በዓለ ሆሣዕና

ያቆን ዮሐንስ ተመስገን

መጋቢት ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ፈጣሬ ዓለማት አምላካችን እግዚአብሔር ምድርን ከነልብሱ ሰማይን ከነግሳንግሱ ፈጥሮ ብቻ አልተወም፤ ገዣቸው ይሆን ዘንድ በመጨረሻው የፍጥረት ቀን አዳምን በእጁ አበጃጀው እንጂ። ፈጥሮም የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበት። አዳምም ሕያው ፍጥረት ሆነ። እንዲነዳቸው፣ እንዲገዛቸው ልዑል እግዚአብሔር አዳምን በፍጥረታት ላይ በመሾም ኃጢአት በማይደርስባት ገነት በግርማ አስቀመጠው።

አዳም እግዚአብሔር ያዘዘውን ረሳ፤ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ለመታዘዝ ምልክት እንድትሆን የተነገረውን ዕፀ በለስ ሊቆርጥ ተነሣ። በመጨረሻም እጁን ልኮ ቆረጠ፤ በላም፤ በመብላቱም ወደቀ፤ ከገነትም ተባረረ።

ከገነት ለተባረረው አዳም በደሉን ይቅር ይለው ዘንድ እግዚአብሔር ከሰው ተወለደ፤ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋሐደ፤ ወደ ግብጽ ተሰደደ፤ በኋላም በዮርዳኖስ ተጠመቀ፤ ከተጠመቀም በኋላ ብሕትውናንና የገዳም ሕይወትን ሊያስተምር ወደ ገዳመ ቆረንጦስ ሄደ። ከ፵ ቀን በኋላም ተመልሶ ደቀ መዛሙርትን ማስተማር ጀመረ፤ ይህ ሂደት ሦስት ዓመት ዘለቀ፤ የጌታችን ዕድሜም ሠላሳ ሦስት ዓመት ሞላ።

ጌታችን ከተወለደ ፴፫ የምሕረት ዘመናት ተቆጠሩ። ዕለቱ እሑድ፣ ቀኑ መጋቢት ፳፪ ነበር። በምድር የሚመላለስበትን ዘመን ሊጨርስ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ለደብረ ዘይት ትራራ ቅርብ ወደ ሆነችው ቤተ ፋጌና ቢታንያ መንደር ገሰገሰ፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ጴጥሮስና ዮሐንስን እንዲህ አላቸው፤ ‘‘በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደርም በገባችሁ ጊዜ ሰው በላዩ ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ፤ ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖርም ጌታው ይሻዋል በሉ’’ አላቸው፤ (ማር.፲፩፥፪) ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም እንደታዘዙት አደርጉ፡፡

የታሰሩትን ሊፈታ መጥቱዋልና የታሰርውን ፍቱልኝ አለ፤ ሰውን ሁሉ ከማዕሰረ ኃጢአት የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሰ ሲያጠይቅ ነው። በአህያ ላይ ሁኖ ሲገባም የሚበዙት ሕዝብ ለጌታችን ክብር ለአህያዋ ልብሳቸውን ጎዘጎዙ፤ ልብስ ገላን ይሸፍናልና ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ። በፊት በኋላ ሁነው ‘‘ለወልደ ዳዊት መድኃኒት መባል ይገባዋል’’ እያሉ አመሰገኑ፤ ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነውና “ሆሣዕና በአርያም” ሲሉ ቀኑን ዋሉ፡፡ በፊቱ ያሉት የሐዋርያት በኋላው ያሉት የነቢያት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሌላም ትርጉም የብሉያትና የሐዲሳት ምሳሌዎች ሁነዋል። በዚህም የፊተኛውም የኋኛውም ዘመን ጌታ መሆኑ ተገልጧል፡፡

ሕዝቡ ሲዘምሩ የያዙት የዘንባባ ዝንጣፊም ጥንቱን አባቶቹ በብሉይ በዘንባባ ይገለገሉበት የነበረውን ያሳያል፤ እነ አብርሃምና እነ ይስሐቅ ሲወለዱ የዘንባባ ሰሌን ይዘረጋላቸው ነበርና። እሥራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ሰሌን ይዘው አመስግነው ነበርና። እሾህ አለው ትእምርተ ኃይል ትእምርተ መዊዕ አለህ ማለታቸው ነው። (ትር. ወን. ዘማቴዎስ)

