‹‹በዚያን ጊዜ ይጾማሉ›› (ማቴ.፱፥፲፮)

ዲያቆን ይትባረክ ብርሃኔ

ሰኔ ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት በዓለ ጰራቅሊጦስ በዋለ ማግስት ጀምሮ የሚጾመው ጾም ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል። የዚህ ጾም የመግቢያው ቀን በየዓመቱ የሚለያይ ሲሆን “ቢፈጥን ከግንቦት ፲፮ አይቀድምም፤ ቢዘገይ ደግሞ ከሰኔ ፳ አያልፍም” ብለው ሊቃውንት አባቶቻችን ያስተምራሉ። ይህ ጾም የሚፈታበት ቀን ግን እንደ መግቢያው የማይቀያየር ሲሆን ሁልጊዜ ሐምሌ አምስት በቅዱሳን ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ የሰማዕትነት መታሰቢያ በዓል ቀን ጾሙ ይጠናቀቃል።

በዚህ ጾም የሐዋርያት ክብራቸው፣ ቅድስናቸው እንዲሁም  አገልግሎታቸው ይታሰባል፡፡ ሁሉን ትተው ጌታን መከተላቸው፣ ዓለምን ዞረው ማስተማራቸውና ስለ ቅዱስ ስሙ በጽናትና በጥብዐት መከራ መቀበላቸው ይታወሳል፡፡ ስለ ተሰጣቸው የወንጌል አደራ እስከ ሞት ድረስ መታመናቸው ይሰበካል።

ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ጾም ሁለት ነገሮችን መሠረት በማድረግ ጾመውታል። የመጀመሪያው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወላቸውን ጾምን የአገልግሎት መጀመሪያ የማድረግ አርአያነት ነው። ይኸውም ክብር ይግባውና አምላካችን ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ አብ በሰማይ ተናግሮ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ ክብሩ፣ አምላክነቱ የባሕርይ ልጅነቱ የተገለጠ ሲሆን ከተጠመቀ በኋላ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ ቀን እና ፵ ሌሊት ጾሟል። (ማቴ.፫ እና ፬) ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን ጌታችን ያደረገውን ተግባር አርአያ በማድረግ በበዓለ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ፣ ኃይልን ተቀብለው የጸጋ ልጅነታቸው ሲገለጥ ለአገልግሎት ከኢየሩሳሌም ከመውጣታቸው በፊት ጾምን የአገልግሎታቸው መጀመሪያ በማድረግ ጾመዋል። ይህም አርአያነት ቀጥሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እና በርናባስ ለስብከት አገልግሎት በተለዩ/በተመረጡ ጊዜም ጾመዋል። (ሐዋ.፲፫፥፪-፫) ስለዚህ ጾምን የአገልግሎት መጀመሪያ ማድረግ የመጀመሪያው መሠረት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀራጭ በነበረው በማቴዎስ ቤት ተቀምጦ ሳለ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ‹‹እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድን ነው?›› ብለው ለጠየቁት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ነው። ይኽውም  ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወስድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ይጾማሉ›› ብሎ የመለሰው መልስ በሐዋርያት በተግባር መፈጸሙን እንድረዳ ነው። ይህም ቃል ይፈጸም ዘንድ ሚዜዎች የተባሉ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙሽራው ክርስቶስ ከእነርሱ በተለየ/ባረገ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ጾመውታል።(ማቴ.፱፥፲፴-፲፮)

ዛሬ ደግሞ እኛ ክርስቲያኖች ከቅዱሳን ሐዋርያት በረከት እንሳተፍ ዘንድ ይህን ቅዱስ ጾም እንጾማለን። እነርሱ ጾመው በጀመሩት አገልግሎት ዓለምን በስብከተ ወንጌል ጨው ሆነው እንዳጣፈጡ በክህነት የሚያገልግሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክላቸው፣ ይቀበልላቸው፣ ያሳካላቸው ዘንድ በትጋት ሆነው ይጾሙታል። ይህ ሲባል ግን ምንም እንኳን ይህን ትልቅ በረከት የሚያሰጥ ጾም ‹‹የቄስ ጾም›› እያሉ ራሳቸውን የሚያስቱ ቢኖሩም ቤተ ክርስቲያናችን ግን በቀኖና ወስና የዐዋጅ ጾም ብላዋለችና ሁላችንም ክርስቲያኖች ከሰባት ዓመት ጀምሮ ልንጾመው ይገባል። (ፍት.ነገ.፲፭፣ገጽ.፭፻፷፮)

በዚህ ጾም ቅዱሳን ሐዋርያት ራሳቸውን ለአገልግሎት እንዳዘጋጁ፣ እንደጸለዩ እና አገልግሎታቸውንም እንደፈጸሙ እኛም በቀጣይ ልንጀምረው ያሰብነው በልቦናችን ያለው መልካም አሳብ ይፈጸም ዘንድ እግዚአብሔርን እየለመንን እንጾመዋለን። የእነርሱን አገልግሎት የባረከ አምላክ የእኛንም አገልግሎታችንን፣ ሥራችንን፣ ትምህርታችንን፣ ትዳራችንን በአጠቃላይ ሕይወታችንን እንዲባርክልን እየተማጸንን እንጾመዋለን።

የቅዱሳን ሐዋርያት ረድኤት፣ በረከት፣ ድል የምትነሣ፣ ጥርጥር ነቅዕ የሌለባት ሃይማኖታቸው ከሁላችን ጋር ትሁን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!