በዓለ ቅዱስ ሚካኤል

ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በእስክንድርያ ከተማ ክላወባጥራ የተባለች ንግሥት የበጥሊሙስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኲራብ ነበር፤ ሕዝቡም ሰኔ በገባ በዐሥራ ሁለት የዚህን ጣዖት በዓል ያከብሩ ነበር። ይህንም ግብራቸው እንዲተው አባታችን እለ እስክንድሮስ ቢነግራቸው አይሆንም አሉት።

በኋላም ጻድቅ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሲነግሥ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኃዋ ወአብያተ ጣዖታት ይትዐፀዋ የሚል አዋጅ ስለወጣ በዚህ ምቹ ጊዜም የጣዖት አምልኮ እንደምን ያለ ክፉ ግብር እንደሆነና በጎ ዋጋም እንደሌለው ነግሮ እንዲተዉ ቢጠይቃቸው እኛስ ይህን አንተውም አሉት። እርሱም በጥበብ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ይህን ግብር ብትተው በዚህች ቦታ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን እንሠራለን። መሥዋዕታችሁንም በዚያ ለቅዱስ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ አላቸው።›› በዚህ ተደስተው ተመለሱና ያንን የጣዖት ቤት አፍርሰው እጅግ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ስም ሠሩ። የመልአኩንም በዓለ ንግሥ በዚህች ዕለት አከበሯት። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ የከበረ የመላእክት አለቃ የመልአኩ የሚካኤል የመታሰቢያውን በዓል በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይከበራል፡፡

ንዑድ ክቡር የሚሆን የዋህ ተአዛዚ ባሕራንን በሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን ያዳነበት ድንቅ ተአምርም ይህ ነው። አንድ ደግ ሰው በዚያች ይኖር ነበር። ክፉ ጎረቤት ነበረው። ይህም ደግ ሰው ነዳያንን እጅግ የሚወድ የቅዱስ ሚካኤልንም ዝክር ሳያስታጉል የሚዘክር ሰው ነው። በዚህ ሥራው ግን ይህ ክፉ ጎረቤቱ ይዘብትበት ነበር። በኋላም ያ ደግ ሰው የሚሞትበት ቀን ሲደርስ ሚስቱን ዝክረ ሚካኤልን እንዳታቋርጥና ነዳያንን እንዳትዘነጋ ነግሯት ያርፋል። እርሷም ፀንሳ ነበርና እርሱ ከሞተ በኋላ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። ምጥም ቢጠናባት ወደ መልአኩ ጮኸች፤ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ተራዳትና መልከ መልካም የሆነ ልጅ ወለደች። መልአኩም እንዲህ ሲል አላት። ‹‹ልጅሽ የዚህ የጎረቤትሽን ሀብት ይወርሳል።›› መልአኩም ለጎረቤታቸው ጆሮውንም ከፍቶለት ነበርና ይህን ነገር ሰማ። በዚህም ‹‹በምን ምክንያት ወስጄ ላጥፋው›› ብሎ ሲያስብ ሴቲቱ እጅግ ብቻዋን ለማሳደግ ተቸገረች፤ ‹‹ላሳድግልሽ፤ ለአንቺም ይኸው ገንዘብ እሰጥሻለሁ›› ብሎ ብዙ ወርቅ ሰጣት። እርሱም ‹‹ከእንግዲህ አርፋለሁ›› ብሎ ልጁን መጣያ ሳጥን ያዘጋጅና ወደ ባሕር ይጥለዋል። ባሕሩም ሩቅ ሀገር ወስዶት ከዳር ይጥለዋል፤

