በኮሌራ በሽታ ጉዳት ለደረሰባቸው ምእመናን ድጋፍ ተደረገ 

በካሣሁን ለምለሙ 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የዳሰነች ሕዝበ ክርስቲያን የእርዳታ ድጋፍ ተደረገ፡፡

የኮሌራ ወረርሽኝ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ዳሰነች ወረዳ በመከሠቱ ምክንያት የሃያ ሦስት ምእመናን ሕይወት ማለፉን  የከተማዋ ርእሰ መስተዳድር አቶ ቀብራራው ተክሌ መግለጣቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በዳሰነች ወረዳ ኡሞራቲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ጉዳት ለደርስባችው ምእመናን ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም የማጽናኛ ትምህርት ሰጥተው፤ በከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ተገኝተውም በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ልማትና ሕንጻ አሠሪ ማኅበር አማካይነት የተዘጋጀውን ርዳታ ድጋፍ አድርገዋል ሲል የዘገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡

የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ልማትና ሕንጻ ቤተክርስቲያን አሠሪ ማኅበር  ጸሐፊ ቀሲስ አበባየሁ፤ ማኅበሩ በሀገረ ስብከቱ እየሠራ ያለውን የስብከተ ወንጌልና የልማት ሥራ አብራርተዋል፤ አያይዘውም በአዲስ አበባ የሚገኙ አባሎቻቸውን አስተባብረው በወረርሽኙ ለተጎዱ ምእመናን የምግብ እህልና የቁሳቁስ ርዳታ ማድረጋቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ያኩማ ዐሥራት፤ ከአሁን በፊት በደቡብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ጊዜያት በሰባት ቦታዎች በሽታው የታየ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅኃ በዳሰነች ወረዳ ወረርሽኙ ተቀስቅሶ ሃያ ሦስት ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል ማለታቸውን ከዘገባው የተገኘው መርጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀድማ በመድረስ በወረርሽኙ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ ማድረጓ የዞኑን ምክትል አስተዳዳሪ እንዳስደሰታቸው የዘገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ልማትና ሕንጻ አሠሪ ማኅበር ከብፁዕነታቸው ጋር በመሆን በኡሞራቲ ከተማ ተገኝቶ ርዳታ በማድረጉ ምስጋና ማቅረባቸውንም አክሎ ገልጿል፡፡