በዓይኖችህ ታየዋለህ

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

ታኅሣሥ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በሰማርያ ረኃብ በጸናበት ዘመን የሚቀመስም ጠፋ፤ ከረኃቡ ጽናት የተነሣ እናት ልጇን እስከ መብላት ደረሰች። በእዚያም ሀገር ኤልሳዕ የሚባል የእግዚአብሔር ሰው ነበረ። እንዲህም አለ፤ ነገ በዚህች ከተማ በአንድ ሰቅል አንድ መሥፈርያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ሁለት መስፈርያ ገብስ ይሸመታል። ያኔ ንጉሡ በእግዚአብሔር ላይ ተገዳደረ፤ እንዴት ይቻላልም አለ። የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳ እንዲህ አለው፤ “ታየዋለህ እንጅ አትቀምሰውም” ልብን የሚከፍል ንግግር! በረኃብ የቆየች ሀገር ደስ በምትሰኝበት ሰዓት የማይጨበጥ ሕልም ሲሆን ምንኛ ያሳዝናል?  የሶርያ ንጉሥ ሲመኘው የኖረውን ነገር በዓይኑ አየው ግን አልቀመሰውም።  (፪ነገ.፯፥፪)

በእውነት ዛሬ ስንት ነገር ተመኝተን ሳንቀምሰው ቀረን? እየፈለግነው የማናገኘው፣ እየጠራነው መልስ ያጣንለት፤ ምን ያህል ጉዳይ አለ? አንባቢ ሆይ! እስኪ ምኞትህ እንደ ሕልም የማይጨበጥ የሆነበትን ጊዜ ቆም ብለህ አስበው፤ አሰብክ? ምክንያቱ ምንድን ነው? አለፈልኝ ስትል አንተ እራስህ ማለፍ የምትጀምርበት ለምንድን ነው? በእግዚአብሔር ላይ ስለምታጉረመርም አይደል?  እምነትህ በሥጦታው እንጅ በሰጭው ላይ ስላልሆነ? አስታውስ! ጥሩ ነገር ስታገኝ “ይህን አደረኩ፤ የልፋቴ ውጤት ነው” ያልክበትን ጊዜ፣ በተቃራኒው ደግሞ አንተን ደስ የማይልህ ነገር ሲሆን “እግዚአብሔር ይህን አረግኝ” እያልክ እርሱን የከሰስክበትን ጊዜ ቆም በልና አስተውል! ትክክል ማን ነው? ያደረገልህን አመስግነህ ታውቃለህ? “የረዳኝ አምላኬ ነው ብለህስ ይሆን?” እንጃ! እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? ቤት ሠርተሃል? ብዙ ሀብትም አከማችተሃል? በእዚያስ ትኮፈሳለህ። እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል፤ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድር የእግሬ መረገጫ ናት፡፡” (ኢሳ.፷፮፥፩) እናም ምድር ላይ እግሬን ላሳርፍ ነውና ቤትህን አንሳ ቢልህ ወዴት ትወስደዋለህ? ወዴትስ ታሸሸዋለህ? ሀብትህንስ በየት ታከማቸዋለህ? እሽ ርእሱን ተወው! አንተ እራስህ ወግድልኝ ቢልህ ወዴት ትሔዳለህ? አስተውል! አንተ የእኔ ብለህ የምትመፃደቀው ሀብትህ ይቅርና አንተ እራስህ እኮ ያንተ አይደለህም። ታዲያ ለምን የፈጠረህን ማመስገን አፍህ ተያዘ? ዲዳስ ደንቆሮስ ለምን ሆንክ? በእግዚአብሔር ላይ እያመጽክስ የሰበሰብከውን የምትበላው ይመስልሃል?