ከዚህም በኋላ አንድ በጎቹን ያሠማራ ሰው ያገኘዋል። ያንንም ሳጥን ወስዶ ከቤት ያኖረዋል፤  በምን መክፈት እንደሚችል ሲያስብ ዳግመኛ ወደ ባሕሩ እንዲሄድ እግዚአብሔር ሐሳብ ያሳድርበትና ተነሥቶ ይሄዳል። ሲሄድም ዓሣ አጥማጅ ያገኝና ዓሣ ለእርሱና ለቤተሰቡ እንዲያጠምድለት ይነግረዋል። ያም ዓሣ አጥማጅ ሲያጠምድ ታላቅ ዓሣ አገኘና ሰጠው። ዋጋውን ሰጥቶም ወደ ቤት ተመለሰና ሆዱን ቢሰነጥቀው ቁልፉን በዚያ አገኘው። በዚያም ቢከፍተ መልከ መልካም ልጅ አገኘ። ልጅም ስላልነበረው እጅጉን ተደሰተ። ባሕራን ብሎም ሰየመው።

ከብዙ ጊዜያት በኋላ ያ ክፉ ሰው ከንግድ ተመልሶ በዚያ መንገድ ሲያልፍ መሸበትና ከዚህ ሰው ቤት አደረ። ባሕራንንም ተመለከተውና ሰውየውን ልጁ እንደሆነ ለማወቅ ታሪኩን ጠየቀው፤ ሰውየውም የሆነውን ሁሉ ነገረው። ክፉ ሰውም እንዳልሞተ ባወቀ ጊዜ ደነገጠና መልእክት ሊልከው ስለሚፈልግ የባሕራንን አባት ልጁን እንዲሰጠው ጠየቀው። እርሱም ተስማምቶ ሰጠው። በክፋትም ተነሣሥቶ ባሕራንን እንዳገኘው እንዲገድለው ለአገልጋዩ ደብዳቤ ጽፎ አገልጋዩና እርሱ ብቻ የሚያውቁትን ማኅተም አድርጎ ሰጠው። ‹‹ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፡፡ ማንም ዐይወቅ፡፡››  ለባሕራንም ለመንገዱ የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው፡፡

የራሱን የሞት ደብዳቤ እንደያዘ ሳያውቅም ባሕራን ወደታዘዘበት ሥፋራ ተጓዘ፤ ከዚያ ሰው ቤት ለመድረስ ሲቀርብ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው›› አለው፡፡ ‹‹ወደ ዕገሌ ሀገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለ ጠጋ የተጻፈች መልእክት ናት›› አለው፡፡ ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፤ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡ የሞቱን ደብዳቤ ያቺን የሞት መልእክት ደምስሶ በሕይወት ቀየረለት። በእርሱም ፈንታ በንፍሐት ለውጦ እንደህ ብሎ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን፣ ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን፣ ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ፡፡ እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም እገሌ ሆይ! በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት፡፡››

አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ‹‹ወደ ባለ ጠጋው ቤት ሂደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ስጠው፡፡ በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው፡፡ እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ›› አለው፡፡ ባሕራንም ‹‹እሺ ጌታዬ ያዘዝኸኝን ዅሉ አደርጋለሁ›› አለ፡፡

ባሕራንም ወደ ባለ ጠጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው፡፡ ካአነበባት በኋላም በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ፡፡ አስተውሎም እርግጠኛ እንደ ሆነ ዐወቀ፡፡ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለ ጠጋውን ልጅ አጋቡት፡፡ ዐርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ፡፡ ሀብቱንም ሁሉ አወረሱት።

ከዚህ በኋላ ባለ ጠጋው ከሄደበት ሲመለስ ጊዜ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ‹‹ይህ የምሰማው ምንድነው›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እነርሱም ‹‹ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት፡፡ እነሆ ለዐርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው፡፡ ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝኽ ሰጥተውታል›› አሉት፡፡ ይህንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ፡፡

ባሕራንም ከዚህ በኋላ የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር በሚገ’ባ እየዘከረና ለቤተ ክርስቲያኑም እየታዘዘ የሚያገለግል ሆነ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የዚህም የከበረ መልአክ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን፤ ለዘላለሙ አሜን፡፡