በዓለ ፅንሰቱ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

መጋቢት ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የዓለም ቤዛ፣ የዓለም መድኃኒት፣ የሰው ልጆች አዳኝ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ ወደ ምድር ይመጣ ዘንድ የድኅነት ግብሩ የተፈጸመበት የምሥራች ቃል የተነገረበት እንዲሁም ከንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰበት ዕለት መጋቢት ፳፱ ታላቅ በዓል ነው፡፡ የነገረ ድኅነቱ የመፈጸሚያ ጅማሮ ይህ ዕለት የተቀደሰ በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ትዘክረዋለች፤ ታከብረዋለችም፡፡

ቅዱሱ መጽሐፍ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሟ ናዝሬት ወደምትባለው ወደ አንዲት የገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሚሆን ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨችው ወደ ድንግል ተላከ፤ የዚያችም ድንግል ስሟ ማርያም ይባል ነበር፡፡ መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ÷ ‹‹ደስ ይበልሽ÷ ጸጋን የተመላሽ ሆይ÷ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ›› አላት፡፡ እርስዋም ባየችው ጊዜ ከአነጋገሩ የተነሣ ደነገጠችና ‹‹ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?›› ብላ አሰበች፡፡ መልአኩም እንዲህ አላት÷ ‹‹ማርያም ሆይ÷  በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ፡፡ እነሆ ትፀንሺያለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፡፡ እርሱም ታላቅ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤  እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ ለያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለሙ ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም›› አላት፡፡  ማርያምም መልአኩን ‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?›› አለችው፡፡ መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት÷ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል፤ ከአንቺ የሚወለደውም ቅዱስ ነው፤ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፡፡ እነሆ÷ ከዘመዶችሽ ወገን የምትሆን ኤልሣቤጥ እርስዋ እንኳ በእርጅናዋ ወንድ ልጅን ፀንሳለች፤ መካን ትባል የነበረችው ከፀነሰች እነሆ÷ ይህ ስድስተኛው ወር ነው፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለምና›› አላት፡፡ ማርያምም መልአኩን ‹‹ እነሆኝ÷ የእግዚአብሔር ባሪያው አለሁ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› አለችው፤ ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእርስዋ ዘንድ ሄደ፤ አካላዊ ቃልም በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተፀነሰ፡፡ (ሉቃ. ፩፥፳፰-፳፱፣ ኢሳ. ፯÷፲፬)

በክርስቶስ ክርስቲያን የምንባል የእግዚአብሔር ልጆችም ይህን ቃል በማሰብ ድኅነታችን ተስፋ እናደርግለን! አምላችን እግዚአብሔር እንደ ቸርነቱና ምሕረቱ ኃጢአታችንን ይቅር ብሎ ያድነን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!