በዓለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ

ከመጽሐፈ ስንክሳር

በመስከረም ፪ ቀን የካህኑ ዘካርያስ ልጅ የከበረ አጥማቂው ዮሐንስ ሕግን አፍራሽ በሆነ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ ሰማዕት ሆነ!

ይህም እንዲህ ነው፤ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ነቢዩ ዮሐንስ በገሠጸው ጊዜ ፊልጶስ ወንድሙ ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስም የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ይለው ነበርና። ቅዱስ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድሙን የፊሊጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሌላም ያደርገው ስለነበረ ክፉ ሥራ ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም በተግሣጽ ላይ ተግሣጽን ጨመረ። ስለዚህም ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አኖረው።

ሄሮድስም ዮሐንስን ይፈራው ነበር። ጻድቅ ቅዱስ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበርና ብዙ ይጠባበቀውም ነበር። ሄሮድስ የተወለደባትን ቀን በዓል የሚያከበርባት ዕለት ነበረች፡፡ መኳንንቱን አለቆቹን መሣፍንቱን ሹሞቹን በገሊላ አገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።

የሄሮድያዳ ልጅም ወደ አዳራሹ ገብታ ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፣ ከእርሱ ጋር በማእድ የነበሩትንም፤ ንጉሡም ያችን ብላቴና ‹‹የምትሺውን ለምኚኝ እሰጥሻለሁ›› አላት፡፡ እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ሊሰጣት ማለላት፡፡

ወጥታም ‹‹እናቷን ምን ልለምነው?›› አለቻት፣ እናቷም ‹‹የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ›› አለቻት። ያን ጊዜም እየሮጠች ወደ ንጉሡ ገብታ ‹‹የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ›› ብላ ለመነችው።

ንጉሡም ስለ መሐላው አብረው ስለነበሩት ሰዎች አዘነ እምቢ ሊላት ግን አልወደደም። ያንጊዜም ባለወጎችን ላከ በእስር ቤትም ሳለ የዮሐንስን ራስ ቆረጡ፣ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጧት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች።

በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋፄ ሆነ። ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮህ ዘልፋዋለች። ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ መጥተው በድኑን ወስደው ቀበሩት።

የቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መስከረም