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቅዱስ ዩልያኖስ አረፈ፡፡ ሕዝቡም ቅዱስ ድሜጥሮስ ጳጳስ እንደሚሆን ቅዱስ ዩልያኖስ ነግሯቸው ስለነበር ወንበር ባዶውን አያድርምና ‹‹በአባታችን ቦታ ተቀመጥ (ተሾምልን)›› ብለው ያዙት፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስም ‹‹እኔ ገበሬ፤ ሕጋዊ ሚስት ያገባሁ ነኝ፤ እንዴት በንጹሕ በማርቆስ ወንበር ላይ እቀመጣለሁ? በምን ዓይነት ሁኔታስ ጳጳስ እሆናለሁኝ?›› ቢላቸው ግድ አሉትና ሾሙት፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ ቅዳሴና መጻሕፍት (ብሉይና ሐዲስ) ተገልጾለት ሕዝቡን አስተምሯል፡፡ የሕዝቡ ኃጢአት እየታየውም ‹‹አንተ በቅተሀል ቁረብ፤ አንተ ግን ገና ነህ›› እያለ ይመልስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ሕዝቡ ‹‹ጋለሞታውን አቅፎ በማርቆስ ወንበር ላይ ብናስቀምጠው እኛን አትቁረቡ ይለናል›› ብለው በሀሜት ወደቁ፡፡

ከዚያም በኋላ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ዝም በማለትህ ሕዝቡ በሀሜት ተጎዱ፤ በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ነገር ግለጽ›› ብሎ አዘዘው፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስም ሕዝቡ አንድ አንድ እንጨት ይዘው ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እንጨቱንም አስደምሮ (አቃጥሎ) ቅዳሴ ገባ፤ ከቅዳሴ ሲወጣም በእሳት ውስጥ እየተመላለሰ አጠናቸው፡፡ ልዕልተ ወይንን ከሴቶች መቆሚያ ጠርቶ ‹‹መጐናጸፊያሽን ዘርጊ›› በማለት ልብሷ ላይ ፍሕሙን ዘግኖ ቢያስቀምጠው ከዘሃው ላይ አንዲት እንኳን ሳይጠቁር ቀርቷል፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ይህንን አይተው ‹‹አባታችን ሆይ ይህንን የሠራኸውን ሥራ ታረዳን ዘንድ ከቅድስናን እንሻለን›› ቢሉት ‹‹የሠራሁት ከንቱ ውዳሴን ሽቼ አይደለም፡፡ እናንተ እኔን አምታችሁ ስለእኔ እንዳትጐዱ እንድትድኑም ከዚህች ሴት ጋር በመካከላችን ተሠውሮ ያለውን ምሥጢር እገልጽላችሁ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስለአዘዘኝ ነው እንጂ›› አላቸው፡፡ በዚያን ጊዜም በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቀው ለመኑት እርሱም ይቅር አላቸው፤ አጽናናቸውም፡፡

ቅዱስ ድሜጥሮስ መቶ ሰማንያ አስከ ሁለት መቶ ሃያ ሁለት ዓ.ም በመንበረ እስክንድርያ ላይ ሲቆይ ትልቅ ምኞትን ይመኝ ነበር፡፡ ይኸውም ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾምና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ በዓለ ደብረ ዘይት፣ በዓለ ሆሳዕና፣ በዓለ ትንሣኤና በዓለ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ፤ በዓለ ርክበ ካህናትና ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፤ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፤ በዓለ ስቅለት ከዓርብ ባይወጡ፤ ባይነዋወጡ ይመኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ በዓላት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነበረበት ዘመን በእነዚህ ቀናት ስለዋሉ ነው፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ በዓላትና አጽዋማት ከጥንት ዕለታቸው እንዳይወጡ ሲመኝ የታዘዘ መልአክ ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹ነገር በምኞት ይገኛልን? ሱባዔ ገብተህ አግኘው›› ብሎ ነገረው፡፡ ‹‹ከሌሊቱ ሃይ ሦስት ሱባዔ ግባና አበቅቴ ይሁንህ፡፡ ከቀኑ ሰባት ሱባዔ ገብተህ መጥቅዕ ይሁንህ›› ብሎም አዘዘው፡፡ ‹‹ሌሊቱን አብዝቶ ቀኑን ለምን አሳነሰው›› ቢሉ ቀን የታመመ ሲጠይቅ፣ የታሰረ ሲጎበኝ፣ ወንጌል ሲያስተምር ስለሚውል ቀኑን አሳጥሮ ሌሊቱን አስረዝሞታል፡፡›› አወጅ፡- ማንኛውም ቁጥር ከሰላሣ ከበለጠ በሠላሳ (በዐውደ ወርኅ) እንግደፈው ወይንም ለሠላሳ እናፍለው፡፡ እንደሚታወቀው አንድ ሱባዔ ማለት ሰባት ቀናት ናቸው፡፡ ሰባት ጊዜ ሃያ ሦስት መቶ ስድሳ አንድ ይሆናል፡፡ መቶ ስድሳ አንድን በሰላሳ ስንገድፈው/ስናካፍለው/ አምስት ዐውደ ወርኅ ሆኖ ዐስራ አንድ ይቀራል፡፡ ዐስራ አንድን ‹‹አበቅቴ›› ብሎታል፡፡ የቀኑን ሰባት ሱባዔ በሰባት ስናባዛው ዐርባ ዘጠኝ ይሆናል፡፡ በሰላሳ ስንገድፈው /ስናካፍለው/ አንድ ጊዜ ደርሶ ዐሥራ ዘጠኝ ይተርፋል፤ ይህንን ‹‹መጥቅዕ›› ብሎታል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ ኢየዓርግና ኢይወርድ ተገልጾለት ባሕረ ሐሳብን አስተምሯል፡፡

ከሁለት ጥምር ቃል የተገኘው ባሕረ ሀሳብ ‹‹ቁጥር ያለው ዘመን›› የሚል ትርጓሜ እንዳለው ከዚህ እንረዳለን፡፡ የእያንዳንዱን ቃላት ፍቺ በተናጠል ብናይ ‹‹ባሕር›› ዘመን ‹‹ሀሰበ›› ደግሞ ቆጠረ ማለት ነው፡፡ በዚህም ባሕረ ሀሳብ የዘመን አቆጣጠር ማለት ይሆናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኃ ጥቅምት