ወደ ቤተ መቅደሱ ሲደርስም ሁለት ክፋቶች ተስተውለዋል። ቤተ መቅደሱን ለንግድ መገበያያነት ያዋሉት እና ለጌታችን ምስጋና እንዳይቀርብ ሲከለክሉ የታዩ የቤተ መቅደሱ አካባቢ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጌታችን ለሁለቱም መልስ ሰጠ። የምስጋና መቅደሱን ለመገበያያነት ያደረጉትን ‘‘ቤቴ የጸሎት ቤት ነው’’ ብሎ እርግብና ዋኖሳቸውን ገለባብጦ አባረራቸው፡፡ (ዮሐ.፪፥፲፮) ምስጋና የከለከሉትንም አስገድዶ ራሱን አያስመልክምና “እናንት ባታመሰግኑኝ የቢታንያ ድንጋዮች ያመሰኙኛል” ብሎ ምስጋናው በፍጥረት ሁሉ ዘንድ እንጂ ከሰው ወገን ብቻ አለመሆኑን ግዑዛኑን ድንጋዮች ለምስጋና አስነሥቷል፡፡ ካህናቱ ቢከለክሉም ሕፃናቱን አበረታቸው። በዚህም ማንም የእግዚአብሔርን ምስጋና ሊከለክል እንደማይችል በሚገባ አሳያቸው።

ቤተ ክርስቲያንን ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሰዎች ከቤተ ፋጌ ነጋዴዎች መማር አለባቸው። ጌታም በዕለተ ሆሣዕና ያስተማረው ይህን ነው። በሐዋርያት እግር የተተኩ ጳጳሳትና ሊቃውንት ባያስቆሙ እንኳን በገነት መግቢያ ሚዛን  ተመዝነው መውደቃቸው እሙን ነው። ማንም የአገልግሎት ስፍራን ከጸሎት ይልቅ ለጥቅም፣ ከምስጋና ይልቅ ለክርክርና ጭቅጭቅ ቢያውል እንደ ቤተ ፋጌዋ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ፈታሒ በርትዕ ኮናኒ በጽድቅ ነውና በጥበቡ ለይቶ ያባርራል። መች እንድሚቀጣ እርሱ ያውቃል።

እግዚአብሔር ለምስጋና የሚሰለፉትን እየመረጠ ምስጋናውን የሚያስተጓጉሉትን በሌሎች እየተካ ዓለም ታልፋለች። ለምስጋና ለሚሰለፉት መንግሥተ ሰማይ ትተካለች። ምስጋናውን ሲያደናቅፉ ለነበሩ እንደ ቤተ ፋጌ ነጋዴዎችና አናመሰግንም ብለው አፋቸውን እንደዘጉ ምቀኞች ከርስታቸው ሰማያዊቷ ቤት ወጥተው ከእግዚአብሔር ቤት ተለይተው ገሃነመ እሳት ይወርዳሉ። ጉልበት ሳይደክም ወደ ገዳማት ማጓዝ፣ ዐይን ሳይፈዝ ለጸሎት መትጋት፣ ጀሮ ሳይደነዝዝ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት፣ ምላስ ሳይታሰር ለምስጋና መትጋት ይገባል። ይህ ከሆነ ወደ በእግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንጂ በሆሣዕና እንደሆነው ሁሉ ወደፊት ገነትን በሚጠብቁ ልዑላን መላእክት በእሳት ሰይፍ እየተባረሩ በሰይጣን ሠራዊት እየተንገላቱ ወደ ሲዖል መውረድ የለም። ምስጋናውን ሲከለክሉ ዕድላቸው እንደተወሰደባቸው ሳይሆን ለምስጋና የዘንባባ ዝንጣፊ እንድያዙት ያድርገን። ቤተ መቅደሱን ለንግድ ሳይሆን ያለንን ጨርቅ እንኳን ለጌታችን ክብር የምናነጥፍበት የተሰበረ ልብ  ያድለን፤ አሜን!