ልብ ስለሌለህ፦ “አሁንስ አበዛኸው ምን እያልክ ነው? እንዴት ደግሞ ልብ የሌለኝ?” ትለኝ እንደሆነ ልብህ ካንተ ጋር መቼ አድሮ ያውቃልና ብየ እመልስልሀለው። ንገረኝ እስኪ! የሕይወት መውጫ የሆነው ልብህ በሙት ለሙት መንደር ሲኮበልል እንደ ጥንብ አንሳ እሬሳ ፍለጋ የት ነው ምትውለው? አስተውል! አልታደል ብለህ እንጅ አንተ እኮ ትውልድህ ቤተልሔም ክርስቶስ የተወለደበት፣ ውሎህ ከመላእክት ጋር፣ ምስጋናህ አዲስ የሆነ፣ ከመላእክት ጋር በኅብረት የምታመሰግን፣ ሀገርህ በሰማይ፣ ምግብህ የንጉሡ ፍሪዳ፣ መጠጥህ ሰማያዊው ወይን ሆኖ ሳለ አንተ እያየኸው የማትቀምሰው ፍርፋሪ ፍለጋ አሰር ስትቅም የምትውል አይደለህምን። ልብ በል ወዳጄ! ከመንደርህና ከሀገርህ ወጥተህ ከሰማያዊው ማዕረግህ ወርደህ፣ መንደር ለመንደር ሥጋ ፍለጋ ስትዋደቅ ስትውል! አያሳዝንም? ልብህ ከብልሎ አንተን ፍለጋ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው ከሙታን ሰፈር ሲያገኝህ ምን የሚልህ ይመስልሃል? ታየዋለህ እንጅ አትቀምሰውም የሚልህ አይመስልህምን?

አንባቢ ሆይ! ሞት እንዳለስ የምታስታውሰው መቼ ነው? ዘመድ፣ ጎረቤት፣ እኅትና ወንድም ሲሞት ነው? ወይንስ መቼ ነው? ሥጋ ቤትና የሬሳ ሳጥን አንደ ሰፈር ሁነው፣ አንተ ልትጠጣና ልትበላ ስትገባ የሬሳ ሳጥን ሊገዙ የመጡ ሰዎችስ አልገጠሙህም? አስተውል! መጠጥ ቤት ገብተህ ስትጨፍር በርህ ላይ የሬሳ ሳጥን አለ። ያም ሳጥን ያንተ መቀበርያ ነውና ሞት እንዳለ ሊያስተምርህ የተላከልህ የንስሓ መምህርህ አድርገው። ከሚመጣው መቅሠፍት ታመልጥ ዘንድ በማስተዋል ተራመድ። ዛሬም ኤልሳዕ የሆኑ መምህራን “ታየዋለህ እንጅ አትበላውም” እያሉ ድምጻቸውን እያስተጋቡ ነውና በእርጋታ ሁነህ አድምጣቸው። ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመምጣት ቸኩል እንጅ ከቤቱ ለመውጣት አትቸኩል፤ ምንም አታተርፍምና።

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ! የሦርያው ንጉሡ እንደተባለው ያ አስከፊ የራብ ዘመን አልፎ ሊበላ ወደ ቤተ መንግሡት ሲገባ ወድቆ በእራሱ አገልጋዮች ተረጋግጦ ሞተ አይቶት፥ ሊበላ ተመኝቶት፥ ሳይበላው ቀረ፤ እናም ወዳጄ ሆይ አይተኸው ያልበላኸው ነገረ እንዳለ አስተዋልክን? እግዚአብሔር በሰዎች ላይ ድንቅ ሥራ ሲሠራ አየኸው? አንተ ግን ነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቀምሳችሁ እወቁት” እያለህ አሻፈረኝ ብለህ አይተህ ሳትቀምሰው ቀረህ። (መዝ.፴፫፥፯) የሚደንቀው ግን “ሥጋዬን ብሉ፤ ደሜን ጠጡ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ” እየለህ ሁሌ በቤተ ክርስቲያኑ ሲፈተት ምእመናኑ ሲበሉት እያየህ ዝም ብለህ ስትመጣ ምነኛ ታሳዝናለህ? እንደ ንጉሡ አይተኸው ሳትቀምሰው ስትቀር?

በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረምህን ትተህ፣ የሽንገላ ኑሮህን አስወግደህ፣ ከሙታን መንደር ወጥህ፣ የሚጠቅምህን ብቻ አድርግ! ቸርነቱ የበዛው አምላክ ትቀምሰው ዘንድ በስስት ዓይኑ እያየህ፥ እየጠበቀህ፥ ነውና ተነሣ፤ ሳትሞት ከሙታን መንደር ተነሥተህ ብላ!