በፍቅር ተቀበለኝ!

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

እኔ ራሴን ዓይኔን ተመልክቼ

ቁመና ደም ግባቴን በመስታወት ለክቼ

ቁንጅናዬን ሳደንቅ

በአፈጣጠሬ ስመጻድቅ

እንዲህ አበጃጅቶ የፈጠረኝ

ለየት አድርጐ ከፍ ያደረገኝ

መጨረሻዬ ምን ሊሆን ነው? እንዲህ ያሳመረኝ?

እንደ ሐውልት ቀርጾ ዘለዓለማዊ ሊያደርገኝ?

ወይስ እንደ  አለት አበርትቶ እንደ ተራራ ሊያጸናኝ

መልሱን መረመርኩኝ . . . . .

ለካስ!. . . እንደ ሰውሰው አድርጐ የፈጠረኝ

በዕድሜ ገመድ የምታሰር ደካማ ነኝ

ዛሬ ውበቴ በአደባባይ ተለፍፎ

በአመሻሹ እንደ አበባ ረግፎ

ነገ አፈር ነኝ በመቃብር የምተኛ

ነገ ሙት ነኝ

በዛሬ ማንነት የምጠየቅ በደለኛ

ምግባሬ ሆኖብኝ የመረረ ፍሬ

በአጋንንት ሰንሰለት የፊጥኝ ታስሬ

በዝሙት ተለክፌ ሰውነቴ ረክሶ

በኃጢአት አረንቋ እግሬ ተለውሶ

ሰዎች ተጸይፈው ምራቅ ሲተፉብኝ

በደሌን ዘርዝረው ሲጠቋቆሙብኝ

ዘመድ እንደሌለው ከሰው ተለይቼ

ስኖር በምድር ላይ አንገቴን ደፍቼ

ቅድመ ዓለም የነበረ የተወለደ ከአባቱ

ድኅረ ዓለም የተገኘ ከማርያም ከእናቱ

ለበሽተኞች መድኃኒት ለኃጥአን ተስፋ

መናፍስትን የሚገሥጽ ደዌን የሚያጠፋ

ወዳጅ ስላገኘሁ ሸክሜን የሚሸከም

ዓለም ትቼሻለሁ፣ ላልመለስብሽ  ሄድኩኝ ለዘለዓለም

የማይጨበጥ እሳት የሚዳሰስ ሰውነቱን

በሽቶ ላከብረው. ልዘክረው ሞቱን

አነባሁ አለቀስኩ እንደ አንዷ እንዲቆጥረኝ ከባሮቹ

ስለመራኝ ስለ ፍቅሩ ተደፍቼ ከእግሮቹ

ተጸጽቼ በእንባዬ ብማጸነው ማረኝ ብዬ

የትናንት ማንነቴ ከዛሬው ተለየ።

ኃጢአቴን ደምስሶ ወገኑ ሊያደርገኝ

ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ተቀበለኝ!

ይህን የዓለም መድኅን የበጐች እረኛ

የድንግል ማርያም ልጅ የእውነት መገኛ

ከአብ የተላከ ለአዳም ዘር ሁሉ እንዲሆን መዳኛ

አይሁድ በቅንዓት በመስቀል ሰቀሉት

መከራን አጽንተው ጌታዬን ገደሉት

ሦስት ቀን በሙሉ ኀዘን በርትቶብኝ

የሚያጽናናኝ ጠፋ አይዞሽ የሚለኝ

ገና በማለዳ በሌሊት በድቅድቅ

ወጋገን ሳይታይ ፀሐይ ሳይፈነጥቅ

እንባዬን ጠርጌ ኀዘኔን ቋጥሬ

ተነሣሁ ማለዳ በወፎች ዝማሬ

ሽቶዬን አንግቤ እግሮቹን ልቀባው

ከመቃብር ስፍራ ሔድኩኝ ልሳለመው

በልቤ ሰሌዳ ፍቅሩ ተስሎብኝ

የአይሁድ ማስፈራራት ዛቻው ሳይታየኝ

የፈሪሳውያን የሞት ፍርድ ሳይገታኝ

የካህናት አለቆች ጅራፍ ሳያቆመኝ

የራስ ቅል ከሆነች ተራራማ ቦታ

ገሰገስኩ ወጣሁኝ ወደ ጎለጎታ

ከመቃብር ስፍራ ድንጋይ ተፈንቅሎ

የተከፈነበት ጨርቅ ተጠቅልሎ

ሥጋው ከተኛበት ጌታን ስላጣሁት

ወስደውታል ብዬ ለቅሶዬን ጀመርኩት

የሰማይ መልአክ መተከዜን አይቶ

ፊቱን እንደ ፀሐይ ልብሱን አብርቶ

የሰው ልጅ ተገርፎ መከራ ሊቀበል

ከኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰቀል

ሞትን በሞት ሽሮ አዳምን ሊያከብረው

በሦስተኛው ቀን ሊነሳ ግድ ነው

ሕያው ከሙታን መካከል እንዴት ይፈለጋል

እንደተናገረው ክርስቶስ ተነሥቷል

ይህንን ሄዳችሁ ለዓለም ንገሩ

የክብሩን ጌትነት ዝናውንም አውሩ

በሚያጽናና ቃላት በፍጹም ደስታ

ምሥራች ነገረኝ ይገባል እልልታ

ሰማያት ራዱ ምድር ተናወጠች

መለኮት መሸከም ዓለም ስላልቻለች

ከመቃብር ስፍራ ብርሃን ፈነጠቀ

የቀራንዮ አምባ አበራ ደመቀ

በጨለማ ያለን ብርሃን ወጣልን

ሞት የነገሰብን ሕይወትን አገኘን

የሲኦል በራፏ ቁልፎቿ ተሰብሯል

ለአዳም ልጆች ሁሉ ድኅነት ተበሥሯል

ከርስት ጉልታችን ስንኖር ተፈናቅለን

ዛሬ ግን በጌታ ገነት አገኘን

በአትክልቱ ስፍራ መንገዴን ሳቀና

ማርያም ብሎ ጠራኝ ጌታ በጐዳና

‘ረቡኒ’ አልኩት መምህር ነውና

በእውነት እንዳለ ክርስቶስ ተነሥቷል

ለሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤው አብርቷል!!!